የመፃህፍቱ አዘጋጅ ጆሴፍ ፍራንሲስ በዓለማየሁ መፅሃፍ ምስጋና ላይ ባሰፈረው ማስታወሻ “የልኡል ዓለማየሁን አሳዛኝ ታሪክ የሚያብራሩ ምንም ሰነዶች በሌሉበት፤ በተለያዩ ገጠመኞች የተሞላውን የልኡሉን ሕይወት ለመተረክ መነሳቴን እጅግ ፈታኝ ሆኖ አግኝቼዋለሁ” ብሏል፡፡
በሁለቱም መፃህፍት ላይ የሰፈረውን የጀርባ አስተያየት (Blurb) የፃፉት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት “አፄ ቴዎድሮስ” የተሰኘው መፅሃፍ ላይ በሰጡት ምስክርነት “ከኢትዮጵያ ታላላቅ ነገስታት አንዱ የሆኑት አፄ ቴዎድሮስ ከሀገሪቱ አስደናቂና ተወዳጅ መሪዎች አንዱ ናቸው ቢባል ተገቢ ነው፡፡ የማያጠያይቅ ጀግንነት ያላቸውና የዘመናዊ ሥልጣኔ አቀንቃኝነታቸው ልዩ የሚያደርጋቸው ንጉስ ናቸው፡፡ ጆሴፍ ፍራንሲስ ስለዚህ ስለ አፄ ቴዎድሮስ ፅሁፍ ሊደነቅ ይገባዋል” ሲሉ አወድሰውታል፡፡ የአሁኑ “ልኡል አለማየሁ” መፅሃፍ በመጀመርያው እትም ላይ ያልተካተቱ መረጃዎችና ምስሎችን እንዳካተተ ለአዲስ አድማስ የተናገረው አዘጋጁ፤ “አማራ አቀፍ ልማት ማህበር” ለመፃህፍቱ ህትመት ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሶ ለማህበሩ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡ መፃህፍቱ በ“ቡክ ዎርልድ” ሁሉም ቅርንጫፎቹ የሚገኙ ሲሆን የእያንዳንዱ ዋጋ 50 ብር እንደሆነ ታውቋል፡፡ ጆሴፍ ፍራንሲስ “የአድዋ ጦርነት” የሚል መፅሃፍም አዘጋጅቶ ለንባብ ማቅረቡ የሚታወቅ ሲሆን የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ በመገንባት ረገድ የላቀ አስተዋፅኦ ሊያበረክት የሚችል “የኢትዮጵያ ድንቃድንቆች” የተሰኘ መፅሃፍ በቅርቡ ለገበያ እንደሚያቀርብ አስታውቆዋል፡፡ ጆሴፍ በአሁኑ ጊዜ በግሪክ ኮሙኒቲ ስኩል በማህበራዊ ሳይንስ መምህርነት እያስተማረ የሚገኝ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ 29 ዓመት ገደማ አስቆጥሮዋል፡፡