Saturday, 21 July 2018 12:25

ጠ/ሚኒስትሩ ከ3 ሺህ ምሁራን ጋር ውይይት ያደርጋሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 የተሳታፊ መምህራን አመራረጥ አድሎአዊ ነው ተብሏል
             

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በመላ ሃገሪቱ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ከተውጣጡ 3 ሺህ ያህል ምሁራን ጋር ከነገ በስቲያ ሰኞ ውይይት የሚያደርጉ ሲሆን በመድረኩ የሚሳተፉ ምሁራን አመራረጥ የፖለቲካ ወገንተኝነትን መስፈርት ያደረገ ነው ሲሉ መምህራን ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ምሁራኑ የሚያደርጉት ውይይት “በተጀመረው ሃገራዊ ለውጥ ላይ የምሁራን ሚና ምንድን ነው?” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ እንደሚያተኩር ታውቋል፡፡
 የውይይት መድረኩ የተዘጋጀው የትምህርት ሚኒስቴር ከጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤት ጋር በመተባበር ሲሆን ጠ/ሚኒስትሩ ወደ መንበረ ስልጣኑ ከመጡ ወዲህ ከምሁራን ጋር የሚገናኙበት የመጀመሪያው መድረክ ነው  ተብሏል፡፡
ምሁራኑ ከ45 የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ከ4 የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተውጣጡ መሆናቸውን የገለጸው የጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት፤ ተሣታፊዎች የተመረጡትም በፆታና በትምህርት ደረጃ ተመጣጥነው እንደሆነ ጠቁሟል፡፡  
ምንጮች ለአዲስ አድማስ እንደጠቆሙት፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና አዳማ ዩኒቨርሲቲ እያንዳንዳቸው 150 ተሳታፊ መምህራንን መርጠው እንዲልኩ እድል ሲሰጣቸው፣ ቀሪዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች እያንዳንዳቸው 100 መምህራንን መርጠው እንዲልኩ ተጠይቀዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት፤ የተሣታፊዎች ኮታ የወጣው ተቋማቱ የተመሰረቱበትን ጊዜ መሠረት በማድረግ ነው ብሏል፡፡  
ቅሬታቸውን ለአዲስ አድማስ የተናገሩ ምሁራን፤ የተሳታፊዎች አመራረጥ አድሎአዊ ነው ሲሉ የተቹ ሲሆን በዋናነት አመራረጡ የፖለቲካ ወገንተኝነትን መስፈርት ያደረገ ነው ብለዋል፡፡ “ከዚህ ቀደም በኢህአዴግ አመራሮች በሚዘጋጁ ስብሰባዎች ላይ ሲሳተፉ የነበሩ መምህራን ናቸው አሁንም በተሳታፊነት የተመለመሉት” የሚሉት መምህራኑ፤ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን መድረኮች መንግስት ላይ የሰላ ትችት ሲያቀርቡ የነበሩ ምሁራን ከመድረኩ እንዲገለሉ ተደርገዋል ብለዋል፡፡  
የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት በበኩሉ፤ መምህራኑን መልምሎ ለውይይቱ መላክ ለዩኒቨርሲቲዎቹ አስተዳደሮች የተሰጠ ሃላፊነት መሆኑን አስታውቋል፡፡

Read 3285 times