Saturday, 24 February 2018 12:03

“ጅብ ጥጃ ጠብቅ” ቢባል፤ “ቢጠፋብኝስ?” አለ

Written by 
Rate this item
(22 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን አንድ እረኛ በጎቹን እየጠበቀ ሳለ፣ አንድ ሀሳብ መጣለትና ከፍ ወዳለው ኮረብታ ወጣ፡፡
ከዚያም፤ “ተኩላ! ተኩላ! በጎቻችንን ሊጨርስ መጥቷል፡፡ ቶሎ ድረሱ!” ሲል ለመንደሩ ህዝብ ጮኸ፡፡
መንደሬው ጦር ያለው ጦሩን፣ ቆንጨራ ያለው ቆንጨራውን፣ ዱላ የያዘ ዱላውን ይዞ እየሮጠ ኮረብታውን ወጥቶ ወደ ግጦሹ ሜዳ ሄደ፡፡
“የታለ፣ ተኩላው?” ብለው ጠየቁት፡፡
“ተኩላውማ ወደ እናንተ ስጮህ ሰምቶ ሸሸ!” አላቸው፡፡
መንደሬዎቹ አመለጠን ብለው እየተናደዱ ተመለሱ፡፡
ከአንድ ሳምንት በኋላ ያ እረኛ እንደገና ወደ ኮረብታው ይመጣል፡፡
ከዚያም፤
“ተኩላ! ተኩላ! ያ ተኩላ በጎቻችንን ሊበላ መጥቷል፡፡ ድረሱልኝ!” አለ፡፡
መንደርተኞቹ፤
“ዛሬስ አያመልጠንም! በታችም በላይም መውጫ መግቢያውን እንዝጋበት፤ የትም አይጠፋም!” እያሉ በግሪሳ መጡ!”
እግጦሹ ሜዳ ሲደርሱ፤
“የታለ ተኩላው? ዛሬ አንምረውም!” አሉና ጠየቁት፤ እረኛውን፡፡
እረኛውም፤
“አይ ዛሬ እንኳን ማ ለችግሬ እንደሚደርስ፣ ማ እንደማይመጣ፣ ማ ለበጎቹ እንደሚጨነቅ፣ ማ እንደማይጨነቅ፣ ለመለየት ብዬ ነው እንጂ ተኩላው አልመጣም! አለና መለሰ፡፡
መንደርተኞቹ፤ እየተናደዱና በእረኛው እያማረሩ ወደየቤታቸው ተመለሱ፡፡
በሶስተኛው ሳምንት በእርግጥም ተኩላው መጣ!
እረኛው እየሮጠ፣ እያለከለከ ወደ ተራራው ወጣ፡፡
“ተኩላ! ተኩላ! ዛሬ የምሩ ተኩላ መጥቷል፡፡ በጎቻችሁ እንዳይበሉ በነብስ ድረሱ!” አለ፡፡ ማን ይስማው? ማንም ሰው ሳይመጣ ቀረ! ተኩላው በነፃነት የሚችለውን ያህል በግ ቅርጥፍ አድርጎ በላና ሄደ፡፡
*        *      *
“ዋዛ ፈዛዛ ልብ አያስገዛ” የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ውሸት ሆነው ሲደጋገሙ ዕውነት የሚመስሉ፣ ወይም የሚሆኑ አያሌ ነገሮች አሉ፡፡ በእርግጥ ደግሞ የሂትለር ዋና ፀሐፊ ጎብልስ፤ “አንድን ውሸት ደጋግሞ በመናገር ወይም በማስነገር ዕውነት ለማድረግ ይቻላል” የሚለውንም አንዘነጋም! ህብረተሰብ በእጅጉ ባልነቃበት አገር፤ ውሸትን ዕውነት ለማስመሰልም ሆነ ዕውነትን ውሸት ለማስመሰል መሞከር አያስገርምም! ፖለቲካ ብዙ የማስመሰል ጥበብ አለበት፡፡ ሀሳዊውን ፖለቲከኛ ከሀቀኛው መለየት የህዝብ ኃላፊነት ነው! በዘልማድ “እገሌ ክፉኛ ይቦተለካል” ማለት፤ ሸፋጭ ነው፣ ቀጣፊ ነው ማለት ነው፡፡ ምናልባት Politics is a dirty game የተባለው ለዚህ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በእርግጥም ፖለቲካ አስቀያሚ ጨዋታ ነው፡፡ በፖለቲካ ይሉኝታ የለም። ያም ሆኖ በፖለቲካው በዚህ መንገድ ብሄድ ያዋጣኛል አያዋጣኝም ብሎ መጠየቅ፤ የብልህ እርምጃ ነው፡፡ ትላንት ያሉትን ሽምጥጥ አድርጎ መካድ ፖለቲካ ነው፡፡
ፖለቲካ ለሱ መፈጠርን ይጠይቃል፡፡ ምሁር ወይም የሙያ ሰው ለፖለቲካ አይሆንም፤ የሚባለው ከዚህ መሰረታዊ የፖለቲካ ባህሪ በመነሳት ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን በየትኛውም የፖለቲካ ጎራ እንሰለፍ፣ የሀገርና የህዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ መቆም የሀቀኛ ፖለቲከኛ ተግባር መሆን አለበት፡፡
ከፖለቲከኝነት ጋር ሳይነጣጠል እጅ ለእጅ ተያይዞ የሚጓዝ አንድ አባዜ አለ - ሙስና! ይህ አባዜ በተለይ በአፍሪካ መሪዎች ዘንድ እንደ ማተብ የሚጠለቅ፣ እንደ ዳዊት የሚደገም የዕለት የሰርክ ፀሎት ነው! “የዕለት እንጀራዬን አታሳጣኝ” ወደ “የዕለት ሙስናዬን አታሳጣኝ” ተለውጧል! “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” የሚለው ተረት፤ የባለስልጣኑ መሪ - መፈክር ሆኗል፡፡
በሙስና የተሰራው ህንፃ አፍ ቢኖረው ስንቱን ባጋለጠ ነበር፡፡ የታጠረም ሆነ ያልታጠረ አጥር አፍ ቢኖረው፣ ስንቱን ጉድ ባደረገ ነበር፡፡ ወገናዊነት መናገር ቢችል ኖሮ፣ ስንቱን ግፍ ባስረዳን ነበር፡፡ ዲሞክራሲ አፍ ቢኖረው ኖሮ፣ ስንቱን ሀሳዊ ዲሞክራት አፉን ባስዘጋ ነበር፡፡ ፍትህ ርትዕ አንቀፅ መጥቀስ ቢችል ኖሮ፣ ስንቱን ኢ-ፍትሐዊ ድርጊት ባደባባይ ባጋለጠ ነበር፡፡ ሀገራችን ገና ብዙ መንገድ ይጠብቃታል። ማደግ ያለበት መለወጥ ያለበት፣ መቀልበስ ያለበት አያሌ ጉዳይ ይጠብቃታል፡፡ ይህን መፈፀም ያለባቸው ከየጎራው ያሉ አካላት በሙሉ ፈቃደኝነትና ቆራጥነት ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡ አፋቸው ሌላ ልባቸው ሌላ የሚያስብ ከሆነ ግን “ጅብ፤ ጥጃ ጠብቅ” ቢባል፤ “ቢጠፋብኝስ?” አለ፤ እንደተባለው ይሆናል!  

Read 8236 times