Saturday, 22 July 2017 15:19

ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ከአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ጋር ተወያዩ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

     የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ሠሞኑን ከ150 የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ጋር በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ የተወያዩ ሲሆን አዲሱ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደርም ኢትዮጵያ በተለይ ሽብርን በመከላከል የአሜሪካ ስትራቴጂካዊ አጋር ሆኖ እንደምትቀጥል  ከአስተዳደሩ ማረጋገጫ መስጠቱን የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
በኢትዮጵያና በአሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለኮንግረሱ አባላት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን ማብራራታቸውን የጠቆሙት ቃል አቀባዩ፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፣ በጉዲፈቻ፣ በኢትዮጵያ በተከሠተው ድርቅና የተረጅዎች ሁኔታ ላይ ጥያቄ ቀርቦ ማብራሪያ ተሠጥቷል ብለዋል፡፡
ከኮንግረስ አባላቱ ‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መች ይነሣል?›› በሚል ለቀረበው ጥያቄ፤ በአሁን ወቅት ሃገሪቱ የተሻለ ሁኔታ ላይ መሆኗን በመግለፅ፤ በቅርቡ አዋጁ ላይ ውሣኔ እንደሚሰጥ ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል፡፡
ከድርቅና ተረጅዎች ጋር ተያይዞ ለተነሳው ጥያቄ፤ መንግስት በራሱ አቅም የሠው ህይወት ሣይጠፋ መቀልበስ መቻሉን ጠቁመው የውጭ ጉዲፈቻ መከልከሉን በተመለከተ በሰጡት ምላሽ መንግስት በቅድሚያ የሃገር ውስጥ ጉዲፈቻን ለማጠናከር በመወሠኑ የውጭ ጉዲፈቻ መከልከሉን አስረድተዋል፡፡ በ2008  በአገሪቱ ተከስቶ የነበረውን ተቃውሞና ግጭት አስመልክቶ ከኮንግረስ አባላቱ የቀረበ ጥያቄ መኖሩን  የተጠየቁት ቃል አቀባዩ በስብሰባው ላይ የቀረበ ጥያቄ የለም ብለዋል፡፡
ዶ/ር ወርቅነህ ከኮንግረስ አባላቱ በተጨማሪ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆክስ ቲለርሰንና ሴኔቱ የውጭ ግንኙነት ሃላፊ ቦብ ክሮገር ጋር ሠፊ ውይይት ያደረጉ ሲሆን ‹‹ኢትዮጵያ በጣም ታስፈልገናለች፤ የአሜሪካ ስትራቴጂካዊ አጋር ናት›› ማለታቸውን አቶ መለስ ለአዲስ አድማስ አብራርተዋል፡፡

Read 4304 times