Saturday, 20 April 2019 14:04

‹ሳያውቁ በስህተት› እና ‹አውቀውም በሽንፈት›

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)


           “the best is yet to be” ይላል ቤን እዝራ።
‹እድሜ ይስጠን እንጂ፣ ዘመኑ የበጎ ነው። ገና እያበበ እየደመቀ ይሄዳል› የሚል መንፈስ የያዘ ነው እንበል። ‹ለውጥ ሁሉ ለበጎ ነው› እንደማለት።
‹ችግር ካለም፣ ለክፉ አይሰጥም። ሳያውቁ በጥቃቅን ስህተት፣ በጊዜያዊ ዝንፈትና ድክመት ሳቢያ የሚፈጠር ችግር፣ ሊታረም ይችላል። ዘመኑ የበጎ ነውና› የሚል ይሆናል - መልዕክቱ።
በእርግጥም ካለማወቅ፣ ለጸጸት የሚዳርግ ስህተትን ከአንድ የፀጋዬ ገብረመድህን ግጥም እናያለን።
በገዛ ልሳኔ፣ ያንጀቴን ማነቄ
ወይ አለማወቅሽ፣ ወይ አለማወቄ
ነገር ግን፣ ከዚህም የከበደ ፈተና እንዳለ ባለቅኔው ፀጋዬ፣ በድንቅ ግጥሞቹ አንጥሮ፣ አጥርቶና አጉልቶ አሳይቷል - ‹ደሞ መሸ፣ አምባ ልውጣ› የተሰኘውን አስገራሚ ግጥም አንብቡ።
 “the worst is yet to come” ይላል አቤል ተስፋዬ።
‹ከመጥፊያዬ ጋር መግጠሜ መች ጠፋኝ! መለየትም ሞት ሆኖብኝ፣ እድሜዬና እድሜዋ ማጠሩ ነው› የሚል መልዕክት አለው። ‹መላም የለው!› እንደማለት።
ለውጥ ካለ፣ ከድጡ ወደ ማጡ፣…. እንደገና ሌላ ለውጥ ከመጣም፣ ከማጡ ወደ ረመጡ እንደሚሆን እርግጠኛ ነው። መጥፊያችንን መታቀፍ ክፉ ልማድ፣ አይምሬ አመል እንደሆነ ያስጠነቅቃል - (ከዘመኑ የዘረኝነት በሽታ ጋር ይመሳሰላል)።
‹አይጣል ነው› ብለን ለአፀያፊ የጥፋት በሽታ እጅ መስጠት፣ ለወራዳ የውድቀት ቁልቁለት መሸነፍ አለብን? ከተሸነፍን አሳፋሪ ነው።  
ባለማወቅም በስህተትም የሚከሰቱ ችግሮችና የሚፈፀሙ ጥፋቶች፣ ሁሌም ይኖራሉ። የጉዳታቸው መጠን ቢለያይም እንኳ፣ እንዳይደገሙ ማስተካከል፣ እንዳይለመዱም ማቅናትና ማፅናት አያቅትም። እውነትን አክብረው፣ ለማወቅና ለመስራት ከተጉ፣ ሕይወትን የሚያለመልም፣ ዘመኑን የሚያሳምር ውጤት ይገኛልና።
‹ሳያውቁ መሳሳት›፣…. አንዳንዴ፣ እንደ ‹ችግር› የማይቆጠርበትና ጉዳትም የማያመጣበት ጊዜ መኖሩንም አትርሱ። አዋቂና ጥበበኛ ሆኖ የሚወለድ ሰው የለም። በዚያ ላይ እውቀትና ብልሃት፣…. እያንዳንዱን ነገር በዝርዝር፣ ሁሉንም ነገር በጥቅል፣ በልዩ ምትሃት፣ በአንዳች ቅፅበት አይቶ፣ በአንዳች እፍታ አውቆ መጨረስ ማለት አይደለም።
እውነትን ፅኑ መሰረት አድርጎ፣ የአእምሮን ብርሃን ይዞ፣ የእውቀትን መንገድ ተከትሎ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ፣ ከእርከን ወደ እርከን እየደረጀ ወደ ከፍታ የሚወጣ ድንቅ ጉዞ ነው፣ እውቀትና ብልሃት። የሰው የሕልውና ክብርና የሕይወት ጣዕም፣ የዚህ ጉዞ ውጤት ነው። በዚህ መሃል፣ በየጊዜውና በየአጋጣሚው የሚከሰቱ ስህተቶች አይኖሩም ማለት አይደለም። ነገር ግን፣ አንዳንዶቹ በተጨማሪው እውቀትና ትጋት የሚታረሙ ናቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ እንደችግርም አይቆጠሩም - እንዲያውም ፈገግ የሚያሰኙ ሊሆኑ ይችላሉ።
When I am grown to man’s eastate
Is small letter hall be very proud and great
And tell the other girls and boys
Not to meddle with my toys.
አድጎ፣ ትልቅ ሆኖ፣ ‹ድንቅ ሰው› ወደሚያስብል ማዕረግ ሲበቃ ለማየት የሚመኝ ልጅ፣ ምኞቱ ሲሞላ፣ ለጥቃቅን የመጫወቻ ቁሳቁስና ለአሻንጉሊት ደንታ እንደማይኖረው ገና አለማወቁ ፈገግ ያስብላል እንጂ አያሳስብም።
የምር አሳሳቢ ችግር የሚፈጠረው፣ ከእድሜ ጋር እውቀቱ ያላደገ እንደሆነ ነው። በእድሜ እየገፋ፣ የአዋቂ ሕፃን መሆን ካማረው ነው - ጥፋቱ። ‹ዘመኑ የመረጃ፣ የእውቀትና የነፃነት ነው› ብሎ እየተናገረ፣ እንደድሮው ለእውነተኛ መረጃም ሆነ ለማስረጃ ደንታ ቢስ ከሆነ ነው - ችግሩ። ከዚህም አልፎ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየለየለት ከእውነት ጋር ተጣልቶ፣ ውሸትንና አሉቧልታን እንደመተማመኛ ታጥቆ፣ የመበሻሸቅና የመሳደብ፣ የመወነጃጀልና የዛቻ ውድድር ውስጥ መግባትን እንደ ብልጠት ሲቆጥር ነው - ክፋቱ። ጭፍንነትና ጥላቻን መስበክ፣ መጠፋፋትንና እልቂትን መቀስቀስ፣ የእለት ስራ እስኪሆንባቸው ድረስ ቁልቁል የሚወርዱም እያየን ነው።
ይሄ፣ “ባለማወቅና ከስህተት” ሳቢያ የሚመጣ ችግር አይደለም። “የመጣው ይምጣ” ከሚል ጭፍንነት ጋር፡ “የባሰውም እየመጣ”…የዘወትሩን ክፉ አመል የሙጢኝ ይዞ ለመቀጠል የመንደፋደፍ በሽታ ነው፡፡ አፀያፊው የዘረኝነት ቅስቀሳ አመል ሆኖበት፣ ዘግናኝ ጥፋት በየቦታው ሲፈፀም እያየም፣ በማግስቱ እንደ ትናንቱ ዘረኝነትን ያቦካል፡፡
ይሄ “የአዋቂ” ጭፍንነት ነው፡፡ ለክፉ አመል የመሸነፍ ውርደት ነው - ከክፋት ጋር ተቆራኝቷልና እያወቁ አለቁ የሚያሰኝ፡፡
“አለማወቅና መሳሳት” ግን፤ ከዚህ በእጅጉ ይለያል፡፡ ሌሎቹን ትተን ሁለት ስንኞችን ብቻ ከቤን እዝራ ወስደን እንመልከት፡፡  
Grow old along with me
The best is yet to be.
“ከእድሜ ጋር፤ ዘመኑ እያበበ፣ ሕይወት እየለመለመ ይሄዳል” የሚል መልዕክት የሚያስተላልፍ ቢሆን፣ ስህተቱ ምኑ ላይ ነው? በእርግጥም፣ የሰው ተፈጥሮ፣ በእድሜ እያደገ በሰብዕና እየከበረ ሕይወቱን ቢያሳምር ተገቢ ነው፡፡ ጊዜና እድሜ፣ በራሳቸው ጊዜና መንገድ፣ መጪውን ዘመን አሳምረው ያደምቃሉ ማለት ግን አይደለም፡፡ አለበለዚያማ “ጊዜ የጣለው፤ ጊዜ ያነሳው!” ከሚል ኋላቀር አስተሳሰብ ጋር፤
እጃችንን አጣጥፈን፣ አበባ ዘመን እንዲመጣ የምንጠብቅ ከሆነ፣ በስህተትና በከንቱ እንወድቃለን፡፡
ከሁሉም በፊት፣ ከዚህ አይነት ስህተት ለመዳን፣ “የአዋቂ ህፃን” አለመሆን ይቀድማል፡፡ በጥቅሉ መልካምን ፈልገን፣ በደፈናው መጓዝን ተመኝተን፣ …ዝርዝሩ ግን፣ እዚያው የህፃን መጫወቻ ላይ ብቻ ቆሞ ከመቅረት ያለፈና የላቀ አላማና ዝርዝር ግብ ከሌለን፣ ገና ከአላዋቂነት ፈቀቅ አላልንም፡፡ “ከየት ወዴት መሄድ እንደምንመኝ፣ ገና አልተገነዘብንም፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፡፡ በየት በኩልና እንዴት፣ መቼ እና በምን ያህል ጥረት” የሚሉ ጥያቄዎችንም ጭምር አሰላስለን፣ አስተማማኝ ብቃት ካልገነባን፣ የሚያዋጣ ዘዴና መንገድ ካልቀየስን፣ በውጤታማ ጥረት እየተጋን የምንጓዝበትን ብርታት ካላዘጋጀን…ምኞታችን ሁሉ ከንቱ ይሆናል “ንፋስን እንደመጨበጥ” ተብሎ የለ!
መልካም ምኞት፣ ጥሩ ነው፡፡ መልካም ጅምር ነው፡፡ ነገር ግን ምኞታችን ከየት ወዴት እንደሆነ ሳናውቅ፣ መቼና እንዴት ወደ ስኬት እንደምንጓዝ ሳናገናዝብ የምንቀመጥ ከሆነ ውድቀትን መጋበዝ ይሆናል ይህንን ለማሳየት የጠቀስኳቸውን ነው የሚል ስንኞች እንደገና ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡
It will be well, no need to care
Though how it will, and when and where
We cannot see, and can’t declare.
የፀጋዬ ገብረመድህንን ድንቅ ግጥም፣ ከአቤል ተስፋዬ ሁለት የቢልቦርድ ቁንጮ ዘፈኖች ጋር በማዛመድ ከባባዶቹን መልዕክቶች ለማሳየት ተጨማሪ ቀጠሮ ያስፈልጋል፡፡

Read 7556 times