Monday, 18 September 2017 10:26

የእውቋ ደራሲ ሰዓዳ መሀመድን ህይወት እንታደግ ተባለ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)


                          “ለውጭ አገር ህክምና 2 ሚ. ብር ያስፈልጋታል”
                          “አሁንም ከተጋገዝን ልናድናት እንችላለን” ወዳጆቿ
                                 
      በአጫጭር ልቦለዶች እንዲሁም በሬዲዮና በቴሌቪዥን ድራማዎች ደራሲነቷ የምትታወቀው ሰዓዳ መሀመድ፤ በጤናዋ ላይ በደረሰው እክል አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልጋታል ተባለ፡፡ ደራሲዋ በአሁኑ ወቅት ሁለቱም ኩላሊቶቿ ከጥቅም ውጭ በመሆናቸው ዲያሊስስ እያደረገች እንደምትገኝ የተገለፀ ሲሆን ውጭ አገር ሄዳ ለመታከም ወደ 2 ሚ. ብር ገደማ እንደሚያስፈልጋት ዘመድ ወዳጆቿ ጠቁመው ይህችን ብርቅ ደራሲ ከተደቀነባት አደጋ ለመታደግ ሁሉም ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ሴቶችና ህፃናት ህይወት እንዲለወጥ በሙያዋ በርካታ አስተዋፅኦ እንዳደረገች የሚነገርላት ደራሲዋ በተለይ በፓፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር፣ እሷ በዋና ፀሀፊነት የተሳተፈችባቸው ድራማዎች “Art for Social Change” (ኪነ-ጥበብ ለማህበረሰባዊ ለውጥ) በሚል መርህ የተሰሩ እንደነበሩና በዚህም የበርካታ ኢትዮጵያን ህይወት ትርጉም ባለው መልኩ የለወጡና ብዙዎችን ከሞት ማትረፍ የቻሉ መሆናቸውን ጆንስ ሆፕ ኪንስ፣ ዓለም አቀፍ የስነ-ህዝብ ድርጅት (UNFPA) እና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ባካሄዷቸው ጥናቶች ማረጋገጣቸው ታውቋል፡፡
ደራሲ ሰዓዳ ድርሰት በይፋ ከጀመረችበት ከ1985 ዓ.ም አንስቶ ያለ እረፍትና ያለማቋረጥ ስትሰራ እንደነበር የገለፁ ወዳጆቿ፡፡ እረፍት እንድታደርግ በተደጋጋሚ ቢነግሯትም እሷ ግን እንዲሁ ስትተጋ በመኖሯ ለዚህ የጤና እክል እንደተጋለጠች በቁጭት የገለፁ ሲሆን አሁንም ከተጋገዝን ልናድናት እንችላለን በሚል ሙሉ ትኩረት ሰጥተው እየተንቀሳቀሱ መሆኑም ታውቋል፡፡
“አትበገሬዋ እመቤት” (The Iron Lady) በሚል ቅፅል ስም የምትታወቀው ደራሲዋ፤ “እሾሀማ ወርቅ” በሚል ርዕስ ታትሞ በኢትዮጵያ ሬዲዮ “ከመፅሐፍት ዓለም” በሚል የተተረከ ረጅም ልቦለድ ያላት ሲሆን “እፍታ” ቁጥር 2, 3, 4 እና 5 በመባል በሚታወቁት መፅሀፍት ላይ በርካታ ድርሰቶችንም አሳትማለች፡፡ “ወንዞች እስኪሞሉ” እና “ያልተነበቡ ልቦች” በሚል ርዕስ በፖፕሌሽን ሚዲያ ሴንተር ባሳተማቸው መድበሎች ላይ አጫጭር ልቦለዶቿም ተካትተዋል፡፡ በ”እለታዊ አዲስ” ጋዜጣ እና በ”ሩህ” ጋዜጣና መፅሄት ስትሰራ የነበረችው ሰዓዳ፤ በኢትዮጵያ ሬዲዮ የተላለፉ “ያልተደፈነ ጉድጓድ”፣ “ያበቃ ህልም”፣ “ጥልፍልፎሽ”፣ “መክሊት”፣ “ሶስቱ መስኮቶች” እና “የእባቡ እግሮች” የተሰኙ ድራማዎች ደራሲም ናት፡፡
ሰዓዳ ከዚህም በተጨማሪ “ብስራት”፣ “ምዕራፍ”፣ “የረገቡ ፈትሎች”፣ “የብርሀን አፅናፎች” እና “የወንዝ ድንጋይ” የተሰኙ በፖፕሌሺን ሚዲያ የተሰሩትን የሬዲዮ ድራማዎች ከታዋቂ ጋዜጠኛና ደራሲ ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ፣ መስፍን ጌታቸውና ከአዲስ ገ/ማሪያም ጋር በጋራ የፃፈች ሲሆን  በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (EBC) ይተላለፍ የነበረውን “የቤት ስራ” ድራማን ከቴዎድሮስ ተ/አረጋይ ጋር በጋራ ስትፅፍ እንደነበርና “የዘመን” ድራማ የስደቱን ክፍል ማዘጋጀቷም ታውቋል፡፡
ሁለቱም ኩላሊቶቿ ከጥቅም ውጭ ሆነው በስቃይ ላይ ለምትገኘው ለዚህች ድንቅ ደራሲ ሁሉም ተባብሮ ወደ ጤናዋ እንድትመለስ ይደግፉት ዘንድ ወዳጅ ዘመዶቿ እርዳታ ለማድረግ ለሚሹ ወገኖች በእናቷ ወ/ሮ ከድጃ መሐመድ ስም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ ቁጥር 1000218481648 ከውጭ ድጋፋቸውን ለሚያደርጉ SWIFT CODE-CBETETAA ማስገባት ይችላሉ ተብሏል፡፡

Read 2098 times