Saturday, 26 August 2017 00:00

ለውጪ አገር ህክምና የሚጠየቀው ክፍያ የተጋነነ ነው ተባለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

   ለውጪ አገር ህክምና እየተባለ በተለያዩ መንገዶች የሚጠየቀው የክፍያ መጠን በእጅጉ የተጋነነ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን ህሙማን ተመጣጣኝ በሆነ ክፍያ ጥራት ያለው ህክምና ሊያገኙ የሚችሉበት መንገድ እንዳለ ተገለፀ፡፡
የ“ጌትዌል ሚዲካል ትራቭል” (የህክምና ጉዞ) ሥራ አስኪያጅ ዶክተር በጋሻው ባይለየን ሰሞኑን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ በተለያዩ ህመሞች ተይዘው በውጪ አገር ህክምና ማግኘት የሚገባቸው ህሙማን፣ ህክምናውን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት የሚችሉበት መንገድ ስላለ፣ ለውጭ አገር ህክምና እየተባለ በሚነገር የተጋነነ ክፍያ ምክንያት በፍራቻ ህክምናውን ሳያገኙ መቅረት አይገባቸውም ብለዋል፡፡  
በኢትዮጵያ ውስጥ ህክምናው በማይሰጥ ህመሞች ለተያዙና ከፍተኛ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ህሙማን፣ ድርጅታቸው፤ ሙያዊ የምክር አገልግሎት እንደሚሰጥና አለም አቀፍ ደረጃቸውን በጠበቁ ሆስፒታሎች ህክምና የሚያገኙበትን ሁኔታ እንደሚያመቻችም ገልፀዋል፡፡ ለህሙማን ተገቢውን ህክምና ተመጣጣኝ በሆነ ክፍያ የሚያገኙበት አገልግሎት ሲሰጥ እንደቆየ የጠቆሙት ዶ/ር በጋሻው፤ እስከ አሁን ድረስም ተቋሙ ከሁለት ሺህ በላይ ለሆኑ ህሙማን አገልግሎት መስጠቱን ተናግረዋል።
“ጌትዌል ሜዲካል ትራቭል” በአምስት የዓለማችን አገራት ውስጥ በሚገኙ 13 አለም አቀፍ ደረጃቸውን ከጠበቁ ሆስፒታሎች ጋር ባለው የሥራ ግንኙነት፣ ህሙማን በየሆስፒታሎቹ ተገቢውን ህክምና ለማግኘት እንዲችሉ በማድረግ፣ ክህመማቸው ተፈውሰው፣ ሰላማዊ ኑሮአቸውን ለመቀጠል እንዲችሉ ያግዛል ተብሏል፡፡
ድርጅቱ ለካንሰር፣ ለልብና ሳንባ ቀዶ ህክምና፣ ለነርቭ፣ ለአጥንት መገጣጠሚያ ችግሮች እንዲሁም መውለድ ለተሣናቸው ጥንዶች የሚሰጡ ህክምናዎችን ጨምሮ የውስጥ አካል (ኩላሊት፣ ጉበትና መቅኔ) የማስቀየር ህክምናዎችን በአለም አቀፍ ደረጃ፣ ከፍተኛ ዕውቅና ባላቸው ሆስፒታሎች፣ ታማሚዎችን በመላክ፣ ያለምንም ውጣ ውረድ የሚሹትን ህክምና እንዲያገኙ ያደርጋል ብለዋል-ዶ/ር በጋሻው፡፡


Read 1804 times Last modified on Saturday, 26 August 2017 11:46