Sunday, 11 June 2017 00:00

በመንግሥት አካላት ላይ ስለተወሰዱ ርምጃዎች ሪፖርት ይቀርባል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

  በ68 ማረሚያ ቤቶችና 61 ፖሊስ ጣቢያዎች የእስረኞች አያያዝን በተመለከተ ምርመራ አድርጌአለሁ ብሏል
       
      የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፤ በግጭቶች ላይ ያቀረባቸው ሪፖርቶችን መሰረት በማድረግ፣ የመብት ጥሰት በፈፀሙ የመንግስት አካላት ላይ የተወሰደን እርምጃ በተመለከተ  በቅርቡ ለፓርላማው ሪፖርት እንደሚያቀርብ የገለጸ ሲሆን በተመረጡ ማረሚያ ቤቶችና ፖሊስ ጣቢያዎች፣ የእስረኞች አያያዝን በተመለከተ ምርመራ ማድረጉንም አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ ተቃውሞና ግጭቶችን በተመለከተ ለሁለት ጊዜያት ያደረጋቸውን የምርመራ ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ባቀረበበት ወቅት “በደል ፈፅመዋል” የተባሉ አካላት የተወሰደባቸውን እርምጃ ተከታትዬ ሪፖርት አቀርባለሁ ማለቱ የሚታወስ ሲሆን በዚህም መሰረት የእርምጃ አወሳሰድ ሪፖርቱን አዘጋጅቶ ማጠናቀቁን ጠቁሞ፣ በ15 ቀናት ውስጥ ለም/ቤቱ ሪፖርቱን እንደሚያቀርብ የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ አባዲ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡
ፓርላማው “በደል ፈፅመዋል፤ተጠያቂ ይሁኑ” ባላቸው አካላት ላይ የተወሰደን የህግ እርምጃ ለመመርመር፣ ኮሚሽኑ፣ ዘጠኝ ቡድኖችን  ወደ ኦሮሚያ፣ አማራና ደቡብ ክልል፡- ኮንሶና ጌዴኦ ዞኖች ልኮ፣ ምርመራውን ሲያከናውን እንደነበር የጠቆሙት አቶ ብርሃኑ፤ ምርመራው ተጠናቆ በግኝቱ ላይ በዛሬው ዕለት ከየክልሎቹ አመራሮች ጋር ውይይት ይደረግበታል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የቅማንት ማህበረሰብ ጉዳይ በህገ መንግስቱ መሰረት መፍትሄ እንዲሰጠው የተላለፈው የውሳኔ ሃሳብ ስለ መፈፀም አለመፈፀሙ፣ ለህዝብ ብሶትና ተቃውሞ ምክንያት የሆኑ ችግሮች ስለመቀረፋቸው፣ የስራ አጥነት ጥያቄዎች ስለመመለስ አለመመለሳቸው ሪፖርቱ እንደሚያካትት አቶ ብርሃኑ ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል ኮሚሽኑ ከወትሮው በተለየ በሀገሪቱ ከሚገኙ 114 ማረሚያ ቤቶች መካከል በተመረጡ 68 ማረሚያ ቤቶችና 61 ፖሊስ ጣቢያዎች ያለውን የእስረኞች አያያዝ በተመለከተ ምርመራ ማድረጉንና ይህም ሪፖርት አብሮ ለፓርላማው እንደሚቀርብ ኃላፊው ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል። የታራሚዎች መብት አጠባበቅን በተመለከተ የተደረገው ምርመራ፤ የተባበሩት መንግስታት ባስቀመጠው መስፈርቶች መሰረት መሆኑን ያስረዱት ኃላፊው፤ ይህም ቅሬታ የሚቀርብባቸውን የማረሚያ ቤቶችና የፖሊስ ጣቢያዎች አሰራር ለማሻሻል እንደሚጠቅም ተናግረዋል፡፡  
በፖሊስ ጣቢያዎች ተጠርጣሪዎች በፍ/ቤት ትዕዛዝ ስለመያዛቸው፣ ምርመራ ሲደረግባቸው ሰብአዊ መብታቸው መጠበቁንና ያለ ኃይልና አስገዳጅነት መመርመራቸውን እንዲሁም ሌሎች የሰብአዊ መብት ጉዳዮች በምርመራው መካተታቸውን አቶ ብርሃኑ አስታውቀዋል፡፡ 

Read 4204 times