Monday, 19 June 2017 10:19

“ግሪን ላይት አውቶሜካኒክ” የስልጠና ማዕከል ተመረቀ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ከአንድ አመት በፊት በቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ፤ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለትና በቅርቡ ግንባታው የተጠናቀቀው ‹‹ግሪን ላይት አውቶሜካኒክ” የስልጠና ማዕከል ረቡዕ ረፋድ ላይ በይፋ ተመረቀ፡፡ በኪያ ሞተርስና በኮሪያን ኢንተርናሽናል ኮኦፕሬቲቭ ኤጀንሲ (KOICA) ወጪው ተሸፍኖ፣ በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የተገነባው ይሄው ማዕከል፤ ባለ 4 ወለል ህንፃ ሲሆን ኢትዮጵያዊያንን ወጣቶች በአውቶሜካኒክ ስልጠና ወስደው ባለሙያ የሚሆኑበት ነው ተብሏል፡፡
ህንፃው ለአውቶ ሜካኔክና ለእጅ ስራ ሙያ ስልጠና የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ያሟላ ሲሆን በቀጣይም በተጨማሪ ቁሳቁሶች ተደራጅቶ በአጠቃላይ ለ615 ወጣት ወንዶችና ሴቶች ስልጠና ይዘጋጃል ተብሏል፡፡ በቀጣዩ ግንቦት ስልጠና መስጠት ይጀምራል የተባለው ማዕከሉ፤ የህንፃውን ግንባታ ጨምሮ ለአምስት ዓመት የሚቆይ ፕሮጀክት ሲሆን 220 ወጣቶችን በአውቶ ሜካኒክ፣ 395ቱን ደግሞ በእጅ ስራ ሙያ አሰልጥኖ፣ ራሳቸውን እንዲችሉ የማድረግ እቅድ ይዟል፡፡ ማዕከሉ የራሱ የአስተዳደር ቁመናና ስርዓተ ትምህርት እየተቀረፀለት እንደሆነም ተገልጿል፡፡
ስድስት የመማሪያ ክፍሎች፣ ሶስት ወርክሾፖች፣ አምስት ቢሮዎች፣ አምስት የእቃ ማከማቻ ክፍሎች፣ ሁለት የመምህራን ቢሮዎች፣ አንድ የICT ክፍል፣ አንድ ቤተ መፅሀፍት፣ አንድ ጋራዥና አንድ ላውንጅ አሟልቶ የያዘም ነው ተብሏል ህንፃው፡፡ በዚህ ማዕከል በአውቶ ሞቲቭ ኢንጂን በሌቭል 1 እና በሌቭል 2 በፓወር ትሬይንም እንዲሁ በሌቭል 1እና ሁለት ስልጠና የሚሰጠው ማዕከሉ በቀጣዩ ግንቦት በሁለት ዙር ስልጠና ለመስጠት ሰልጣኞችን መመዝገቡን አስታውቋል፡፡
በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የወርልድ ቪዥን ካንትሪ ዳይሬክተር ኤድዋርድ ብራውን ባደረጉት ንግግር፤ “ካንትሪ ዳይሬክተር ሆኜ ከተሾምኩ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የጎበኘሁት ትልቅ ፕሮጀክት በመሆኑ ለእኔ ትልቅ በዓል ነው” ብለዋል። ሌላው በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ በእንግድነት የተገኙት የአዲስ አበባ ቴክኒክ፣ ሙያና ትምህርት ስልጠና ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ ዘሩ ስሙር፤ ኮሪያና ኢትዮጵያ ባላቸው ታሪካዊ ግንኙነት በእጅጉ ኢትዮጵያን እየደገፉ መሆኑን ጠቁመው መንግስት በቴክኒክና ስልጠና በርካቶችን ተጠቃሚ እያደረገ ቢሆንም ሁሉንም ስለማያዳርስ እንዲህ አይነት ድርጅቶች የሚያደርጉት ድጋፍ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡ የኮሪያ አምባሳደር በኢትዮጵያ ሚስተር ሙን ሁዋን ኪም ኢትዮጵያ ለኮሪያ ባለውለታ በመሆኗ ይህን ውለታ ለመመለስ ብዙ ምክንያቶችን እንፈልጋለን፤ ይሄም ፕሮጀክት ውለታ ለመመለስ አንዱ መንገድ ነው ብለዋል፡፡ ማዕከሉ ለሚያከናውነው የ5 ዓመት ፕሮጀክት፤ የ2.5 ሚ ዶላር (57.8) በጀት ተይዞለታል ተብሏል፡፡

Read 1868 times