Saturday, 16 June 2012 12:37

“ኮልድ ፕሌይ” ከቢበር ጋር አንሰራም አሉ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

“ኮልድ ፕሌይ” የተባለው ታዋቂው የእንግሊዝ የሙዚቃ ቡድን ከካናዳዊው የ18 ዓመት ዘፋኝ ጀስቲን ቢበር ጋር ተጣምረው ለመስራት እንደማይፈልጉ “ዘ ሚረር” ጋዜጣ አመለከተ፡፡ የኮልድ ፕሌይ መሪ ድምፃዊ ክሪስ ማርቲን ለጋዜጣው በሰጠው አስተያየት፤ ከታዳጊውና ከመልከመልካሙ ጀስቲን ቢበር ጋር በመስራት የባንዱ አባላት በሽምግልናቸው እንዲሾፍ እንደማይፈልጉ ገልፆ ታዳጊው ያቀረበውን በጋራ የሙዚቃ ቪዲዮ የመስራት ጥያቄ (ግብዣ) እንዳልተቀበሉት ተናግሯል፡፡

“ፕሪንሰስ ኦፍ ቻይና” ዘፈን የተባለውን ዜማ ከሪሃና ጋር መስራታቸውን እንደወደዱት ግን ተናግሯል፡፡ ለ”ኮልድ ፕሌይ” የሙዚቃ ባንድ አምስተኛ አልበም የሆነውን “ማይሎ ዛይሎቶ” ለማስተዋወቅ ዛሬና ነገ በማንችስተር ሲቲ ስታዲየም ደማቅ የሙዚቃ ኮንሰርት የሚቀርብ ሲሆን የመግቢያ ትኬቱ በ90 ደቂቃ ተሸጦ ማለቁ የባንዱን ተወዳጅነት ይጠቁማል ተብሏል፡፡ ኮንሰርቱን 50ሺ ገደማ ተመልካቾች እንደሚታደሙት ይጠበቃል፡፡ ኮልድ ፕሌይ በሚያቀርበው ኮንሰርቱ የባንዱ መሪ ድምፃዊው ክሪስ ማርቲን፤ ሁለቱ ጊታሪስቶች ጋይ ቤሪማንና ጆኒ ቢኪላንድ እንዲሁም ድራመሩ ዊል ሻምፒዮን ይጫወታሉ፡፡ከዓመት በፊት ለገበያ የቀረበው የባንዱ አምስተኛ አልበም በአሜሪካ 1 ሚሊዮን ቅጂዎች ሲሸጡ፤ በእንግሊዝ ደግሞ ከ900ሺ በላይ ቅጂዎች ተሸጠዋል፡፡ የ “ኮልድ ፕሌይ” ቡድን ሰባት የግራሚ አዋርድ የተሸለሙ ሲሆን በመላው ዓለም ከ50 ሚሊዮን በላይ የአልበማቸውን ቅጂዎች ሸጠዋል፡፡

 

 

Read 885 times Last modified on Saturday, 16 June 2012 12:43