Sunday, 25 June 2017 00:00

በጠ/ሚ ኃይለማርያም ተማፅኖ በኩዌት የታሰሩ ኢትዮጵያውያን ምህረት ተደረገላቸው ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

    ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በኩዌት በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ምህረት እንዲደረግላቸው ለሀገሪቱ መንግስት በፃፉት የተማፅኖ ደብዳቤ መሰረት ለታሳሪዎች ምህረት መደረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ለአዲስ አድማስ አስታውቋል፡፡
በኩዌት እስር ቤቶች በርካታ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ምክንያቶች ታስረው እንደሚገኙ የጠቆሙት ቃል አቀባዩ አቶ መለስ አለም፤ መንግስት ለጉዳዩ ከወትሮው የላቀ ትኩረት በመስጠት ባደረገው እንቅስቃሴ የሀገሪቱ መንግስት ለታሳሪዎች ምህረት ማድረጉን አስረድተዋል፡፡ ይሁንና ምህረት የተደረገላቸው ዜጎች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ እስካሁን በውል የታወቀ ነገር የሌለ  ሲሆን ከእስር ሲፈቱ የሚታወቅ ይሆናል ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡
ለኢትዮጵያዊያኑ እስረኞች የተደረገውን ምህረት ተከትሎም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ  ዶ/ር ወርቅነህ ገበየው ለኩዌት መንግስት ምስጋና ማቅረባቸው ተጠቁሟል፡፡
በተመሳሳይ በሳኡዲ አረቢያ የተለያዩ እስር ቤቶች ከሚገኙ ከ200 በላይ ኢትዮጵያውን እስረኞች መካከል 87 ያህሉን በድርድር ማስለቀቁን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፃፉት የተማፅኖ ደብዳቤ በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ጥሰዋል ተብለው በዛምቢያና ታንዛኒያ ታስረው የነበሩ 600 ያህል ኢትዮጵያውያን እንዲፈቱ መደረጉም ተመልክቷል፡፡  

Read 4985 times