Saturday, 18 May 2019 00:00

ሥራ ፈጣሪ፣ አነቃቂ ዲስኩር አቅራቢ፣ የሚዲያ ሥራ አስፈፃሚ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 አባቴ ህልምን መተለም አስተምሮኛል:: “ትላልቅ ነገሮችን መስራት እችላለሁ!” የሚል እምነት እንዲያድርብኝ የሚያስችለኝን ልበ ሙሉነት ያስታጠቀኝ እሱ ነው፡፡ ይሄ ለእኔ ታላቅ ስጦታ ነው:: በእርግጥ ይሄን ታላቅ ስጦታ እንዴት መጠቀም እንደምችል ለማወቅ የተወሰነ ጊዜ ፈጅቶብኛል:: ወጣት ሳለሁ፣ ጥሩም ይሁን መጥፎ ሁሉን ነገር የመቃወምና የመፈታተን አመል ነበረብኝ፡፡ በዕድሜ ስበስል ግን፣ ነገሩ ከሰዎች እንደሚያራርቀኝ እየተገነዘብኩ በመምጣቴ ባህሪዬን አስተካከልኩ፡፡ 29 ዓመት ገደማ እስኪሆነኝ ድረስ፣ ከራሴ ማንነት ጋር ሰላም ለመፍጠር የቻልኩ አይመስለኝም:: ይሄኔ ነው ስለ ራሴና ስለ ህይወት ጉዞዬ መፈተሽ የጀመርኩት፡፡ “ለመሆኑ ምን ያል አበረከትኩ?”፣ “እንዴትስ ነው ሰዎች ላይ ተፅዕኖ ያሳደርኩት?”፣ እና “ከመነሻውስ የመኖሬ ፋይዳ ምንድነው”፣ የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ በንቃት ማሰብ ያዝኩ፡፡ እነዚህ ጉዳዮች አሁንም ድረስ ለራሴ የማቀርባቸው ጥያቄዎች ናቸው፡፡ በእርግጥም ማንነትን ለሰዎች ከማረጋገጥ ይልቅ፣ ራሴን ሆኜ ለመኖር መቻል ሺ ጊዜ የተሻለ ነው፡፡
እናቴ አሰፋሽ ካሳሁን ብርቱና ለጋስ ሴት ናት:: አምስት ልጆቿን ጨምሮ (እኔ የበኩር ልጅ ነኝ) ከዘመድ አዝማዱ ጋር 16 የሚደርሰውን የቤተሰቡን አባላት ቀጥ አድርጋ ታስተዳድር ነበር፡፡ ቤት ያፈራውን ተካፍሎ መብላትን፣ ከሰዎች ጋር በደስታ መኖርንና ህይወትን ቀለል አድርጎ መመልከት የተማርኩት በለጋ ዕድሜዬ ነው፡፡ ከቤታችን ጠፍቶ የማያውቀውን ሳቅና ጨዋታ እያጣጣምኩ ነበር የልጅነት እድሜዬን ያሳለፍኩት፡፡
እናቴ መምህርት ነበረች፡፡ በ13 ዓመቴ አባቴ ከሞተ በኋላ፣ ያንን ሁሉ ቤተሰብ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ደሞዟ ቀጥ አድርጋ አስተዳድራለች፡፡ ለጊዜው ልንቸገር እንችላለን፡፡ ዋናው ነገር ግን በውስጣችን ያለውን እምነትና የሚገጥመንን መልካም እድሎች እንዴት እንደምንጠቀምባቸው ማወቅ ነው፤ ይሄንንም የተማርኩት ከእናቴ ነበር፡፡
አባቴ በእኔ ህይወት ውስጥ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ መጀመሪያ በዕደማርያም ላብራቶሪ ትምህርት ቤት፣ ከዚያም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተምሯል፡፡ በኋላ ላይ ከጓደኞቹ ጋር “ዓለም የህዝብ ግንኙነት” የተባለ ድርጅት አቋቋመ፡፡ አባቴ በአዕምሮ ብሩህነትም ሆነ በቁንጅና ማንም ጫፌ ላይ እንደማይደርስና የተፈጠርኩትም ታላላቅ ነገሮችን ለማከናወን እንደሆነ እየነገረኝ ነበር ያደግሁትና፣ ራሴን ሰማይ አሳክዬ እንዳስብ አድርጎኛል፡፡ የትምህርት ውጤቴ ጥሩ ይሁን እንጂ፣ በትምህርት ቤት ረባሽ መሆኔ አባቴን አያሳስበውም ነበር፡፡ እንደውም ለረባሽነቴ ሰበብ ይፈጥርልኝ ነበር:: “ሌላው ተማሪ ሙሉ ቀን የሚፈጅበትን ትምህርት፣ የኔ ልጅ በግማሽ ቀን ፉት ትለዋለች፡፡ ከዚያ ምን ታድርግ? ይሰለቻታል፤ ለዚህ ነው ረባሽ የሆነችው” እያለ እናቴን ለማሳመን ሲሞክር አስታውሳለሁ፤ እኔም ታዲያ ያንን አምኜ እቀበል ነበር፡፡ በወ.ወ.ከ.ማ የሚዘጋጀውን የተማሪዎች ክርክር እሱ በሊቀ መንበርነት ሊመራ ሲሄድ፣ እኔንም ይወስደኝና ክርክሩን እንድከታተል ያደርጋል:: ዝግጅቱ ተጠናቆ ወደ ቤታችን ስንመለስ ደግሞ፣ በክርክሩ የተለያዩ ሃሳቦችን ይዘው የተሳተፉትን ሁለቱንም ወገኖች ተከራክሬ የምረታበትን ዘዴና ብልሃት ያስተምረኝ ነበር፡፡ አባቴ በልጅነቴ በውስጤ ያሳደረብኝ ልበ-ሙሉነት አሁንም ድረስ አብሮኝ አለ::
አባቴ በ42 ዓመቱ በመኪና አደጋ ህይወቱ ሲያልፍ፣ ሰማይ የተደፋብኝ መሰለኝ፡። መላ ቤተሰቡን የማስተዳደር ኃላፊነት ጫንቃዋ ላይ የወደቀባት እናቴ፤ የምታፈናፍን አልነበረችም:: ከጓደኞቼ ጋር ወጥቼ ሻይ ቡና እንድል እንኳን አትፈቅድልኝም ነበር፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ካጠናቀቀቅሁ በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብገባም አልተሳካልኝም፡፡ ከቤቴ ወጥቼ በዩኒቨርሲቲ መኖሪያ ቤት ስኖር የመጀመሪያዬ ስለነበር፣ አዲሱን ነፃነቴን ሳጣጥም፣ ትምህርቱን ችላ አልኩና በፈተና ወደቅሁ:: እንደ አባቴ ሃሳብ ቢሆን ኖሮ፣ ወደ አሜሪካ ሄጄ ነበር የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን የምከታተለው:: ይሄ እንደማይሳካ ሲገባኝ፣ ማስቸገር ጀመርኩ፡፡ ይሄኔ ለሩሲያ ነፃ የትምህርት እድል እንዳመለክት ቤተሰቤ ወሰነ፡፡ በወቅቱ ውሳኔውን ተቃውሜ ነበር፤ የሚሰማኝ አላገኘሁም እንጂ፡፡
የሆነው ሆኖ፣ የትምህርት እድሉን አገኘሁና ወደ ሩሲያ ሚኒክስ ተጓዝኩ፡፡ እዚያ የገጠመኝ ነገር ጨርሶ ያልጠበቅሁት ነበር፡፡ ህዝቡንና ባህሉን ወደድኩት፤ ቋንቋውና ሥነ ፅሑፉም ማረከኝ፡፡ ከቤተሰቤ ጋር የምገናኘው በደብዳቤ ብቻ ነበር፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሌላ ሰው ሆንኩ፤ በፍጥነትም በአእምሮ በሰልኩ፡፡ ከአራት ዓመት በኋላ ግን ያላሰብኩት ችግር ተፈጠረ፡፡ እዚያው የተቋቋመ የኢትዮጵያ ወጣቶች ማኅበር፣ ‹ፀረ-አብዮተኛ› ብሎ ወነጀለኝ፡፡ ‹እግሬ አውጪኝ› ብዬ ከሩሲያ በማምለጥ በፖላንድ በኩል ጀርመን ገባሁ፡፡ ሩሲያና ኢትዮጵያ በወዳጅነት የከነፉበት ወቅት ስለነበር፣ መዘዙ ለቤተሰቦቼም እንዳይተርፍ ሰግቼ ደብዳቤ መፃፃፉንም ተውኩት:: ጀርመን ውስጥ የጠበቀኝ የስደት ኑሮ የከፋ ነበር:: በማትፈልገኝ አገር ውስጥ፣ ወይ አልኖርኩ ወይ አልሞትኩ በሚያሰኝ እንጥልጥል ሕይወት ውስጥ፣ ሞራል የሚያላሽቅ አስጨናቂ ጊዜ አሳለፍኩ፡፡ ጥሎ አይጥልም እንዲሉ፣ ደጋግ ሰዎች አላጣሁም፡፡ ያንን ክፉ ጊዜ ያሳለፍኩት በእነሱ እርዳታ ነበር፡፡ የማታ ማታም በአሜሪካ ጥገኝነት አገኘሁ፡፡ አሜሪካ ሄጄም ቢሆን፣ ደጋግ ሰዎች ላይ ነበር የወደቅሁት፡፡ በእነሱ ድጋፍ፣ በማውንት ሆልዩክ ኮሌጅ ነፃ የትምህርት ዕድል አገኘሁ፡፡ በኮሌጁ ትምህርቴን ተከታትዬ፣ በ27 ዓመቴ በዓለም አቀፍ ግንኙነት የመጀመሪያ ዲግሪዬን አገኘሁና፣ የአባቴን ምኞት ለማሳካት በቃሁ፡፡
ከዚያም ወደ ቦስተን ሄጄ ሥራ ጀመርኩ፡፡ ታናናሾቼንና እናቴን ወደ አሜሪካ አምጥቻቸው ስለነበር፣ እነሱን ለመርዳት በሁለት ቦታዎች መሥራት ነበረብኝ፡፡ ከሰኞ እስከ አርብ በስደተኞች ማዕከል ስሰራ፣ ቅዳሜና እሁድን ደግሞ በቦስተን ሎገን አውሮፕላን ማረፊያ፣ የስጦታ መደብር አስተዳድር ነበር፡፡ በኋላ ላይ ወደ ዋሺንግተን ዲሲ ሄጄ፣ የአባቴ ወዳጅ አቶ ፀሐይ ተፈራ በሚመሩት “የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ልማት ምክር ቤት” ውስጥ መስራት ጀመርከ፡፡
በ1983 ዓ.ም የደርግ ወታደራዊ መንግስት ከስልጣን ሲገረሰስ፣ በአለቃዬ በአቶ ፀሐይ አማካኝነት ዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ በአምባሳደር ብርሃነ ገ/ክርስቶስ፣ በፕሬስ አማካሪነት ተቀጠርኩ፡፡ በኤምባሲው ስቀጠር፣ ስለ ፕሬስ አማካሪነት የማውቀው ነገር አልነበረም:: ጥልቅ የሥራ ስሜት የነበራቸው የሥራ ባልደረቦቼ ምስጋና ይግባቸውና፣ በእነሱ ድጋፍ ስራ ላይ ሆኜ ሙያውን ተማርኩት፡፡ ከአዲሱ መንግስት ጋር ፖለቲካዊ ግንኙነት ባይኖረኝም፣ ራሱን ችሎ በሁለት እግሩ የመቆም ዕድል እንዲያገኝ ፍላጎት ነበረኝ፡፡ በኤምባሲው ለስድስት ዓመት ካገለገልኩ በኋላ፣ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ የመስራት ፍላጎቴም ተሳካ፡፡
በቢቢሲ ሞዴል ከመንግስት ጣልቃ ገብነት ነፃ በሆነ መልኩ እንዲሰራ እንደ አዲስ የተቋቋመውን የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅትን በኃላፊነት እንድመራ ተሾምኩ፡፡ የሰራተኞቼን ቁጥር አሳንሼ ባስብም፣ 1500 ሰራተኞች እንደነበሩት ተረዳሁ፤ በዚያ ላይ ፖለቲካ ምን ያህል የስራ ድባቡን እንደሚነው በቅጡ አልመዘንኩትምና እንደ ቀላል ነበር የቆጠርኩት፡፡ ከዚያ ይልቅ፣ አዳዲስ ፕሮግራሞን የመጀመር ጉጉቴ አይሎ ነበርና፡፡ ተወዳጅ የምርመራ ጋዜጠኝነት ፕሮግራም በኢቴቪ ከመጀመራችንም በተጨማሪ፣ ቲቪ አፍሪካ የተሰኘ ፊልሞችን የሚያሰራጭ ሁለተኛ ቻናል ከፍተናል፡፡ በኔ በኩል፣ ህብረተሰቡ ኢቴቪን ወዶትና ተማርኮበት እንዲመለከተው እንጂ፣ አማራጭ የቴሌቪዥን ሥርጭት ስላጣ ብቻ እንዲያየው አልፈልግም ነበር:: ጋዜጠኞች፣ አዳዲሶቹን ፕሮግራሞች ማራኪ ለማድረግ፣ እጥፍ ድርብ ትጋት አሳይተዋል፡፡ ትጋታቸውም ታዲያ መና አልቀረም፡፡ ህብረተሰቡ ፕሮግራሞቹን ወደዳቸው፡፡ በድርጅቱ የአራት ዓመታት ቆይታዬ፣ ግሩም የባለሙያዎች ቡድን ድጋፍ አልተለየኝም፡፡
ድርጅቱን በመራሁባቸው የመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት (1990 እስከ 1992 ዓ.ም)፣ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ዙሪያ የመንግስት ቃል አቀባይ በመሆን አገልግያለሁ፡፡ ጦርነቱ የፈነዳው ከአሜሪካ ከመጣሁ ከወር በኋላ ነበር፡፡ አገሪቱ በጦርነት ላይ በነበረችበት በዚያ ቀውጢ ሰዓት፣ የተሻለ አስተዋፅኦ በማበረክትበት ዘርፍ የድርሻዬን የመወጣት ኃላፊነት አለብኝ የሚል እምነት ስለነበረኝ፣ ለአገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች፣ ቀንና ሌሊት ሳልል በየእለቱ፣ እስከ አራት ጊዜ በተደጋጋሚ ስለ ጦርነቱ ሁኔታ መግለጫ እሰጥ ነበር፡።
ከኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ስወጣ፣ ምንም የመስራት እቅድ አልነበረኝም፡፡ በዚህ ሰዓት ነበር፣ መዓዛ አሸናፊ መንግስቱ። የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅትን ለመመስረት እንዳግትዛት የጠየቀችኝ፡፡ የድርጅቱ አላማ፣ የሴቶችን ድምፅ በማጉላት መብታቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡ ድርጅቱን ለማቋቋምና መነሻ የገንዘብ ድጋፍ ለማሰባሰብ፣ ከዚያም ድርጅቱን የምትመራ ዋና ዳይሬክተር ለመቅጠር አመት ያህል ፈጅቶብኛል፡፡ በመቀጠል የሰራሁት፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የስነ ፆታ ክፍል ውስጥ ነበር:: ከዚያም ከኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ጋር ዩኒሴፍ በቀረፀው ፕሮጀክት ላይ በትብብር ሰርቻለሁ፡፡ የልጃገረዶች መድረክ የማቋቋም ዓላማ ያነገበው ይሄ ፕሮጀክት፣ በጣም የማረከኝ ስራ ነበር ማለት እችላለሁ፡፡ በ1994 ዓ.ም የተከሰተውን ረሃብ ለመቋቋም፣ “አንድ ብር ለአንድ ወገን” የተሰኘውን የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘመቻ፣ ከጓደኞቼ ጋር የመራሁትም በዚሁ ጊዜ ነበር፡፡ በበጎ ፈቃደኞች የተጠነሰሰው ይሄው ዘመቻ፣ ከትንሽ ተነስቶ ትልቅ ደረጃ ላይ ለመድረስ የቻለው በህዝቡ የበጎ ፍቃድ ተሳትፎ ነበር፡፡ ያልተሳተፈበት ዜጋ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ህፃናትን፣ የንግድ ሰዎችን፣ የመንግስት ባለስልጣትን፣ ዝነኞችንና የዩኒቨርሲቲ ምሁራንን እንዲሁም የወታደሩን ክፍል ሳይቀር ባሳተፈው ፕሮጀክት። 14 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል፡፡ በወቅቱ ለወገኑ ለመድረስ የድጋፍ እጁን የዘረጋው የሰው ብዛት ሲታይ፣ ሁለመናን በስሜት የሚያጥለቀልቅ ኃይል ነበረው፡፡
ከዚህ በኋላ በመላው አፍሪካ የአመራር ሰጪነት ፕሮግራም ከሚቀርፁ አምስት ሴቶች አንዷ እንድሆን ከብሪቲሽ ካውንስል ሃሳብ ቀረበልኝ፡፡ ይህን በመቀበል ፕሮግራም በመቅረፅ ብቻ ሳይሆን፣ ተግባራዊ የሚያደርጉ ሰዎችንም በማሰልጠን ለአራት ዓመታት ሰራሁ፤ ከእውቀታችንና ከተሞክሯችን ጋር አብሮም እያደገ የመጣ መመሪያ አወጣን፡፡ ይሄ አጋጣሚ በአንድ በኩል አፍሪካን በቅጡ እንዳውቃት እድል የፈጠረልኝ ሲሆን፤ በሌላ በኩልም ደግሞ ፕሮግራሞችን ለማቀድና ለመቅረፅ የሚያስችል ልበ-ሙሉነትን እንዳዳብር አስችሎኛል፡፡
‹ኢመርጅ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር› የተባለ የራሴን አማካሪ ድርጅት የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ የመሰረትኩ ሲሆን፣ በቅርቡ ደግሞ የልጃገረዶችን አቅም የሚያጎለብት “የኛ” የተሰኘ ድንቅ ፕሮጀክት ላይ መስራት ጀምረናል፡፡ ኢመርጅን እንደገና በአዲስ መልኩ የማቋቋም ዕድሉ ቢሰጠኝ፣ የምክር አገልግሎት ተቋም ከማድረግ ይልቅ፤ በአመራር፣ በሥነ ፆታና በተግባቦት ዙሪያ ድንቅ ውይይቶች የሚያብቡበት፣ እንዲሁም ለትግበራ የሚመቹ አዳዲስ ሃሳቦች የሚፈልቁበት የልህቀት ማዕከል ነበር የማደርገው፡፡ በአዲስ አበባ እቴጌ ጣይቱ ብጡልን ሃውልት ለማሳነፅና የራሴን የቴሌቪዥን ጣቢያ ለመጀመር አልማለሁ፡፡ የሴቶች ኮሌጅ የመክፈት ህልምም አለኝ፡፡
ለሥራ የሚገፋፋኝ ኃይል የሚመነጨው፣ “እዚህ ምድር ላይ ያለሁት ለዓላማ ነው” ከሚለው እምነቴ ነው፡፡ ይህ እምነቴ “የሚጠበቅብኝን ያህል አልሰራሁም” የሚል ሃሳብ ሽው ሲልብኝ፤ አንዳንዴ የመረበሽና ያለመረጋጋት ስሜት ይፈጥርብኛል:: ይሄም ሆኖ ግን ስሰራ አቅሜን ሁሌ አንጠፍጥፌ እንደምሰራ ስለማውቅ፣ በምሰራው ስራ እኮራለሁ:: ሁሌም ለራሴ ታማኝ ነኝና በምሰራው ሥራ ላይም እምነት አለኝ፡፡
ኢትዮጵያ፣ ሰዎች ሁሉ ያሻቸውን ህልም መተለም የሚችሉባት አገር እንድትሆን እመኛለሁ፡፡ አሜሪካ ታላቅ አገር ለመሆን የበቃችው፣ ሰዎች ያሻቸውን ማለም የሚችሉባት አገር ስለሆነች ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ኢትዮጵያ፣ ብቃትና አቅም እንዲሁም የማለም ችሎታ የሚለመልሙባትና የሚከበሩባት አገር እንድትሆን እሻለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ሴቶች እርስ በርስ እንዲደጋገፉና “አንቺ ሲሳካልሽ እኔም ይሳካልኛል፣ አንቹ ስትደምቂ እኔም እደምቃለሁ” የሚል ባህል እንዲኖራቸው እመኛለሁ፡፡
ለልጃገረዶች በራሳችሁ ላይ እምነት ይኑራችሁ፤ ራሳችሁንም አድንቁ፤ የምትሹትን ነገርም እንደሚገባችሁ እመኑ እላለሁ፡፡ መሆን የምትሹትን ሁሉ መሆን ትችላላችሁ፡፡ ለሌሎች ሰዎች ወሬም እምብዛም አትጨነቁ፣ ይልቁንም ከራሳችሁ ጋር ለምታደርጉት ውይይት ትኩረት ስጡ፡፡ ጥላችሁ የምትሄዱት የእግራችሁ አሻራ፣ ለሌሎች በር የሚከፍትና ጥርት ብሎና ደምቆ የሚታይ መሆኑንም እርግጠኞች ሁኑ፡፡     
ምንጭ፡- (የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት በመስከረም 2007 ዓ.ም “ተምሳሌት” በሚል ርዕስ ካሳተመውና የስኬታማ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ታሪክ ከሚተርከው መጽሐፍ የተወሰደ)

Read 2034 times Last modified on Monday, 20 May 2019 10:48