Sunday, 27 August 2017 00:00

የክፍሌ አቦቸር ሣልሳዊ መጽሐፍ የጫረብኝ ትዝታ

Written by  ከዳግላስ ጴጥሮስ
Rate this item
(9 votes)

 በምርጥ ቃላት ተከሽነው፣ በውብ ገለፃዎች ተሸምነው፣ ስሜትን በሚኮረኩሩ አባባሎች ተቀናብረው ከሚበየኑ የጥበባት ዘርፎች መካከል፣ ሥነ ግጥምን የሚተካከል ይኖራል የሚል ግምት የለኝም፡፡ የሥነ ግጥም ተመራማሪ ምሁራን ብቻ ሳይሆኑ የግጥም መጽሐፍ ለማሳተም የሚሞክሩ ደራስያንና ደራስያትም ሳይቀሩ አብዛኛውን ጊዜ በግጥም መድበላቸው መግቢያ ወይንም የመቅድም ክፍል ውስጥ ስለ ድንቅ ሥነ ግጥም ባህርያት (ሳይንሱን) ወይንም ስለ ምርጥ ግጥም (ምርቱን) ምንነት በተመለከተ በብያኔ መልክ የራሳቸውን መረዳት፣ በተመረጡ ቃላት ተጠብበው ወርወር ማድረጋቸው የተለመደ ነው፡፡
በግሌ ግን አንድ ግጥም ውስጤን ዘልቆ ካነዘረኝ፣ ስሜቴን ኮርኩሮ ለአንዳች ምላሽ ከቀሰቀሰኝ ወይም የማኅበረሰቤን የፊት ዕድፍ ካመላከተኝና የማበሻውን መፍትሔ ከጠቆመኝ፣ ያ ግጥም ለእኔ በእውነትም “ከቅልጥም የሚጥም” ብርታት ይኖረዋል፡፡ የጥሩ ግጥም ባህርያት እኒህና እኒያን ይመሳስላሉ ከሚል ደማቅ ትንታኔም የበለጠ ለውስጤ እርካታን ሲፈጥር ይሰማኛል፡፡
ሀገሬ ካፈራቻቸው ድንቅ ገጣሚያን መካከል ወዳጄ ክፍሌ አቦቸር (ሻለቃ)፣ በቀዳሚነት ከምጠቅሳቸው መካከል አንዱ ነው፡፡ “ከጣትም ጣት ይበልጣል” እንዲሉ፣ በሀገር ጉዳይ ብዕሩ እያነባ፣ አንዳንዴም እየፈገገ፣ ሲያሻውም እየቆዘመ፣ በቃላት ትንታግ የስሜት ወላፈንን የማቀጣጠል ብርታት ካላቸው ብዕረኞች ውስጥ  ገጣሚ ክፍሌ አቦቸርን የሚጋፋ ባለተሰጥዖ፣ በቀዳሚነት መጥቀሱ አይሆንልኝም፡፡
ክፍሌ አቦቸር በቀዳሚ ሥራዎቹም ሆነ “ምሥጢሯን-ያልገለጠልን” በሚል ርዕስ ሰሞኑን ለንባብ ባበቃው ሣልሳዊ መጽሐፉ ውስጥ የብዕር ቀለሙን ያዋሃደውም ሆነ መጻፊያ ሰሌዳውን የዘረጋው፣ በሀገሩ  ማዕከላዊ ጉዳይ ላይ ነው፡፡ ሀገሩ ለእርሱ አልፋ ኦሜጋው ነች፡፡ ሀገሩን ሲያሞግስ አቤት ሲያምርበት፡፡ ውበቷን አድምቆ ሲሞሽራት ደግሞ አቤት ስትዋብለት፡፡ የሀገሩን ሀዘን ሀዘኔ ብሎ፣ ጉስቁልናዋን ብቻ ሳይሆን ተስፋዋንም ሲያመላክት አቤት ሲዋጣለት፡፡ አብነት ልጥቀስ፡-
ከቀበሌሽ፣ ከአፈርሽ ላይ፣
ከግንድሽ ስር፣ እኔም በቀልኩ፣
ከጅረትሽ-ተራጭቼ፣ በአደግሽበት መንደር-አደኩ፣
በቋንቋሽ፣ አፌን ፈትቼ፣
“ሀ”
ባልሽበት፣ ፊደል-ቆጠርኩ፣
በሮጥሽበት፣ ሜዳ፣ ዳገት፣
እኔም ድኬ፣ ከዚያው ከረምኩ፡፡
ይሄን ይዤ፣ ተሸክሜ፣
እንዳ’መትሽ፣ ዓመት ጨረስኩ፣
በስክነትሽ - ሰከንኩና፣ የኋላዬን - ለፊት፣ አሰብኩ። … ይለናል፡፡
ገጣሚውን በተመለከተ አንድ አይረሴ ትዝታ ልቀስቅስ፡-
የቅዱስ መጽሐፉ ሙሴ፤ ከግብፅ ባርነት ነፃ ያወጣቸውን ወገኖቹን አርባ ዓመት ከመራቸው በኋላ ወደ ተስፋ ምድራቸው እየተቃረቡ ሲሄዱ፣ የፈጣሪው አፈ ጉባዔ በመሆን ለሕዝቡ እንዲህ በማለት ነበር የምድረ በዳውን ጉዞ ያስታወሳቸው፤ “አርባ ዓመት በምድረ በዳ መራኋችሁ፣ ልብሳችሁም አላረጀባችሁም፣ ጫማችሁም በእግራችሁ ላይ አላረጀባችሁም”
ዕድሜውን ያደለን ብጤዎቼ፣ ልክ በዚህ ወር፣ የዛሬ አርባ ዓመት እንደ መጽሐፉ ሙሴ ወደ ኋላ ልመልሳችሁ፡፡ የኢትዮጵያ ሚሊሽያ ሠራዊት የሚከተለውን መዝሙር እየዘመረ፣ ሀገሩን ከሶማሊያ ወራሪ ለመፋለም እንደምን በጀግንነት ወኔ እንደተንቀሳቀሰ ለማስታወስ፤
“ይህ ነው ምኞቴ፣ እኔስ በሕይወቴ፣
ከራሴ በፊት፣ ለኢትዮጵያ እናቴ”
እነዚህ ሁለት ስንኞች ተራ ስንኞች ብቻ አይደሉም፡፡ የተሸከሙት መልዕክት የሀገር ያህል ይሰፋል፡፡ ብዙዎቻችን ይህንን ድንቅ ዝማሬ የምናስታውሰው ትናንት እንደተከወነ ትዕይንት ነው፡፡ እንደ እስራኤላዊያን የምድረ በዳ ልብስ ዛሬም ከአርባ ዓመት በኋላ ግጥሙ አልነተበብንም፣ ዜማውም አላረጀብንም፡፡ ይልቅዬ ከታጠቅ ጦር ሠፈር እንደ ውሃ ሙላት እየተመመ፣ የአዲስ አበባን ዋና ዋና ጎዳናዎች  በድንቅ ዝማሬው እያወደ፣ በማሳረጊያነትም በመስቀል አደባባይ በአስደናቂ ወኔው ወገኑን ያኮራው በክዋክብት ቁጥር ልክ የሚገመተው ባለ ዝንጉርጉር ዩኒፎርሙ የሚሊሽያ ሠራዊት ምስል ዛሬም በውስጣችን ሕያው ነው። የብሔራዊ መዝሙር ያህል ክብደት የነበረውን ያንን መዝሙር ባስታወስነው ቁጥርም በትዝታ አርባ ዓመታት ተጉዘን፣ ከዚያ ጀግና ሠራዊት ጋር በለሆሳስ አብረን መዘመራችን እውነት ነው። ዕድሜውን አብዝቶ ይስጥልን፤ የግጥሙ ደራሲ ወዳጄ ክፍሌ አቦቸር!
በነገራችን ላይ የዛሬ አርባ ዓመት፣ የኢትዮጵያ ጀግኖች ከሶማሊያ ተስፋፊ ሠራዊት ጋር ለሉዓላዊነታችን ክብር ሲሉ የፈጸሙትን ዘመን አይሽሬ ተጋድሎና ትንቅንቅ በተመለከተ በአስደናቂ ትዕይንታዊ ትረካ ታትሞ፣ ከእጃችን የገባውን የሁለተኛ ደረጃ የሕብረተሰባዊት ኢትዮጵያ የጦር ሜዳ ጀብዱ ሜዳይ ተሸላሚ የመቶ አለቃ በቀለ በላይ ሁንዴን ታሪክ፣ “የጀግና ወረታ” መጽሐፍ ውስጥ በሚገባና እጅግ በሚያስደንቅ ትረካ የቀረበ ስለሆነ ማንበብ ይቻላል፡፡ እኒህ ጀግና መኮንን ዛሬ ያሉበትን ጎስቋላ ሕይወት የተመለከተ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሁሉ፣ ልክ እንደ እኔ ዓይኑ ብቻ ሳይሆን ልቡም ማንባቱ አይቀርም፡፡ ሀገሬ የፊት ፊቷን ብቻ እያየች፣ ለቀዳሚ ታሪኳና ጀግኖቿ ምን ያህል ፊት እንደነሳችም እኒህ የሀገር ጀግና ጥሩ ማሳያ ይሆናሉ። ባለፈው ሣምንት፣በዚሁ ጋዜጣ ላይ የእኒህ ጀግና ታሪክ መቅረቡ  ይታወሳል፡፡
“ይህ ነው ምኞቴ”ን መሰል በሙዚቃ የተቀናበሩ የገጣሚ ክፍሌ አቦቸር ግጥሞች በርካታ ናቸው። የሙዚቃው ንጉሥ ጥላሁን ገሠሠ፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ ፊቱ በእንባ እየታጠበ፣ በእናት ሀገር ፍቅር፤ በሚያውቀኝ በማውቀው፣ ለአንድነቱ ለነፃነቱ፣ ውረድ በለው፣ እንኳንስ በሕይወቴ እያለሁ በቁሜ፣ ለሀገሬ ስታገል ለድንበሯ፣ ከመራራው ትግል ከጀግኖች ደም ጀርባ ወዘተ. የሚሉት ግጥሞች፣ የክፍሌ አቦቸር የምንግዜም አይረሴ ሥራዎች ናቸው፡፡ በድምፃዊ ነዋይ ደበበ የተቀነቀኑ የተወሰኑ መሳጭ ግጥሞችም አይዘነጉም፡፡
ገጣሚ ክፍሌ አቦቸር፤ ከአሁን ቀደም “የእኔ ጋሻ” በሚል ርዕስ በ1978 ዓ.ም እና “አንድ ቀን” በሚል ርዕስ በ1982 ዓ.ም ሁለት መጻሕፍትን ለአንባቢያን ማድረሱ ይታወሳል፡፡ በ1970ዎቹ አጋማሽም የኢትዮጵያ ማተሚያ ኮርፖሬሽን፣ “ጽጌረዳ ብዕር” በሚል ርዕስ አሳትሞት በነበረው የግጥም መድበል ውስጥም የተወሰኑ ግጥሞች ተካተውለታል፡፡
የክፍሌ አቦቸርን የግጥም ሥራዎች ብስለትና ጥልቀት በተመለከተ ትዝታ ልቀስቅስ ብያለሁና፣ በርካታ ሃያሲያን የተፋለሙበትን አንድ የራሴን ገጠመኝ ላስታውስ፡፡ “የእኔ ጋሻ” የግጥም መድበሉን ያነበብኩት መጽሐፉ ለገበያ በቀረበበት ሰሞን ነበር፡፡ መጽሐፉን እንደገዛሁ፣ አራት ኪሎ ከቢሮዬ ጎን ይገኝ ከነበረውና አዘውትሬ ቡና ከምጠጣበት ከሽረጋ ቡና ቤት አረፍ ብዬ፣ ቡናዬን እየተጎነጨሁ፣ መጽሐፉን ማገላበጥ ጀመርኩኝ፡፡ ከዚያ በፊት ገጣሚውን የማውቀው በርቀት እንጂ ቅርበት አልነበረንም፡፡
ቡናዬን ፉት እያልኩ አለፍ አለፍ እያልኩ ግጥሞቹን ሳነብ፣ የአገጣጠሙ የተለየ ስልትና ሀገራዊ ይዘታቸው ውስጤን እንደ ክራር ምት ማንዘር ሲጀምረኝ ይታወቀኛል፡፡ ግጥሞቹ “አሃ!” እያሰኙኝ፣ እዚያው ቡናዬን ደጋግሜ እያስቀዳሁ፣ መጽሐፉን በአንድ ቁጭታ ንባብ፣ ከቡናዬ ጋር ፉት እያልኩ አጣጣምኩት፡፡
መጽሐፉን አንብቤ ብቻ በመገረም አላለፍኩም። ወዲያው ቢሮዬ እንደገባሁ፤ “የእኔ ጋሻ የግጥም መድበል” በሚል ርዕስ፣ ሂሳዊ ቅኝት ጽፌ፣ ለየዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ፣ ለወዳጄ ለአቶ ስሜነህ መኮንን አቀበልኩትና ጽሁፉ፣ በተለመደው የብዕር ስሜ፣ ሚያዝያ 25 ቀን 1978 ዓ.ም ታትሞ ለንባብ በቃ፡፡ ብዙዎችም በመልዕክቱ ደስ መሰኘታቸውን ተገነዘብኩ፡፡ በሣምንቱ ግንቦት 2 ቀን 1978 ዓ.ም ሌላው የወቅቱ ዝነኛ ባለ ብዕር ባጎር፣ የዳግላስ ጴጥሮስን ግምገማ በመተቸት፣ “የእኔ ጋሻ” የግጥም መድበል - በሚል ርዕስ የትምህርት ጥቅሱ ቦታ ብቻ ተለዋውጦ፣  ሃሳቤን በማደባየት፣ ሂሳዊ ግምገማቸውን አስነበቡን፡፡
አሸናፊ ዘደቡብ ከአዲስ አበባም፣ ግንቦት 9 ቀን 1978 ዓ.ም “የእኔ ጋሻ የግጥም መድበል” በሚል ተመሳሳይ ርዕስ፣ ባጎርን በመደገፍ፣ የሂስ አረራቸውን በዳግላስ ላይ አስወነጨፉ፡፡ “በእኔ ጋሻ” የግጥም መጽሐፍ ላይ የተጫረው የሂስ ክብሪት ወገን ለይቶ እየተጋጋለ ተፋፋመ፡፡ በአራተኛው ሣምንት፣ “የእኔ ጋሻ” እንደዚያ ነው? በሚል ርዕስ ዳግላስ ጴጥሮስ የመልስ መልስ በመስጠት፣ ባጎርንና አሸናፊ ዘደቡብን መሞገቱን ተያያዘው፡፡ በአምስተኛው ሣምንት፣ ግንቦት 23 ቀን 1978 ዓ.ም መድፉ የሚሰኙ ብዕረኛ፣ “ትችቱ ተገቢ አይደለም” በሚል ርዕስ በዚያው በዛሬይቱ ጋዜጣ የፍልሚያ መድረክ ላይ ሂሳዊ መድፋቸውን አፈነዱ፡፡ በሚቀጥለው ሣምንት፣ ዕውቁ የሀገራችን የቤተክህነት ሊቅ የተከበሩ አፈ ሊቅ አክሊሉ፣ “የእኔ ጋሻ እንደምን ቅኔ ለመባል በቃ?” በሚል መከራከሪያ፣ የብዕር ጦርነቱን ተቀላቀሉ፡፡ ከአፈ ሊቅ አክሊሉ ቀጥለው ዶ/ር ኢሳይያስ ዓለሜን መሰል ሌሎች በርካታ ዝነኛና ጎምቱ ባለብዕሮች፣ የሂሱን ሜዳ የጦርነት ቀጠና በማድረግ፣ በዛሬይቱ ሣምንታዊ ጋዜጣ ላይ የሃሳባቸውን ባዙቃ እያፈነዱ ጋዜጣዋን አጨሷት። አቤት ያ ዘመን!!! እነዚህን መሰል ትዝታዎች፣ የዛሬውን ፕሬስ ድርጅት ቢያባንኑትና ወደ ኋላ እንዲመለከት ቢያደርጉት ምኞቴ ነው፡፡
የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ አንባቢያንም፣ “ደግሞ ማን ይሆን ሣምንት የብዕር ሾተሉን የሚመዘው” እየተባባሉ፣ ጋዜጣዋ ከህትመት ምጣድ ላይ ሳትወጣ ተሻምቶ ለመግዛት፣ የብርሃንና ሰላምን ደጃፍ በሰልፍ ማጣበቡን ተያያዙት። የጋዜጣዋም ዋጋ በኮንትሮባንድ ሽያጭ ቀለበት ውስጥ ገብቶ፣ መደበኛ ዋጋው ከሣንቲም ደረጃ ከፍ ብሎ በጥቁር ገበያ እስከ አሥር ብር አሻቀበ። ለመሆኑ የዛሬይቱ ጋዜጣ ለምንና ማን ነበር ሞት ፈርዶባት፣ ከገበያ እንድትወገድ የወሰነባት? ሁሌም ራሴን እጠይቃለሁ፡፡
ይህንን አብነት መንደርደሪያ በማድረግም ቀደም ባሉት ዘመናትም ሆነ ዛሬ ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው፣ የክፍሌን የግጥም ሥራዎች መሠል የበርካታ ታላላቅ የሀገራችንን ሃያሲያንና የብዕር ሰዎች ቀልብ የሳበና ለሂስ ፍልሚያ ምክንያት የሆነ ድንቅና የተዋጣለት ሥራ፣ በታሪክ ተመዝግቦ መገኘቱን ወይም ዛሬም መኖሩን  እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ክፍሌ አቦቸር ለግጥም የተፈጠረ፣ ግጥምም ለርሱ የገበረለት፣ የሀገራችን ብርቅዬ የጥበብ ሰው መሆኑን ግን ከልቤ እመሰክራለሁ፡፡
“ምሥጢሯን - ያልገለጠልን” በሚል ርዕስ ባለፈው ሰኔ ወር በአሜሪካን ሀገር ታትሞ እዚያው ለምርቃትና ለስርጭት ስለበቃው ሦስተኛው መጽሐፉ በዝርዝር ለመቃኘት፣ መጽሐፉ በሀገር ውስጥ በብዙ አንባቢያን እጅ ስላልገባ፣ለሌላ ጊዜ አስተላልፌዋለሁ፡፡ ለማስተዋወቅ ያህል ብቻ አጠቃላይ ጉዳዮችን መቃኘት ይቻላል። መጽሐፉ ከ60 በላይ ግጥሞችን ሰንቆ፣ በ175 ገፆች የታተመ ነው፡፡ የግጥሞቹ ማዕከላዊ ጭብጥ፣ ያው እንደተለመደው፣ በወቅትና በሁኔታዎች የማይደበዝዘው የሀገሩ ጉዳይ ነው፡፡ በአዲሱ መጽሐፉ ውስጥም እንደ ቀዳሚ ሥራዎቹ፣ ከዘጠና ከመቶ በላይ በሆኑ ግጥሞቹ፣ ኢትዮጵያ በዘርፈ ብዙ መልክ ተስላለች፡፡ ገጣሚው የሀገሩ ጉዳይ ሲያስምጠው አብረን ማቃሰታችን፣ በተስፋ ውጋገን ሲመለከታት አብረን ማጮለቃችን፣ ስለ ሀገሩ በጎነት ፈጣሪውን ሲማጠን አብረን መማለዳችን . . .አይቀርም፡፡ እንደ ቀድሞው፣ ዛሬም ጭብጡ ያው ነው፡፡
ለሀገሬ፣ በሚል ትስስር፣ ለጥበብ ግኝት፣ ቢቀናጅ፣
ደጁን፣ ቢያስረግጥ ቢወዳጅ፣
በእሷ ላይ ክፉ ላሰላ . . .
በክብሯ ለመጣ አደጋ . . .
         ግንባሩን አልነፈጋትም፣
ለክብሯ፣ ያለውን ፍቅር . . .
         በሕይወት፣ አልመጠናትም፡፡
በዙፋን፣ በወርቅ-አጎበር፣
ኢትዮጵያን አልመዘናትም፡፡
ከተክለ-ማንነቷ ስሟ፣ ከታላቅ ታሪኳ ቅጥር፣
ከዓርማዋ፣ ሰንደቅ ጥላ-ሥር፣
እራሱን ከእርሷ ሸሽጎ፣ ጥሪዋን አላሳለፈም፣
እንኳንስ ክብሯን ሊያስደፍር፣ ስሟን አላዘለፈም፡፡
ክፍሌ፤ ሀገሩን በሰውኛ የዘይቤ ብልሃት ከፊት ለፊቱ አስቀምጦ ሲጠይቃት፣ ስትጠይቀው፣ ሲመርቃት ስትመርቀው፣ እውነትም እንደ በ¤ር ልጅ፣ ዓይን ለዓይን እየተያዩ፣ የእናትነትንና የልጅነትን ፍቅር የሚጎራረሱ ይመስላል፤
ዘነጋሽ-እንዴ፣ ሀገሬ፣
ረሳሽው እንዴ፣ ኢትዮጵያ፣
የጀግናሽን፣ “የእምቢኝ” ግዳይ፣
የልጅሽን ውሎ-ሙያ፣
ላስታውስሽ እንዴ፣ ትላንቱን፣
ለክብርሽ ሞቱን-ሲንቀው፣
ለሀቅሽ እልህ ሲንጠው፣
በሚል የቁጭት ቃል፣ በተለያዩ ዘመናት የተነሱትን የሀገራችንን ብርቅዬ መሪዎችና ጀግኖች ልጆቿን በምስል አስደግፎ፣ እየዘረዘረ ታሪክን በታሪክ ያጣቅሳል፡፡ የክፍሌ የሀገር ፍቅር ትኩሳት፣ ስለ ሀገር በገጠማቸው ግጥሞች ብቻ ሳይሆን በሚያነሳሳቸው ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ውስጥ እንኳ ሳይቀር ጥቂት ስንኞችን እንደ ማጣፈጫ ጨው፣ ስለ ሀገሩ ጥቂት ሃሳብ ጣል ማድረጉ አልቀረም፡፡   
“መቼ-ፈራን” የሚለው የገጣሚው መሰናበቻ አጭር ግጥም፣ ኢትዮጵያዊነት የተሸመነባቸውን ብዙ ዕሴቶች ባካተተ የሃሳብ ስብ፣ እንደምን እንዳደለባቸው ለማሳየት፣ እነሆ ፍቅር የረበበት የነፍስ ጩኸቱ፡-
ሁሉን መቻል፣ በጌታ-ዕምነት . .  .
     ዝምታችን በወርቅነት . . .
      ቋንቋ ሆኖ፣ ካላግባባን፤
ሰብዓዊነት-ካላባባን፣
የሀገር-አፈር፣ ምንጭ-ውሃችን፣
      ከ“ዱር” ዕድፍ-ካላጠራን፣
በ“እስቲ-ይሁን፣ ከእኛ ይቅር”
ሠላም ፍቅር ካላደራን!
የዘራነው-ካላፈራ፣ ትዕግስታችን-ካላኮራን!
“ትቶ” ማደር ካላስተወ . . .
“ንቆ” ማለፍ ካላዳነ . . .
በዱር፣ ዕብሪት-ከተገራን
በ“ጎጥ” መንፈስ-ከተጠራን፣
“ገድሎ” መኖር፣ መቼ ፈራን
ገጣሚ ክፍሌ አቦቸር ይህ ነው፣ ይህም ነበር። በተለይም የዛሬዎቹ በርካታ ሀገራዊ ጉዳዮቻችን በሚያባንኑንና በጎ ዕሴቶቻችን ሊዝጉ በወየቡበት በዚህ ወቅት፣እኒህን በመሳሰሉ አነቃቂ የጋራ ሀገራዊ ጉዳዮቻችን ዙሪያ ሥራዬ ብለን፣ ብዕሮቻችን እንዲያምጡ ግድ ልንል ይገባል ባይ ነኝ፡፡ በደረቅ የፕሮፓጋንዳ ኮቾሮ ሳይሆን በጥበብና በፍቅር ቅመም በማዋዛት፡፡ ሀገርም ስለ ራሷ፣ ትውልድም ስለ ራሱ መስማት የሚገባቸውን ጉዳዮች ሁሉ በግልፅነት ከጥበብ ማዕድ የየድርሻቸውን እንዲያነሱ፣ እንደ ገጣሚ ክፍሌ አቦቸር፣ ስሜታችንን ልንጨምቅ፣ ብዕራችንም ከሀገራዊ ዕውነታ እንዳይፋታ ማጠየቁ ግዴታ ሳይሆን ይቀራል? ይህ የቆምንበት ዘመን ለሀገር ክብር፣ ለወገን ኩራት፣ ለእናት ዓለም ደስታ፣ ለትውልድ እርካታ በቅንነትና በትጋት እጅ ለእጅ ተያይዘንና ተግተን ከመሥራትና ከመደጋገፍ ይልቅ የሕይወታችን ሰባቱ ዋነኛ መርሆዎች፡- “ሀ ራስህን አድን!”፣ “ሁ ከራስ በላይ ነፋስ!”፣ “ሂ ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ!”፣ “ሃ ሲሾም ያልበላ . . .!”፣ “ሄ ቀድሞ መገኘት”፣ “ህ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል .. .!”፣ “ሆ ማን ምን ያመጣል!” የሚል የነፍስና የሥጋ ጩኸት ብቻ ከሆነ፣ ታሪክም፣ ሰንሰለቱ ሊቋረጥ የማይችለው የትውልድ ሰልፈኛም መታዘቡና መፋረዱ አይቀርም፡፡ ቸር እንሰንብት!

Read 4093 times