Tuesday, 18 February 2020 00:00

የቻይናው ኩባንያ በኡጋንዳ አባይን ለመገደብ አቅዷል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  ፓዎርቻይና ኢንተርናሽናል ግሩፕ ሊሚትድ የተባለው የቻይና ኩባንያ፣ በኡጋንዳ፣ በአባይ ወንዝ ላይ በ1.4 ቢሊዮን ዶላር ወጪ በአገሪቱ ትልቁን የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ ለመስራት እንዲፈቀድለት ለአገሪቱ መንግስት ጥያቄ ማቅረቡን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
ሮይተርስ አገኘሁት ያለውን ሰነድ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ የቻይናው ኩባንያ ለአገሪቱ መንግስት ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ካገኘና 840 ሜጋ ዋት ሃይል የማመንጨት አቅም ይኖረዋል የተባለው አያጎ የተሰኘው የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ ተጠናቅቆ ስራ የሚጀምር ከሆነ፣ የኡጋንዳ የኤሌክትሪክ ማመንጨት አቅም በ40 በመቶ ያህል ሊያድግ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
ኩባንያው አያጎ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብን ለመገንባት ያቀደው ኮዮጋ እና አልበርት በተባሉት የኡጋንዳ ሃይቆች መካከል በሚገኘው የአባይ ወንዝ ክፍል ላይ መሆኑን ዘገባው ጠቁሞ፣ የአገሪቱ የኤሌክትሪክ ሃይል ባለስልጣን ቃል አቀባይ ጂሊየስ ዋንዴራም፣ የቻይናው ኩባንያ ያቀረበው የግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ሃሳብ፣ ለህዝቡ ቀርቦ አስተያየት እንደሚሰጥበት መናገራቸውንም አመልክቷል፡፡
የቻይናው ኩባንያ ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የሚሆነውን በጀት በከፊል እርዳታና በብድር ለመሸፈን ማቀዱን የጠቆመው ዘገባው፤ ፕሮጀክቱ የኡጋንዳን አጠቃላይ የኤሌክትሪክ ሃይል ምርት ወደ 2 ሺህ 800 ሜጋ ዋት ያደርሰዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጧል፡፡

Read 3368 times