Sunday, 10 December 2017 00:00

የተዋናዩ ትርጉም አጫጭር ልቦለዶች!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

    ከብዙ ሀገሮች ልምድ እንደምናስተውለው፣ ለአንድ ሀገር የሥነ- ጽሑፍ ሥራዎች ማበብ፣ የትርጉም ሚና የዋዛ አለመሆኑን ነው፡፡ ታላላቆቹ የሥነ ጽሑፍ ማህበረሰብ የበቀለባቸው እንደ እንግሊዝ ያሉት ሀገራት እንኳ ምጣዳቸውን ያሟሹት በትርጉም ሥራዎች ነበር፡፡
እኛም ሀገር አይብዛ እንጂ ትርጉሞች ለሥነ ጽሑፋችን አስተዋፅዖ አድርገዋል፡፡ አሁንም እያደረጉ ነው፡፡ በቅርቡ ገበያ ላይ የዋለውን የአርቲስት ፈለቀ አበበን “የከተማው ዘላን” የተሰኘ መጽሐፍ የምቃኘው በዚህ ዓይን ነው፡፡ ባንድ በኩል የአንባቢውን የንባብ ረሃብ ማርካት፤ በሌላ በኩል ለሀገራችን ሥነ-ጽሑፍ ጠቃሚ የሆኑ ፍሬዎችን ማሥቀረት፡፡
ፈለቀ አበበ፣ በ175 ገፆች ቀንብቦ ያሰናዳቸው አጫጭር ታሪኮች፤ በዓለማችን አንቱ የተባሉ ደራሲያን የፃፏቸው ናቸው፡፡ በአፍሪካ በአሜሪካና በአውሮፓ ሥነ ጽሑፍ ግዙፍ ስም ያላቸውን ሰዎች ማንነት ለማየትም ሣይቀር ጠቃሚ ነው እላለሁ። በተለይ ከየደራሲያኑ ሥራዎች ቀድመው፤ ከፎቶግራፋቸው ጋር የተቀመጡት አጫጭር የህይወት ታሪክ መግለጫዎች፣ ሕይወት ታሪካዊ ሂስ በሚለው ዐይን ለማየት ፍንጭ ይሰጡናል፡፡
በተለይ ደግሞ ቼኑዋ አቼቤ፤ ማርክ ትዌይን፤ አንቷን ቼኮቭ፤ ካህሊል ጂብራን፣ ኤድጋር አላን ፖ፣ ኦ ሔነሪ፣ ቶልስቶይ የመሳሰሉትን ደራሲያን ሥራዎችና ፕሮፋይል ማቅረብ በተለይ ለወጣት ደራሲያን ጠቀሜታው ብዙ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ መጽሐፉን በጥቅሉ ሥናየው፣ ብዙዎቹ ታሪኮች የሰው ልጅ ህይወት ውስጥ ያሉ ወጣ ገባዎችንና ጥያቄዎችን የቦረቦሩ ናቸው፡፡ አንዳንዶች የዘመናቸውን ቀለምና ሥዕል ቢያሣዩም፣ ያው ሥዕል ዛሬ በእኛ ዘመንና ሀገር እውን ሆኖ እናየዋለን፡፡ ለምሳሌ ማርክ ትዌይን “የሰዐሊው ዕረፍት”  በሚል ርዕስ የፃፈው ታሪክ፣ ዛሬ በእኛ ሀገር ከያንያን ህይወት  የምናየውን ውጣ ውረድና ፍልሚያ ያሣያል፡፡ ከሁሉ ይልቅ ደግሞ የጥበብ ሥራዎች ዋጋ በህብረተሰቡ ዘንድ ዝቅ ያሉና ዋጋ የማያወጡ በመሆናቸው፣ የደራሲያንና የሰዐሊያንን እንጀራን ለማሸነፍ የሚደረግ ፍልሚያን ያንጸባርቃል፡፡
ፅሁፉ ከያኒያኑ/አርቲስቶቹ የሠሩት ሥራ የሚላስ የሚቀመስ ነገር እንኳ አላመጣ ብሏቸው የዘየዱት መላና በተራቸው ብልጥ ሆነው የሠሩትን ሥራ፣ የተጠቀሙበትን  ጥበብ የሚያሣይ ነው፡፡
ብዙ ጊዜ በቀልብ ሣቢ ፍልስፍናው የምንማለልለት ካህሊል ጂብራን፤ “ትናንት እና ዛሬ” በሚል ርዕስ የፃፈው ልቦለድ፤ ያንድ ገፀ ባህሪን እሣት ላይ የተጣደን ህይወት ያሣየናል፡፡ ታዲያ ገፀ ባህሪው የተጣደበት እሣት፣ ብዙዎቻችን የምንጎመዥለትና አንዳንዴ እርስ በርስ የምንጋደልበት፣ የምንከዳዳበት “ሀብት” የተባለ ብርቅዬ ነገር ነው፡፡ ጂብራን ግን የድህነት ነፃነትና ጥፍጥናን ነው የሚተርከው። እጅግ ውብ የሆነ ቋንቋ የሚጠቀመው ካህሊል ጂብራን፤ እጅግ መሳጭ በሆነ መንገድ በራሱ ዐይን ያየውን ሥራ ያሣየናል፡፡
“ትናንት ፎልፏላ ነበርኩ፤ የህይወት ፌሽታን ሁሉ ከእረኞች ጋር የምካፈልና መብላት፣ መጫወት፤ መስራት፣ መዝፈን፣ መጨፈሩ፣ ለልብ እውነት በተቃኘ ዜማ የታጀበ፡፡ ዛሬ፣ ራሴን ያገኘሁት፤ በቀበሮዎች መካከል በፍርሃት እንደሚንዘፈዘፍ የበግ ግልገል ሆኜ ነው፡፡ በመንገድ ስዘዋወር፤ በጥላቻ የሚንቦገቦጉ አይኖች አፍጥጠውብኝ፤ በንቀት ወይ በቅናት ጣታቸውን ወደኔ ይቀሥራሉ..”
 ይህ ከሀብት ጋር ተያይዞ የመጣውን ጣጣ ጠቋሚ ነው፡፡ የህይወት መልክ ተቀየረ፣ ፅጌረዳዋን ህይወቴን እሾህ ከበባት፣… የነፃነት ባንዲራዬን ቀለም፣ ሀብት አነተበው፡፡-- እያለ ነው፡፡
ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ገደማ ከኢትዮጵያ አንባቢያን ጋር በብዙ የተዋወቀውና “After Twenty Years” በሚለው አጭር ልቦለድ፣ የባህር ዳር ተማሪዎችን ከሃያ ዓመት በኋላ ተቀጣጥረው እንዲገናኙ ያደረገው ኦ ሔነሪ፤ በፈለቀ አበበ አይን ገብቶ፣ የመጽሐፉ ርዕስ የሆነውን “የከተማው ዘላን” የሚለውን አጭር ልቦለድ ተርጉሞለታል፡፡ ኦ ሔነሪ ከሚታወቅበት ልዩ ስልት አንዱ ባልተጠበቀ ሁኔታ ታሪክን መጨረስ ነው፡፡ surprise ending ይሉታል፡፡ ታዲያ በዚህ መጽሐፍም ውስጥ አንድ የማዲሰን አደባባይ አውታታ፣ ዝብርቅርቅ የህይወቱ ቀለበት ሲሽከረከር፣ የሚገጥመውን የየአንጓውን ገጠመኝ ያሣያል፡፡ ህይወት እንዳሰቡዋት ብቻ ሳትሆን እንዳላሰቡዋት፤ እንደተመኟት ሣይሆን እንደተመኘችው እንደሆነ ያሣያል፡፡ ለአበባ የተዘረጋ እጅ እሾህ ሲጨብጥ፣ ሣቅ የናፈቀ ፊት እንባ ሲፈሥበት… ዓይነት ነገር!
ከሠቆቃ ወደ ደልቃቃ ደሴት የሚያደርገው ጉዞ፣ በፖሊሶች እጅ ገብቶ ትርጉሙ ሲዛባ፤ ምኞቱ ሲከሥም፣ ሳቁ ሲረግፍ፣ የልቡ አደባባይ ላይ ሙሾ ሲነግሥ … ብዙ ብሏል፤ ኦ ሔነሪ!
“--ሶፒ በክረምት ወራት ሊኖረው የሚሻው፤ ያን ያህል የተጋነነ ነገርም አይደለም፡፡ መቸም በመርከብ ተሳፍሮ ለመጓዝ አይገደውም፡፡ ወደ ደቡብ ወይም ኔፕልስ ሄዶ በጠራው ሰማይ ስር ክረምቱን ለማሣለፍም ከቶ አይከጅልም፡፡ እሱ የሚጓጓለት አንድና አንድ ነገር ብቻ ቢኖር ሦስቱን ወራት፤ በየቀኑ ትኩስ ምግብ እየታደለው ሌሊቱን፣ በጥሩ አልጋ ላይ የድሎት እንቅልፉን መለጠጥ።---”
የሶፒ ምኞት ይህ ነው፣ ወህኒ ቤት ውስጥ ይህንን መራራ ክረምት ማሳለፍ፡፡ መንገዱ ግን ቀላል አይደለም። በቀላሉ ወህኒ ይገኛል እንዴ?... እርሱም እድል ሲቀና ነው፡፡… ወህኒው ግን ከእኛ ሀገር ወህኒ ጋር የተፈጥሮም የገቢርም ልዩነት እንዳለው የሶፒ ጉጉት ያሣያል፡፡ ወህኒ- ቤት የሚለውን እኛ ማረሚያ ቤት ብለን ስሙን ከመቃብር በቀር ውስጡን ለቄስ ብለን ትተነዋል፡፡ ብቻ የህይወት እርከናችንን ልዩነት፤ የአስተሳሰባችንንም ርቀት እንድናጤን ሳይረዳን አይቀርም፡፡  
ጥልቅ ሥነ ልቡናዊ  ጉድጓዶችን ቆፍሮ፣ የአንባቢን ተመሥጦና ምርመራ የሚጠይቀው ዕውቁ ደራሲ አንቷን ቼኮቭ የፃፋት የአጭር አጭር ልቦለድ፣ ፈለቀ “የዋህ” በሚል- ተርጉሟታል። ተራኪው በአንደኛ መደብ አንፃር ይተርከዋል። ትረካው ያናድዳል፤ ያበሣጫል፤… ያረጋጋል። ጉዳዩ የደሞዝ ክርክር ስለሆነ ከዚህ በፊት በልጅነቴ ሳይቀር የማውቃቸውን ምስኪን ሠራተኞች ህይወት አሳይቶኛል፡፡ በደሞዝ ቀን “ስኒ ሠብረሻል፣ ልብስ ቀደሻል፣ ግድግዳ ፍቀሻል” እየተባሉ ባዶ እጃቸውን የሚባረሩትን የቤት ሰራተኞች አሥታውሶኛል፡፡ ወይ ጉድ! ጥቁሩም ነጩም፣ ፈረንጁም ሀበሻውም- ልቡ አንድ ዐይነት ነው እንዴ? አሠኝቶኛል፡፡ ግን ደራሲው የራሱ ስልት አለው፡፡ ቆንጆ ስልት!... ጭብጡም  ሸጋ ነው፡፡ ከታሪኩ ይህቺን አንቀፅ ልዋስና እንሠንቀው፡፡
“--ግን እንዲያው ልጠይቅሽ እስቲ… ለመሆኑ፣ እንዲህ ሁሉንም ነገር አሜን ብሎ መቀበል አግባብ ነው እንዴ? ለምንድን የማትቃወሚው? ስለ ምን ዝም ትያለሽ? በዚህች ክፉ ዓለም ላይ፤ እንዲህ አንገት ደፍቶና አጉል የዋህ ሆኖ መኖርስ ይቻላል እንዴ?!--”
ይህ ታሪክ እጅግ ብዙ ነገሮችን በጥቂት ቃላት፣ ጠባብዋን ቀዬ፤ ዓለምን በሚያህል ስፋት ያሥቃኛል። ቁም ነገር ተዘልዝሎ ቢቀመጥ ሁልጊዜ ትኩስ ትምህርት ያመጣል የሚል ስሜት ይፈጥራል።
ሌላው በመጽሐፉ የተካተተው የታላቁ ሩሲያዊ ደራሲ ሊዎ ቶልስቶይ “አዋቂዎቹ” የሚለው ድርሰት ነው። ድርሰቱ የቶልስቶይን ሞራላዊ መልክ ያንፀባርቃል። ይህ ደራሲ ለድሆች የሚራራ፣ ያለውን የሚያካፍል፣ ቢቻለው ሰዎች ሁሉ በሠላም እንዲኖሩ የሚተጋ ነው። እስከ መጨረሻው ከሀብት ይልቅ የሰው ልጆችን ወድዶ፣ ሰውን በፍቅር እየተከተለ ያለፈ ሰው ነው፡፡ በዚህ “አዋቂዎች” በሚል ድርሰቱም ይህንኑ ያጎላል፡፡ የህፃናትን ንፅህናና ቅንነት፣ ብልጭ- ድርግም የሚል ስሜትና የአዋቂዎችን ውስጠ ገዳዳነት ይተቻል፡፡ የዕድሜ ብዛት ከበጎ ነገር ይልቅ ብዙ ጊዜ ራስ ወዳድነትንና ቂምን እንደሚያሥታቅፍ፤ ግና ሁሉም ነገር ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚል፤ እንደ ህፃናት የዋህ ብንሆን መልካም እንደሆነ እናስተውልበታለን፡፡ እውነትም በጎ ባልሆነ ሥራችን እናፍርበት ዘንድ እውነት ከፊታችን ይቆማል፡፡
በጥራዙ ውስጥ- ሁለት አጫጭር ልቦለዶችን ያበረከተው ኤድጋር አላን ፖ፤ ከድርሰቶቹ ባሻገር እንድናሥበው የሚያደርጉን ብዙ ነገሮች አሉ። የወንጀል ምርመራ ፅሁፎች ማስተዋወቅ፤ ከዚያም ሌላ የአጭር ልቦለድ አላባውያንን ለዓለም ማበርከቱ፣ ጋዜጠኝነቱና የህትመት ማስታወቂያ ፈር ቀዳጅነት ሁሉ ይታሰባል። ወደ ህይወቱ ስንሄድ አሣዛኝ ኑሮው፣ ቁማርተኝነቱና ሠካራምነቱ --- የግል ህይወቱን በመከራ እየዳጠው ማሣለፉን አንረሳውም፡፡ ሚስት አግብቶ ብርድልብስ አጥታ፣ የእርሱን ኮት ለብሳ ማደሯን፣ ድመት አቅፋ፣ ሙቀት መናፈቅዋን ሥናይ … በተለየ መስመር አስቀምጠን ከንፈር ልንመጥለት ግድ ይለናል፡፡ ግን ደግሞ በዘመኑ ጥሩ የሚባል ገጣሚና ጋዜጣ አዘጋጅነቱን እናደንቃለን። ብቻ አላን ፖ ቢመነዘር ሺህ ሰው የሚወጣው ነበር። ደራሲው “ህያው ልብ” እና “የቀዩ ሞት ጭምብል”ን በዚህ በፈለቀ አበበ መጽሐፍ ልኮልናል፡፡ በተለይ “የቀዩ ሞት ጭምብል” ብዙ የሚፈተሽና ዘርፈ ብዙ የህይወት ጠርዞችን የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡
በአጠቃላይ “የከተማው ዘላን” መፅሐፍ ውስጥ የተካተቱት ድርሰቶች፣በተለያየ ሥነ ልቡናና መልክዐ ምድር፣ በተለያየ ዘመንና ዜግነት የተፃፉ ስለሆኑ፣ በጥናት መንፈስ ላነበባቸው ብዙ ትሩፋት ይኖራቸዋል ብዬ አምናለሁ፡፡
የመጽሐፉ ተርጓሚ ፈለቀ አበበም በሀገራችን ከተለመደው በላይ ሆኖ፣ ትወናውን፣ ግጥሙን አሁን ደግሞ ትርጉሙን መስራቱ እጅግ የሚያስደንቀው ነው። ለራሳችን ያህል እንኳ ማንበብ ተስኖን፣ ባንድ ሞያ ማማ ላይ ተንጠልጥለን፣ “አጨብጭቡልን” ለምንል ባይተዋሮች፤ ፈለቀ ባንድ ጫማ ቆሞ ብዙ መስራት እንደሚቻል አስታውሶናል፡፡ ይሄኔ ነው፣ አንድ ድራማ ላይ ከመንገድ ተጎትቶ መጥቶ ለተወነ “ግልብ”፣ የሚሰጠው “አርቲስት” የሚለው ስያሜ ወሰን አይጠበውም ወይ? የሚያሰኘን፡፡
በመጨረሻ  ፈለቀ አበበን በርታ፣ ቀጥል! ለማለት እወዳለሁ! ካንተ ገና ብዙ እንጠብቃለን!!

Read 2129 times