Sunday, 26 May 2019 00:00

የህግ ባለሙያ፣ ሥራ ፈጣሪ፣ ለተዘነጉ ወገኖች ተሟጋች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  “--የቀጣዩ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ሴቶች፣ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ለሌሎች የአፍሪካ አገራት በአርአያነት የሚጠቀሱ እንደሚሆኑ ተስፋ አለኝ፡፡ ሌሎች ተጨማሪ ሴቶችን ወደ መሪነት በማምጣት፣ በነገዋ አገራችን ሙስናና ድህነትን መቀነስ እንደምንችል አስባለሁ፡፡--”
              የትነበርሽ ንጉሴ ሞላ


                ራሴን የማስበው የሰው ልጅ ሊያሳካቸው የሚችላቸውን ነገሮች ሁሉ ማሳካት እንደሚችል ሰው አድርጌ ነው፡፡ ለራሴ ወዳስቀመጥኳቸው ማናቸውም አይነት ግቦቼ እንዳልደርስ የሚያግዱኝ፤ ምንም አይነት አጥሮችም ሆኑ ምክንያቶች የሉም ብዬ አምናለሁ፡፡ የተፈጠርነው በቴክኖሎጂና በመረጃ ዘመን ላይ ነውና፣ የእኛ ትውልድ ከቀዳሚዎቹ በተሻለ ዕድለኛ ነው፡፡ ማየት የተሳናት ወጣት ሴት እንደመሆኔ፤ አንድ ሰው በወጣትነቱ፣ በሴትነቱና በአካል ጉዳተኝነቱ ሳቢያ የሚደርስበት መገለል ምን ማለት እንደሆነ ይገባኛል፡፡ እንደ ማህበረሰብም ሆነ እንደ አገር የምናካሂደው ልማት፤ ሴቶችን፤ ወጣቶችን፤ አካል ጉዳተኞችንና በአጠቃላይ መገለልና መድልኦ የደረሰባቸውን ሁሉ ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባቱን ለማረጋገጥ እንድሰራ ያነሳሳኝ፤ የራሴ የሕይወት ተመክሮ ነው፡፡
የተወለድኩት በአማራ ክልል በሚገኘውና በእርሻ የሚተዳደር ማህበረሰብ በሚኖርበት ሳይንት በሚባል አካባቢ ነው፡፡ እስከ አምስት አመቴ ያደግሁት፤ አሁንም ድረስ የኤሌክትሪክ ሃይልና የውሃ አቅርቦት ባልተሟላለት፤ ሴቶች በአስር አመት እድሜያቸው ጋብቻ እንዲመሰርቱ በሚገደዱበት የገጠር መንደር ውስጥ ነበር፡፡ ወላጆቼ ትዳራቸውን አፍርሰው በፍቺ በመለያየታቸው፣ በልጅነቴ የእናቴ ዘመዶች ናቸው ያሳደጉኝ፡፡
የእኔ ሕይወት ወዳልተጠበቀ አቅጣጫ ማምራት የጀመረው የአምስት አመት ልጅ ሳለሁ የአይኔን ብርሃን ሳጣ ነበር፡፡ በወቅቱ በአዲስ አበባ የተደረገልኝ የአይን ህክምና ውጤት አልባ መሆኑን ተከትሎ፤ እናቴ ፍላጐቴን ሊያሟላልኝ ወደሚችለው ሻሸመኔ የአይነ ስውራን ካቶሊክ አዳሪ ትምህርት ቤት አስገባችኝ፡፡ ይህም ለእኔ ፍጹም አዲስ አኗኗር ነበር የሆነብኝ፡፡ ምንም አይነት የስጋ ዝምድና ከሌለን ልጆች ጋር ነው ያደግሁት፡፡ የሚያመሳስለን ነገር ቢኖር፤ ሁላችንም ማየት የተሳነን ሕጻናት መሆናችን ብቻ ነበር፡፡ ትምህርት ቤቱ በአብዛኛው የአየርላንድና የእንግሊዝ ዜግነት ባላቸውና ህይወታቸውን ማየት የተሳናቸውን ሕጻናት ለመንከባከብ በሰጡ መነኩሲቶች ነበር የሚተዳደረው፡፡
ምንም አይነት መድልኦ ሳይደርስብን ነው ያደግነው፡፡ ሁላችንም ማየት የተሳነን እንደመሆናችን፤ አብረን እየተጫወትን፤ አብረን ወደ ትምህርት ቤት እየሄድንና በትምህርታችን ብልጫ ለማግኘት እርስ በርስ እየተወዳደርን ነው ልጅነታችንን ያሳለፍነው:: ትምህርት ቤቱ ጠንካራ የትምህርት መሠረት ያለው ነበር፡፡ ጥሩ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎትን ያገኘሁትና ጠንካራ በራስ የመተማመን ስሜት የገነባሁት፤ በትምህርት ቤቱ በነበረኝ ቆይታ ነው:: የካቶሊክ መነኩሲቶቹ አርአያዎቼ ነበሩ፡፡ ሴቶች ጠንካራና ውጤታማ መሪዎች መሆን እንደሚችሉ የተማርኩት ከእነሱ ነው፡፡ ለሌሎች መኖርና ለሌሎች ደህንነት አስተዋጽኦ ማበርከት ምን ማለት እንደሆነ ያሳወቁኝም እነሱ ናቸው፡፡
ስድስተኛ ክፍልን እንደጨረስኩ፤ መነኩሲቶቹ በውስጤ ያሰረጹብኝን በራስ የመተማመን ስሜት ይዤ ወደ አዲስ አበባ መጣሁ፡፡ ዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመግባትም፣ አካል ጉዳተኛ ካልሆኑ ተማሪዎች ጋር መማርና በአመራርና በማህበራዊ ግልጋሎቶች ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ቀጠልኩ፡፡ የትምህርት ቤቱ የተማሪዎች የምክር አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን ለሦስት ተከታታይ ጊዜያት አገልግያለሁ፡፡ የጸረ - አደንዛዥ እጽና የጸረ - ኤችአይቪ ኤድስ ክበባት ሊቀመንበር በመሆንም ሰርቻለሁ፡፡ በትምህርት ቤቱ የነበረኝ ንቁ ተሳትፎ፤ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብቼ በህግ የመጀመሪያ ድግሪዬን መከታተል ስጀምርም ተጠናክሮ ቀጠለ፡፡ የዩኒቨርሲቲው ፀረ-ኤድስ ንቅናቄ ሊቀመንበርና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በመሆንም አገልግያለሁ፡፡ የሴት ተማሪዎች ማህበር የተሰኘውን የሴቶች ክበብ በማቋቋም መርቻለሁ፡፡
ሕግ ለማጥናት የወሰንኩት፤ አንድም ማህበረሰቡ ለሕግ ሙያ የሚሰጠውን ክብርና ታላቅነት በማየት ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ፤ ለሌሎች ለመቆም ሁሌም ትልቅ ፍላጐት ስለነበረኝና ማስረጃን፤ አመክኖንና ሎጂክን በተመለከተ ጥልቀት ባለው መልኩ ትምህርት መውሰዴ፤ ለምሰራው ሥራ የበለጠ አቅምና ችሎታ ያጐናጽፈኛል ብዬ በማሰብ ነው:: ሕግ መማሬ፤ ሁሉም ሰው መብቶች እንዳሉት እንዳስብ አድርጐኛል፡፡ ሀብታሞች ራሳቸውን በገንዘባቸው መከላከል ይችላሉ፡፡ የተገለሉትና ድምጻቸው የማይሰማላቸው የሚከላከሉበት ሕግና ሕገ - መንግሥት ያስፈልጋቸዋል፡፡ እኔም በማህበረሰቡ ውስጥ የሚገኙ ችግረኞችን መብት ለማስከበር ያለኝን ቁርጠኝነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሳደግ ያዝኩ፡፡
በኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኝነትና ልማት ማዕከል ውስጥ የጀመርኩት ሥራ፣ እጅግ አርኪ ሆነልኝ፡፡ ችግረኞችን በተመለከተ፤ ሁሉም ዜጐች እድሎችን በእኩልነት እንዲጠቀሙ የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሥራት ችያለሁ፡፡ ልማት ሴቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን፤ ወጣቶችን፣ አርብቶ አደሮችን፣ የእስልምና እምነት ተከታዮችንና ሌሎችን ያካተተ እንዲሆን የማስቻል ሥራም አከናውኛለሁ:: በ1998 ዓ.ም ከዩኒቨርሲቲ እንደተመረቅሁ፤ ድርጅቱን በማቋቋም የራሴን ድጋፍ ያደረግሁ ሲሆን፣ የሥልጠናና የቅስቀሳ ኃላፊ በመሆንም ሥራዬን ሳከናውን ቆይቻለሁ፡፡ በ2004 ዓ.ም የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ሆንኩኝ፡፡ በተመረቅኩበት ወቅት በርካታ የሥራ ቅጥር ጥያቄዎች ቀርበውልኝ ነበር፡፡ እኔ ግን፣ በራሴ የሕይወት ተመክሮዎች ላይ ለሚታዩ የተለያዩ ጉዳዮች ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ አዲስ ተቋም በማቋቋምና ቅርጽ በማስያዝ ረገድ የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች መጋፈጥ ነበር የመረጥኩት፡፡ በዚህ መሃል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማህበራዊ አገልግሎት ሁለተኛ ዲግሪዬን ተቀበልኩ፡፡
ማንኛውም አዲስ የሚገነባ ህንጻ፣ ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ መሆን እንዳለበት ለሚያስገድደው የኢትዮጵያ የግንባታ ሕግ፣ የተደራሽነት መመሪያ በማርቀቅና ጉዳዩ ግንዛቤ እንዲፈጠርበት በማድረግ ረገድ በሰራሁት ሥራ ትልቅ ኩራት ይሰማኛል:: አካል ጉዳተኞች በአሁኑ ወቅት ጤናን ጨምሮ በተለያዩ የልማት መስኮች ውስጥ መካተታቸውን በማረጋገጥ እንዲሁም በትግራይ ክልል ያሉ አካል ጉዳተኞችን የኢኮኖሚ አቅም በመገንባት ረገድ ውጤታማ ሥራ ሰርቻለሁ፡፡ ዩኒቨርሲቲው የአካል ጉዳተኝነት ፖሊሲ እንዲያወጣና ፖሊሲውን የሚያስፈጽም ማዕከል እንዲያቋቁም በማድረግም የራሴን አስተዋጽኦ አበርክቻለሁ፡፡ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያወጣውን የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት ተቀብላ እንድታጸድቅ በተደረገው ቅስቀሳ ላይም ንቁ ተሳትፎ አድርጊያለሁ::                                                                                                                                                                                                                                    
በመሰል ንቅናቄዎች ላይ ከምሠራቸው ሥራዎች በተጨማሪ፤ በቀበና አካባቢ ያቋቋምኩትን መዋዕለ ሕጻናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የማስተዳደር ሥራም እሠራለሁ፡፡ ግሩም የሆነ ባልና አስደሳች የሆነች ልጅ አሉኝ፡፡ ሁለቱ ናቸው ለህይወቴ ጣዕም የሚሰጡት፡፡
አካል ጉዳተኛ መሆኔ፣ በተለያዩ መንገዶች ፀጋ ሲሆነኝ ተመልክቻለሁ፡፡ የሚገጥሙኝን በርካታ እንቅፋቶች ማለፍ እንደምችል ቀደም ብዬ ነው ያወቅሁት፡፡ ይሄንንም በተግባር አረጋግጫለሁ:: ስለዚህ በሚገጥሙኝ ጥቃቅን ፈተናዎችና እንቅፋቶች አልደናገጥም፡፡ ለመለወጥ አስቸጋሪ የሚሆነው የሌሎችን ሰዎች አመለካከቶች ነው፡፡ አካል ጉዳተኞች እርዳታ ተቀባዮች እንጂ ለራሳቸው መብት መከበር የሚሠሩና አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ እንዳልሆኑ አድርገው የሚያስቡ ብዙዎች ናቸው:: ይህ ፍጹም የተዛባና መቀየር ያለበት አመለካከት ነው፡፡ ይህን መሰሉን አሉታዊ አመለካከት ለማሸነፍ እንድችል ያገዙኝ ነገሮች፤ ግንዛቤ፣ መንፈሰ ጠንካራነት፣ እምነትና ከሌሎች አካል ጉዳተኞችና መገለል የደረሰባቸው ሰዎች ጋር ትስስር በመፍጠር እርስ በርስ መረዳዳት ናቸው፡፡ የገጠሙኝ ችግሮች በሙሉ የበለጠ አጠንክረውኛል፡፡
ትልቁ ፍላጐቴ፤ አካል ጉዳተኞች ጠንካሮችና ነገሮችን የማሳካት አቅም ያላቸው ዜጐች እንደሆኑ ለማህበረሰቡ ማሳየት ነው፡፡ በችግረኞችና በተገለሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚደርሰው መገለል፤ እኔ በሕይወት ሳለሁ አብቅቶ እንደማይ ተስፋ አለኝ፡፡ ይህ እንደሚሆን የሚጠቁሙ ምልክቶችን ማየት ስጀምር፤ እንቅስቃሴዬን ሰፋ በማድረግ፣ ለሁሉም የሰው ልጆች መብቶች መከበር፣ በአገራዊና በአህጉራዊ ደረጃ ለመሥራት እፈልጋለሁ፡፡ ሁሉንም የሰው ልጆች ያካተተች ዓለም ለመፍጠር በመትጋት እንደምታወስ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ለእኔ ታላቋ አርአያዬ እማሆይ ቴሬሳ ናቸው:: የካቶሊክ እምነት ተከታይ እንደመሆኔ፤ ህይወቴን መምራት የምፈልገው ሌሎችን በማገልገል ነው፡፡ ሕይወት ከሌሎች የመውሰድና የመጠቀም ጉዳይ ብቻ አይደለችም፡፡ መልሶ የመስጠትና የሌሎችን ሕይወት በሚለውጡ ነገሮች ላይ አስተዋጽኦ የማበርከትም ጭምር እንጂ፡፡ ለሌሎች አርአያ መሆን ከቻሉና በእድሜ ከሚበልጡኝ ምርጥ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ጋር መገናኘት በመቻሌ፤ እራሴን እንደ እድለኛ ነው የምቆጥረው፡፡ በሕይወት ዘመኔ ያገኘኋቸው ከአስቸጋሪ ሁኔታዎች ተነስተው ከኔ የበለጠ ውጤታማ ሥራ የሰሩ በርካታ ወንዶችና ሴቶች፣ የመነቃቃት ምንጭ ሆነውኛል፡፡ ታሪካቸው ጐልቶ ባይወጣና በአደባባይ ባይዘመርላቸውም፣ ባገኘኋቸው ቁጥር ሁሉ በውስጤ ትልቅ ኃይል ያሰርጹብኛል፡፡
ወደፊት አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ኢትዮጵያውያን ሴቶች የመሪነት ቦታ ላይ ደርሰው እንደማይ ተስፋ አለኝ፡፡ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ከባድ ፈተናዎች አሉባቸው፡፡ በመሪነት ረገድ ትልቅ አቅም ስላላቸው እነዚህ ፈተናዎች፣ የበለጠ ጠንካራ ያደርጓቸዋል፡፡ ልጆቻቸውን በማሳደግ፣ በቤተሰብ ውስጥ ሰላምና ፍትሃዊነት እንዲሰፍንና ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርጉ መፍትሔዎችን በማመንጨት የታወቁ ናቸው፡፡ የቀጣዩ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ሴቶች፣ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ለሌሎች የአፍሪካ አገራት በአርአያነት የሚጠቀሱ እንደሚሆኑ ተስፋ አለኝ፡፡ ሌሎች ተጨማሪ ሴቶችን ወደ መሪነት በማምጣት፣ በነገዋ አገራችን ሙስናና ድህነትን መቀነስ እንደምንችል አስባለሁ፡፡
ኢትዮጵያውያን ልጃገረዶችና ወጣት ሴቶች፣ ከእኔ የሕይወት ተመክሮ መማር ትችላላችሁ:: የሚገጥሟችሁ ፈተናዎች የበለጠ ጠንክራችሁ እንድትሰሩና ብርታት እንድትላበሱ ያደርጓችኋል:: ፈተና የሚገጥማችሁ ትክክለኛ ማንነታችሁን እንድታረጋግጡበት በመሆኑ፣ ፈተና ባጋጠማችሁ ጊዜ ሁሉ እጅ አትስጡ፡፡ ሌላው ነገር ደግሞ፤ ገንዘባችሁን፣ ክህሎታችሁን፣ ሙያችሁን፣ ጊዜያችሁን፣ ጉልበታችሁን በአጠቃላይ ራሳችሁን ለሌሎች አሳልፋችሁ እንድታጋሩ የሚጋብዟችሁ እድሎች ሲፈጠሩ ወደ ኋላ አትበሉ፡፡ ምክንያቱም ይህን ማድረጋችሁ፣ የበለጠ በኃይል እንድትሞሉ ዕድል ይፈጥርላችኋል፡፡ ልብ በሉ! ይህን ካላደረጋችሁ፣ አለኝ የምትሉት ነገር ሁሉ ከናንተው ጋር ተቀብሮ ይቀራል፡፡ በሃይልና በመንፈስ ራሳችሁን መልሳችሁ የምትሞሉበት ዕድልም አታገኙም፡፡  

Read 3583 times