Tuesday, 01 October 2019 10:08

በሕዳሴው ግድብ ጉዳይ አለማቀፉ ማህበረሰብ ጣልቃ እንዲገባ የግብፁ ፕሬዚዳንት ጠየቁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

          • ‹‹በአባይ ወንዝ ዙሪያ ከትብብር ውጪ ሌላ አማራጭ የለም›› - ፕ/ር ሳህለ ወርቅ ዘውዴ
          • ‹‹ግድቡ በቀጣይ አመት በከፊል ሃይል ማመንጨት ይጀምራል››

          የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታ አልሲሲ በተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር አለማቀፉ ማህበረሰብ በሕዳሴው ግድብ ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ እንዲያሸማግል ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ፕሮጀክቱ ቀጠናውን ወደ አለመረጋጋት የሚያስገባ ነው ብለዋል፡፡ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው በአባይ ወንዝ ዙሪያ ከትብብር ውጪ ሌላ አማራጭ የለም ሲሉ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር አስገንዝበዋል::
ፕሬዚዳንት አልሲሲ ባቀረቡት የ15 ደቂቃ ንግግራቸው፤ በዋናነት ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለው ግድብ የአገራቸውን ሕልውና አደጋ ላይ የጣለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
‹‹የአባይ ውሃ ለግብጻውያን የህልውና ጉዳይ ነው›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ ግድቡ፤ የአገራቸውን 55.5 ቢሊዮን ኪዩብ ሜትር ውሃ የሚያሳጣ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ባለፉት 8 አመታት ከኢትዮጵያ ጋር የተደረጉ ድርድሮች ውጤት አለማምጣታቸውን የጠቆሙት አልሲሲ፤ ሁኔታው በዚህ የሚቀጥል ከሆነ አካባቢውን ወደ አለመረጋጋት የሚወስድና የአካባቢውንም ልማት በተለይም የግብጽን ልማት አደጋ ውስጥ የሚጥል ነው ብለዋል፡፡
ችግሩ እልባት እንዲያገኝ አለማቀፉ ማህበረሰብ ጣልቃ በመግባት ገንቢ ሚና እንዲጫወት የጠየቁት ፕሬዚዳንቱ፤ በግድቡ ጉዳይ ሶስቱም አገሮች ከመግባባት ላይ እንዲደርሱ አለማቀፍ ማህበረሰብ እንዲያሸማግላቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ግብጽ የሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ መጀመሯን የገለጸው የአገሪቱ ታዋቂ ጋዜጣ “አልሃራም” በበኩሉ፤ የአገሪቱ ባለሥልጣናት የአውሮፓ፣ አረብና አፍሪካ አገራትን ስለ ጉዳዩ የማስረዳት ስራ እየሰሩ ነው ብሏል።
በተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ ላይ ከ50 አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአማርኛ ቋንቋ ንግግር ያደረጉት ፕ/ር ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው የአባይ ወንዝ ለተፋሰሱ አገራት የጋራ ሀብት እንጂ የጥርጣሬና የውድድር ምንጭ ሊሆን አይገባም ብለዋል፡፡
የአባይን ወንዝ ሁሉንም ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ በትብብርና በቅንጅት ለመጠቀም መስራት ይገባል ያሉት ፕሬዚዳንቷ ከትብብር ውጪ ሌላ አማራጭ የለም ብለዋል፡፡  የሱዳን መንግሥት በበኩሉ የግብጽና የኢትዮጵያን የቃላት ውዝግብ ከዳር ሆኖ ከመታዘብ ባለፈ እስካሁን ያለው ነገር የለም፡፡
የግድቡ የሲቪልና ኤሌክትሮሜካኒካል ሥራ በፍጥነት እየተከናወነ እንደሚገኝ የገለፀው የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ፤ ግብጽ ለምታካሂደው የዲፕሎማሲ ዘመቻ አፀፋዊ ዘመቻ እንደሚያካሂድ አስታውቋል፡፡
ግድቡም ያለ ምንም መስተጓጎል ሥራው እየተከናወነ መሆኑን በመግለጽም በቀጣይ አመት (2013) አጋማሽ ሁለቱ ዩኒቶች ሀይል ማመንጨት ይጀምራሉ ተብሏል፡፡  
በአሁኑ ወቅት የዋናው ግድብ የኮንክሪት ሙሌት 80.4 በመቶ መድረሱን፣ የጐን (የኮርቻ) ግድቡ 96 በመቶ የሃይል ማመንጫ ክፍሉ ደግሞ 70 በመቶ መጠናቀቁ ተገልጿል፡፡ በአጠቃላይ የግድቡ ሥራ አፈጻጸም 68.3 በመቶ መድረሱም ታውቋል፡፡

Read 6693 times