Saturday, 18 November 2017 12:34

ኤርትራዊያን በአዲስ አበባ የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

በኢትዮጵያ በስደት ላይ የሚገኙ ቁጥራቸው እስከ 500 የሚገመት ኤርትራውያን፣ የሀገራቸውን መንግስት በመቃወም ባለፈው ረቡዕ ህዳር 6 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ አፍሪካ ህብረት ጽ/ቤት ፊት ለፊት ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል፡፡
ሰልፈኞቹ የሀገራቸው መንግስት የዜጎችን ሰብአዊ መብት እንደሚጥስ፣ በሃይማኖትና በትምህርት ጉዳዮች ጣልቃ እንደሚገባና ወጣቶችን ለአስከፊ ስደት እየዳረገ እንደሚገኝ ለተቃውሞ ይዘውት በወጡት መፈክር አመልክተዋል። በሀገሪቱ የውስጥ ፖለቲካ ጉዳይም የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስታትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት ጣልቃ ገብተው፣ ዜጎቻቸውን ይታደጉላቸው ዘንድ ጠይቀዋል፡፡
ባለፈው ሰሞን በአስመራ ከተማ ከ26 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገውን የተቃውሞ ሰልፍ ተከትሎ በአገራቸው መንግስት የተፈፀሙ ግድያዎችንና እስሮችን ያወገዙት ሰልፈኞቹ፤ አፍሪካውያን ወንድሞቻቸው ከጎናቸው በመቆም ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ተማጽነዋል። በተቃውሞ ሰልፉ ላይ ከ25 በላይ ሰዎች መገደላቸው መዘገቡ አይዘነጋም፡፡ ኤርትራውያን ስደተኞች፣ በ2009 ዓ.ም ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፍ በአዲስ አበባ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

Read 2348 times