Saturday, 12 October 2019 12:26

ዝክረ - ኤልያስ መልካ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  አንፀባራቂው የሙዚቃ አቀናባሪ


           እውቁ የሙዚቃ አቀናባሪ ኤልያስ መልካ፣ የዛሬ 19 ዓመት ከ‹‹አዲስ አድማስ›› ጋዜጣ ጋር ለሁለት ሳምንት የዘለቀ ቃለ ምልልስ አድርጎ ነበር- ነሐሴ 5 እና 12፤ 1993 ዓ.ም፡፡ ያኔ የ23 ዓመት ወጣት የነበረው ኤልያስ መልካ፤ ከተለያዩ የሙዚቃ ባንዶች ጋር ከመስራቱም ባሻገር በአንጋፋዋ ድምፃዊ በአስቴር አወቀ ኮንሰርት ላይ በጊታሪስትነት ተመርጦ፤ ከሚሊኒየም ባንድ ጋር መጫወቱ ተጠቅሷል - በቃል ምልልሱ፡፡ ከጓደኞቹ ጋር ላስታ ባንድን መስርቶም በንቃት እየሰራ ነበር፡፡ የሙዚቃ አብዮቱን ያቀጣጠለበትን ‹‹አቤን›› የተሰኘ ዘመናዊ የሪኮርዲንግ ስቱዲዮ ያቋቋመውም ያኔ ነው፡፡
በዚህ ስቱዲዮው ያቀናበረው የመጀመሪያ ሥራው ደግሞ የዕውቁ ድምፃዊ ቴዲ አፍሮን ‹‹አቡጊዳ›› የሚል አልበም ነበር:: ከጋዜጣው ጋር ላደረገው ቃለ ምልልስ ሰበብ የሆነው፣ ከቴዲ አፍሮ ጋር ከሰሩት ካሴትና የሙዚቃ ኮንሰርት ጋር በተያያዘ በመሃላቸው የተፈጠረው ቅሬታና እሰጥ አገባ ነበር፡፡ የሚገርመው ታዲያ ኤልያስ መልካ ‹‹ተጣልተናል›› ብሎ የቀድሞ ጓደኛውንና የሙያ አጋሩን ቴዲ አፍሮን በሃሰት ወይም በማጋነን ለማጣጣልና ስም ለማጥፋት አልሞከረም፡፡ የተፈጠረውን ችግርና ቅሬታ በቀጥታና በጨዋነት ነበር ለአዲስ አድማስ ያብራራው፡፡ ከዚያም ባሻገር ለቴዲ አፍሮ የድምፅና የአዘፋፈን ችሎታ ሽንጡን ገትሮ ተከራክሯል - ከጠያቂው ጋዜጠኛ ጋር፡፡ በአገራችን እንደተለመደው፣ ውሸትም ጨምሮ ቢሆን ለማውገዝ ፈጽሞ አልዳዳውም፡፡
አዲስ አድማስ ጋዜጣ በወቅቱ በአርቲስቶቹ መሃል የተፈጠረውን ውዝግብ ብቻ በማውጣት አልተወሰነም፡፡ የጋዜጣው መስራችና ባለቤት የነበረው አቶ አሰፋ ጎሳዬ፤ በአዲስ ዓመት መባቻ ላይ ኤልያስ መልካንና ቴዲ አፍሮን በማስታረቅ፣ አብረው እንዲሰሩ ቃል አስገብቷቸው ነበር፡፡  በጋዜጣው ላይም የሁለቱ አርቲስቶች ፎቶ፣ ገጣሚ ነቢይ መኮንን  ‹‹ሽማግሌ ሊማር ልጆቹን እያየ›› በሚል ከቋጠረላቸው ግጥም ጋር ታጅቦ ወጥቷል:: የምስራቹን ለአንባቢያን ለማጋራት፡፡ እስቲ ከግጥሙ ላይ ጥቂት ስንኞችን መዝዘን እናስታውሳችሁ፡-
‹‹ዘመን ቢራቢሮ
ዘመን ቢራቢሮ
ይኸው በርሮ በርሮ
አደይ አበባ ሆይ
ቀስተ ዳመናው ህብር
እዩ ፈገግታ አምሮ
ናፋቂ መስቀል ወፍ
ጆሮሽን አቅኚና
ስሚ ቅኝት ሰምሮ
ልጅ አዋቂ ትውልድ ባንድ ተነባብሮ
ምን ይሆን ምልኪው ብላቴን ሊገዝፍ
ምን ይሆን ትርጉሙ ሕጻን ጀልባ ሲቀዝፍ
ምንድን ይሆን ፍቺው ፀደይ ሳቅ ሳቅ ሲለው?
መስከረም ፍርግርግ እስክስታ ሲቃጣው?...››
*  *  *  *
ዕውቁ የሙዚቃ አቀናባሪ፣  የዘፈን ግጥምና ዜማ ደራሲ ኤልያስ መልካ፣ በወቅቱ ከአዲስ አድማስ ጋር ካደረገው ቃለ ምልልስ ውስጥ ውዝግቡን አስቀርተን፣ በሙዚቃና ማቀናበር ዙሪያ የሰጠውን ትንተና ለቅኝት ያህል እንዲህ አቅርበነዋል፡-
ሙዚቃን በኮምፒዩተር ማቀናበር
ዜማ ይመጣልሃል - ከዜማ ደራሲ፡፡ ለዜማው የሚስማማ ሪትም (ምት) ትመርጥለታለህ - ሬጌ፣ የአፍሪካ፣ ዲስኮ፣ ጃዝ፣ አማርኛ ምት ወዘተ፡፡ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾች ምን ምን እንደሚጫወቱ ትመርጣለህ፡፡ ጊታሪስቱ እንዴት እንደሚጫወት… ኪቦርድ፣ ሳክስፎን፣… በየቅደም ተከተልም ሆነ በህብረት… ለዜማውና ለምቱ የሚያስፈልግ ሙዚቃ ትመርጣለህ፣ ታስተካክላለህ፡፡ ሁሉንም ራስህ ልትጫወተውም ትችላለህ፤ በኮምፒውተር የማዋሃድና የማቀነባበር እገዛ፡፡ ሙሉ ባንድ የሚሰራውን ነገር ጊታር፣ ሳክስፎን፣ ባስ… ሳያስፈልግህ ብቻህን እያንዳንዱን መሳሪያ በኪቦርድ እየተጫወትክ በኮምፒውተር ታቀናብረዋለህ፡፡ አሁን ‹‹አቤን›› በሚል መጠሪያ አዲስ ስቱዲዮ እየከፈትኩ ነው፡፡ በውጭ አገር አገር ከሚሰራ የካሴት ህትመት (Recording) ጋር የሚስተካከል ጥራት የሚያስገኙ ዘመናዊ መሳሪያዎችን አስመጥቻለሁ፡፡
ጥሩና ተወዳጅ ሙዚቃ መስራት
… ስትሰማው የሚያስደስትህና ስትሰራው ከበድ የሚልህን ትመርጣለህ፡፡ ይሄ ከባድ ነው - ጥሩ ነው ትላለህ፡፡ አንድን ሙዚቃ ስትሰማ በውስጡ የምታገኘውን የፒያኖ ድምጽ ብቻ ትወደው ይሆናል፡፡ በሌላ ሙዚቃ ደግሞ ሳክስፎን ወዘተ፡፡ ሌላው ደግሞ አንድ ሙዚቃ ሲወጣ፣ ብዙ ሰው ከወደደውና ከተቀበለው ጥሩ ነው ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ሙዚቃ ውስጥ ግርግር፣ ቄንጥ ወዘተ ስለበዛበት ብቻ ጥሩ ሙዚቃ ነው ተብሎ ሊነገርለት ይችላል፤ ግን አድማጭ አይወደውም፡፡ እውነትም ጥሩ ሙዚቃ አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በጥንቃቄ፣ በከባድ ችሎታ የተሰሩ፣ በሙዚቃ ባለሙያዎች ዘንድም ጥሩ ሙዚቃ መሆናቸው የሚመሰከርላቸው ዘፈኖች፣ አብዛኛው አድማጭም ሲወዳቸው ታያለህ:: እንዲህ ስል ግን ጥሩ ሙዚቃ ሆኖ አድማጭ የሚያጣ የለም ማለት አይደለም፡፡ ሁለቱንም ማጣጣም ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ጥሩና ተወዳጅ ሙዚቃን መስራት፡፡
ድምፅና ልምምድ
… ካሴት ስትሰራ፣ ሁሉም ነገር ተቀርፆ ካለቀ በኋላ በካሴት ከመታተሙ በፊት የተቀረፀውን ዘፈን ትንሽ እንዲፈጥን ታደርገዋለህ፡፡ ቴፕ ሪኮርደር ተበላሽቶ ካሴት እያፈጠነ ሲጫወት ሰምተህ እንደሆነ ድምፁን ይቀይረዋል፡፡ በእርግጥ በጣም አታፈጥነውም፣ በትንሹ ነው፡፡ ያኔ የድምፁ ቅላፄ ይወጣል፡፡ ቀጠን ይላል፡፡ ግን ያን ያህል ጎልቶ የሚጋነን አይደለም፡፡ አንዳንድ ዘፋኞች ካሴት ሲያሳትሙ አያስፈጥኑም፡፡ ነገር ግን አፍጥነው የሚያሳትሙት ዘፋኞችም ቢሆኑ መድረክ ላይ የሚበላሽባቸው በሌላ ምክንያት ነው፡፡ እዚህ አገር፣ የድምፅ ቅላፄ እንደ ቋሚ ነገር ይቆጠራል፡፡ ድምፅ ግን የሚበላሽና የሚሻሻል ነው፡፡
ድምፃዊ ሁልጊዜ መለማመድ አለበት:: አንድ ጊዜ ዘፍነው ላይ ከወጡ በኋላ ችላ ይሉታል፤ አይለማመዱም፣ ራሳቸውን መጠበቅ ይተዋሉ፡፡ ሌላው ችግር ደግሞ አስመስሎ መዝፈን ላይ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ አስመስለህ የምትዘፍነው የራስህን ድምጽ ለማሻሻል እንጂ አላማህ ማስመሰል ብቻ ከሆነ፣ ራስህ ለዘለቄታው ትበላሻለህ፡፡ ውጭ አገር ዘፋኞች ለድምፃቸው ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ መለማመድ መደበኛና የሁልጊዜ ስራቸው ነው፡፡ ራሳቸውን ይጠብቃሉ፡፡ ይማራሉ፡፡
የአዳዲስ ባለተሰጥኦዎች ጉዳይ…
… ከስር የሚመጡ በጣም በጣም ሀይለኛ ልጆች አሉ፡፡ በየቦታው የሚጫወቱ፣ በትያትር ቤት የሚሰሩም ብዙ ጎበዝ ልጆችን አውቃለሁ:: አሁን ከትንሽ ጊዜ በኋላ ትልቅ ለውጥ የሚያመጡ ይመስለኛል፡፡ ዛሬ የተሻሉ ነገሮች ተፈጥረዋል፡፡
ሙዚቀኞች ኢንፎርሜሽን ያገኛሉ፤ የተለያዩ የሙዚቃ አይነቶችን፣ ዘፈኖችን፣ ስልቶችን፣ አሰራሮችን ያውቃሉ፡፡ ድሮ የተወሰኑ ነገሮች ብቻ ነበር የሚገኘው፤ ያውም ከውጭ ካሴት ለሚላክላቸው ጥቂት ሰዎች:: ዛሬ ግን ብዙ አማራጭ አለ፡፡ ከየአቅጣጫው እውቀትና ልምድህን የሚጨምርልህ ነገር በብዛት ታገኛለህ፡፡ እና ለሙዚቃ ትልቅ እድገት የሚመጣ ይመስለኛል፡፡…


Read 2898 times