Saturday, 26 October 2019 11:55

ኮሜርሽያል ኖሚኒስ ‹‹ሰላም የገና ባዛርና ፌስቲቫል››ን ያዘጋጃል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

   ለኤግዚቢሽኑ 60 ሚ ብር፣ ለግቢው ማስዋቢያ 20 ሚ.ብር በጀት መድቧል
                     
             በንግድ ባንክ ባለቤትነት በ1958 ዓ.ም በኢትዮጵያ ንግድ ሕግ መሰረት የተቋቋመውና ዘርፈ ብዙ ስራዎችን በመላ አገሪቱ በሚገኙ 40 ቅርንጫፎቹ የሚያከናውነው ኮሜርሻያል ኖሚኒስ (CN)፤ የዘንድሮውን የገና በዓል ‹‹ሰላም የገና ባዛርና ኤግዚቢሽን›› ለማዘጋጀት ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ፡፡
ኮሜርሻያል ኖሚኒስ ከተስፋዬ አድርሴ ፕሮሞሽን ጋር በመተባበር፣ እጅግ ግዙፍና ትልቅ ባዛርና  ኤግዚቢሽን ለማዘጋጀት 60 ሚ.ብር በጀት የመደበ ሲሆን የኤግዚቢሽን ማዕከሉን ግቢ ለማዘመንና ለሸማቹም ሆነ ለሻጩ ምቹ ለማድረግ 20 ሚ.ብር መያዙን የኤግዚቢሽን ገበያ ልማት ማዕከል፣ የኮሜርሺያል ኖሚኒስና የተስፋዬ አድርሴ ፕሮሞሽን ሃላፊዎች ገልፀዋል:: ከትላንት በስቲያ ሀሙስ አመሻሽ ላይ ሀላፊዎቹ በካፒታል ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ባዛርና ኤግዜቢሽኑ ለ24 ተከታታይ ቀናት እንደሚቆይና እስከ 1.ሚ የሚደርስ ሰው ይጎበኘዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡
የኤግዚቢሽን ማዕከል በምን መልኩ ተሰርቶ ለኤግዚቢሽንና ፌስቲቫሉ ክፍት እንደሚሆን በአኒሜሽን ለእይታ የቀረበ ሲሆን ሻጭም ሆነ ጎብኚ ፀሐይና አቧራ እንዳያገኘው ጽዳቱን የጠበቀ እንዲሆን፣ የልጆች መጫዎቻ፣ እንዲኖረውና ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን መታሰቡንና ለዚህም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኤግዚቢሽንና ፌስቲቫሉ በርካታ የውጭና የአገር ውስጥ ተሳታፊዎች የሚገኙ ሲሆን ሰላም የሚቀነቀንበት፣ ደረጃውን የጠበቀ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማች የሚቀርብበትና የመዝናኛና የፌስቲቫልነት ለዛው ያማረ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑም ታውቋል፡፡
የኤግዚቢሽኑና የገበያ ልማት ዳይሬክተር አቶ ታምራት አድማሱ፤ ኮሜርሺያል ኖሚኒስ የኤግዚቢሽን የጨረታ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ቢሆንም፣ የኤግዚቢሽን አዘጋጆች ትልልቅ ሥራዎችን እየሰሩ መሆኑን አስታውሰው፣ በስራ ዕድል ፈጠራም ቢሆን በየዓመቱ 8ሺህ ያህል ዜጎች ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመው፣ በእንቁጣጣሽ ኤክስፖ ኢዮሃ አዲስ ኢንተርቴይመንትና ኢቨንት ለ1700 ያህል ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩን አስታውሰዋል:: በኮሜርሻያል ኖሚኒስ በኩል ደግሞ ለ2 ሺ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጠርም ተናግረዋል:: ማዕከሉ ለጊዜው እንዲህ አምሮ መዘጋጀቱ ለሁለቱም ወገን ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ማዕከሉ በ15 ቢ ብር በጀት በትልቅ ቦታ ላይ ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነ ኮንቬንሽን ሕንጻ ለመገንባት መዘጋጀቱን ጨምረው ገልጸዋል:: ከኮሜርሺያል ኖሚኒስ ጋር በአስተባባሪነት አብሮ የሚሰራው ሲሳይ አድርሴ ፕሮሞሽን በአውሮፓና በአሜሪካም ጭምር ተመሳሳይ ሁነቶችን በማዘጋጀት እንደሚታወቅም ተገልጿል፡፡
ኮሜርሻያል ኖሚኒስ ከተቋቋመበት 1958 ዓ.ም ጀምሮ የአገር ውስጥ የሰው ሀይል አቅርቦትና አስተዳደር፣ የኢትዮ ቴሌኮም ምርቶችን በአገር አቀፍ ደረጃ የማከፋፈል፣ የመንግስትና የግል ሕንጻዎችንና ቤቶችን በውክልና ማስተዳደር፣ ሁነት (ኢቨንት) ማዘጋጀት፣ የዌስተርን ዩኒየን የሐዋላ አገልግሎት መስጠት፣ በተለያዩ አማራጮች የደሞዝ ክፍያ አገልግሎት መስጠት፣ የፕሮቪደንት ፈንድና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ማስተዳደር፣ ሕንጻዎችን መግዛትና መሸጥ፣ የተለያዩ ገቢዎችን መሰብሰብ፣ ሌሎች የሶስተኛ ወገኖችን ሥራ በውክልና መስራት፣ ሲ.ቢ.ኢ ብር የባንክ ውክልና አገልግሎት መስጠትና አክሲዮን ማሻሻጥ ከሚሰራቸው በርካታ ሥራዎች ጥቂቶቹ እንደሆኑም በዕለቱ ተገልጿል፡፡


Read 1092 times