Sunday, 04 June 2017 00:00

በፌዴራል ሥርዓቱ ውይይት ላይ ያልተነሱ ችግሮች

Written by  አበራ ገብሩ (የሰማያዊ ፓርቲ አባል)
Rate this item
(1 Vote)

   “እንዴት 26 አመት ሙሉ ጀማሪ ነን ይባላል?!”
                      
       ይህን ጽሁፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ግንቦት 18 ቀን 2009 ዓ.ም በሂልተን ሆቴል በተዘጋጀው በፌዴራል ሥርዓት ግንባታ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ላይ ፓርቲዬን ወክዬ ተገኝቼ ስለነበርና በዕለቱ የፓርቲዬን አቋምና የራሴን ሐሳብ እንዲሁም በውይይቱ የታዘብኩትን ለመግለጽ ፍላጎት የነበረኝ ቢሆንም የመናገር ዕድል ባለማግኘቴ ነው፡፡
ወደ ዋናው ጉዳይ ከመግባቴ በፊት አንድ ትዝብቴን ማስቀመጥ እፈልጋለሁ፡፡ ይኸውም አንድ ተሳታፊ ከኦብኮ ይመስለኛል የተጠቀሙበትን ቃላት የሚመለከት ነው፡፡ በመሠረቱ እንደዚህ ዓይነት የውይይት መድረክ ሲዘጋጅ ሐሳብ ለመለዋወጥ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡
ማንኛውም ተሳታፊ የመሰለውን ሐሳብ ይዞ መቅረብ ይችላል። ሀሳቡ አሳማኝ መሆኑና አለመሆኑ፣ ተቀባይነት ማግኘቱና አለማግኘቱ በውይይቱ ላይ የሚታይ ነው፡፡ “በፌዴሬሽን መዋቀሩን አልፈልግም” ማለትም እኮ መብት ነው፡፡ በውይይት መድረኮች የትኛውንም ሐሳብ መሰንዘር ይቻላል፡፡ ምናልባት ይህን እውነታ ያልተረዳ ተሳታፊ  ሳይሆን አይቀርም፤ ተወደደም ተጠላ ፌዴሬሽን የግድ መሆኑን ነግሮናል፡፡ ተወደደም ተጠላ የሚለው አባባል ለውይይት ቀና አነጋገር ስላልመሰለኝ እንዲታረም ላሳስብ እወዳለሁ።
በመጀመሪያ የፓርቲያችንን አቋም ልግለጽ። ፌዴራላዊ ሥርዓት ሥልጣኑ ሁሉ  በማዕከላዊ መንግሥቱ ሥር እንዳይሆን ሥልጣንን መከፋፈል ስለሆነ ሰማያዊ ፓርቲ የሚደግፈው ጉዳይ ነው። በፕሮግራሙ ላይም የመንግስት አወቃቀር በፌዴራላዊ ሥርኣት እንደሚሆን ይገልጻል። ከዚህም በላይ የፌዴራል መንግስት አወቃቀር መልክዐምድራዊ አቀማመጥን፣ የሕዝብ አሰፋፈርን፣ ለልማትና አስተዳደር አመቺነትን፣ ቋንቋንና ባህልን፣ ታሪክን፣ የሕዝብ ፍላጎትን፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስሮችንና የመሳሰሉትን ሁሉ ከግምት ውስጥ የሚያስገባ መሆን እንዳለበት ይገልጻል። እንግዲህ ከኢህአዴግ ጋር ልዩነታችን፤ ኢህአዴግ ሀገሪቱን በፌዴራል ስርዓት ለመከፋፈል የተጠቀመው ቋንቋን ወይም ብሔርን ብቻ መሠረት ያደረገ መሆኑ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የኢህአዴግ ሰዎች በእውነት ላይ ተመርኩዘው መከራከር ሲያቅታቸው እንደሚሉት፤ “እኛ ፌዴራል ሥርዓትን ሳይሆን የምንቃወመው ኢህአዴግ የተከተለውን መንገድ ነው፡፡” ስለዚህ ፓርቲያችን የሚለው፤ የፌዴራል ሥርዓቱ ከላይ የተገለጹትን እጅግ በጣም አስፈላጊ ጉዳዮች ሁሉ ከግምት ባስገባ መንገድ መዋቀር አለበት ነው፡፡
በዕለቱ ጥናቱን ያቀረቡት ምሁራን ብዙ ጉዳዮችን ያነሱ ቢሆንም ጽሁፋቸውን ባቀረቡበት ርእስ ማለትም “የፌዴራል ሥርዓታችን ብዝኃነትና የጋራ ተጠቃሚነት የማስተናገድ አቅም” በሚለው ሥር ብዙ ሊነሱ የሚገባቸው አንኳር ነጥቦች አልተነሱም ወይም አልካተቱም፡፡ በእኔ እምነት ከዚህ በታች የተጠቀሱት ነጥቦች ሊነሱ ይገባቸው ነበር፡፡  
ምን ዓይነት የፌዴራል ሥርዓት ነው እየተጠቀምን ያለው? ምን አስገኘልን? ምንስ አሳጣን?
የፌዴራል ሥርዓቱ ካመጣው ውጤት አንጻር ተመዝኖ (ያስገኘውና ያመጣው ችግር ተነጻጽሮ) መቀጠል አለበት ወይስ የለበትም የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስ፡፡
ሌሎች አማራጭ የፌዴራል ሥርዓት አሠራሮችና ጥቅምና ጉዳት፡፡     
በአሁኑ ሰአት በሀገራችን ያፈጠጡ ያገጠጡ፣ በምንከተለው የፌዴራል ሥርአት የተነሳ የተፈጠሩ ችግሮችን መቃኘት፡፡ የመፍትሔ ሐሳቦችና አማራጮች ማቅረብ፡፡  
ለምሳሌ በጥናቱ ያልተካተቱ ያፈጠጡና በገሃድ የሚታዩት ችግሮች መካከል ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ይጠቀሳሉ፡-
በክልሎች ድንበር ላይ በየጊዜው የሚፈጠረውና እየተፈጠረ ያለው ግጭት፣
ዜጎች ያለፍላጎታቸው የዚህኛው ወይም የዚያኛው ብሔር ናችሁ መባላቸው፣
ጥቂት ቁጥር ያላቸው ብሔር ብሔረሰቦች፣ ክልል ተብለው በራሳቸው እንዲተዳደሩ ሲፈቀድላቸው፣ በቁጥር ከእነዚህ በብዙ የሚበልጡ ሌሎች ይህን እድል መነፈጋቸው (አሠራሩ ለሁሉም ተመሳሳይ መሆን ሲገባው አልሆነም)፡፡
ሀገራዊ ስሜት መሸርሸሩ፣
ዜጎች በሀገሪቱ ውስጥ በየትኛውም ቦታ እንደ ዜጋ መሥራት እንዳይችሉ ወይም ከቦታ ቦታ በነጻነት እንዳይንቀሳቀሱ ማድረጉ፣
በአንዳንድ አካባቢዎች ዜጎች በጥረታቸው ያፈሩትን ንብረት ተቀምተውና ተነጥቀው ውጡ መባላቸው፣
ዜጎች መንግሥታዊ አገልግሎት ለማግኘት ብዙ ርቀት እንዲጓዙ የሚያስገድድ ሁኔታ መፈጠሩ፡፡ ለምሳሌ የምንጃርና ሸንኮራ ነዋሪዎች፤ አዳማና ናዝሬትን የመሳሰሉ ከተሞችንና አስተዳደሮችን እያለፉ፣ባህር ዳር ድረስ እንዲጓዙ መገደዳቸው እንዲሁም   የቤንች ማጅ ዞን ነዋሪዎች፤ ጅማ በቅርባቸው እያለ አዋሳ እንዲጓዙ መገደዳቸው፡፡
በአንድ ዩኒቨርሲቲ የሚማሩ ተማሪዎች፤ የአንድ ሀገር ልጅ እስከማይመስሉ ድረስ ተነጋግረው መግባባት አለመቻላቸው ማለትም በቋንቋ ችግር አለመግባባታቸው።
በቋንቋ የተነሣ የፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ችግር መፈጠሩና ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ዜጎች በቋንቋ ችግር ሳቢያ የሥራ እድል ማጣታቸውና ሌሎች ብዙ ችግሮች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡
በዚህ የተነሳ የፌዴራል ሥርአታችን የጋራ ተጠቃሚነትን የማስተናገድ አቅም የለውም፤ ብዝሃነትንም ያስተናግዳል ማለት አይቻልም። ስለዚህ የፌዴራል ሥርዓቱ ፈተናውን የወደቀ ሥርዓት ነው፡፡
በዚህ ውይይት ላይ የተሳተፉ የኢህአዴግ ቱባ ባለሥልጣናት ሐሳባቸውን አንፀባርቀዋል፡፡ ብዙ የተነገሩ ጉዳዮች ቢኖሩም ጥቂቶቹ ላይ ብቻ አተኩራለሁ፡፡
የመጀመሪያው ተናጋሪ አቶ አባይ ፀሐይ፤ የፌዴራል ሥርዓቱን በብሔር መከፋፈሉን ትተን፣ በመልክዐ ምድር ብንከፋፍለው፣ ወደ ቀድሞው ሥርአት መመለሳችን ነው ብለዋል፡፡ አቶ አባይ፤ ይህን ሲሉ ይህ ሥርአት ከቀድሞው የሚለየው ሀገሪቱን ቋንቋን ወይም ብሔርን መሠረት አድርጎ በመከፋፈሉ ብቻ ነው ማለታቸው እንደሆነ የተዱት አይመስሉም። ነገር ግን ባለፈው ሥርአት ሀገሪቱ በክፍለ ሀገሮች መከፋፈሏ ብቻ ሳይሆን ዋናውና ትልቁ ልዩነት አሀዳዊ ሥርአት መሆኑ ነው፡፡
ይህም ማለት የክፍለ ሀገር አስተዳዳሪዎች በማእከላዊ መንግስት የሚሾሙ፣ የማእከላዊ መንግስቱን ፍላጎትና ትእዛዝ የሚያስፈጽሙ እንጂ ለይስሙላም ቢሆን በህዝብ የሚመረጡ አይደሉም። በአጠቃላይ ሥልጣኑ ሙሉ በሙሉ በማእከላዊ መንግስት የተያዘ በመሆኑ ፌዴራላዊ ሥርአት አልነበረም፡፡ ስለዚህ ይህ የአቶ አባይ አባባል ውሃ የሚቋጥር አይደለም፡፡
ሌላው ስለ አውራ ፓርቲ ሲናገሩ፤ የእነሱ ምኞት ጠንካራ ተሳታፊና ተፎካካሪ ፓርቲ እንዲኖር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይህማ ቀላል አይደለም እንዴ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አለመኮርኮምና አለማሳደድ ብቻ ይበቃል እኮ፤ ሌላ ከእናንተ የሚጠበቅ ነገር የለም፡፡
በመቀጠል የተናገሩት አቶ ስብሐት ነጋ፤ ኢህአዴግ ሀገሪቱን ሲቆጣጠር ለኢህአፓ፣ ለመኢሶንና ለኢሠፓ “ሀገሪቱን ከመበታተን እናድናት” ብለው ጥሪ አድርገውላቸው እንደነበርና ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ገልጸዋል፡፡ ኢህአዴግ ሀገሪቱን የተቆጣጠረበት ጊዜ እኮ ቅርብ ነው፤ ሩቅ አይደለም። ስለዚህ በጊዜው የነበረውን እውነት ብዙ ሰው የሚያውቀው ይመስለኛል፡፡
ኢሰፓ መጀመሪያውኑ ፕሮግራም ኖሮት፣ አባላት በፕሮግራሙና በአላማው ተማርከውና አምነውበት የገቡበት ድርጅት ባለመሆኑ ሥልጣን ሲያጡ ወይም ችግር ሲመጣ ችግሩን ተቋቁመው አብረውት ሊቆዩና መስዋእትነት ሊከፍሉ የሚችሉ አባላት የነበሩት አይመስለኝም። ለዚህም ነው ከዚያ በኋላ በፍጹም ስለ ፓርቲው የሚሰማ ነገር የሌለው፡፡ ኢህአፓና መኢሶንን በሚመለከት ግን “ትጥቅ ያነሱ ድርጅቶች ናቸው” ተብለው እንደተገፉና እንኳንስ ሊጋበዙ እንዳይመጡ በር እንደተዘጋባቸው እየታወቀ፣ ለምን እንዲህ ለማለት እንደተፈለገ ግልጽ አይደለም፡፡
አቶ ተፈራ ደርበው የተባሉ የኢህአዴግ አመራር፤“ፓርቲዎች ቢዝነስ ውስጥ መግባት የለባቸውም” በሚል ከተሳታፊ ለቀረበው ሐሳብ በሰጡት ምላሽ፤ “ቢዝነስ ውስጥ የገባ ፓርቲ የለም፤ ቢኖርም በህግ ይጠየቃል” አሉ፡፡ ቢሆንማ ጥሩ ነበር፤ በእስር ቤትና በውጭ ያሉት ቦታ ሊለዋወጡ ይችሉ ነበር፡፡
ሌላዋ ስማቸውን የማላስታውሰው ሴት ተሳታፊ፤ ”ዜጎች ከየክልሉ ውጡ እየተባሉ ይባረራሉ” በሚል ለተነሳው አስተያየት አስገራሚ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ህዝባችን እንግዳ ተቀባይ መሆኑን ይገልጹና ነገር ግን ይህን እንዲያደርግ የሚገፋፋው፣ በል በል የሚለውና ለጥፋት የሚያበረታታው አካል አለ ብለዋል፡፡
ውድ የኢህአዴግ ባለሥልጣን፤ በመጀመሪያ እነዚህ ከመኖሪያ ቀያቸው የተባረሩ ወገኖች እንግዳ አይደሉም፡፡ ሀገራቸው ውስጥ ነው የነበሩት፤ ይህ የሥርአቱ ችግር ነው፤ እነዚህ ሰዎች አብዛኞቹ እዚያው ተወልደው አድገው፤ እነሱም በተራቸው ልጅ ወልደው አሳድገው ድረው ኩለው፤ ሀብት አፍርተው፣ ለዘመናት የኖሩበት ነው። እንግዶች አይደሉም፤ እናንተ ናችሁ እንግዶች ያደረጋችኋቸው፤ እንጂ ከሀገሬው ጋርማ ለዘመናት አብረው ኖረዋል፡፡ ኧረ ለመሆኑ ይህን ያህል ጊዜ አብረው ሲኖሩ፣ አብረው ሲሰሩና በጋብቻ ሲተሳሰሩ እንዲያባርሯቸው ያልገፋፋ አካል አሁን በኢህአዴግ ጊዜ ከየት መጥቶ ነው የሚገፋፋው? ይህ አካልስ ማነው? በማን ተፈጠረ? ተጠያቂውስ ማነው? ለምንስ ነበር የማይጠየቀው? ተጎጂዎቹ ለምን ጠያቂ ወገን አጡ? የሚሉት  ጥያቄዎች መልስ ይሻሉ፡፡
 በውይይቱ ላይ መገንዘብ የተቻለው፤ የኢህአዴግ ባለሥልጣናት አሁንም ለለውጥ ዝግጁ እንዳልሆኑ ነው፡፡ አሁንም “የፌዴራል ሥርአቱ ጀማሪ ነው” እያሉን ነው፡፡ እንዴት 26 አመት ሙሉ ጀማሪ ነን ይባላል?! እንዴት 26 አመት ሙሉ የአፈጻጸም ችግር ነው የሚል ሰበብ ይሰጣል?!
በመጨረሻም ውይይቱን ያዘጋጁትን ሁለት የሚዲያ ተቋማትና ጽሁፉን ያቀረቡትን ምሁራን በእጅጉ እያመሰገንኩ ወደፊትም ተመሳሳይ የውይይት መድረኮች ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ላሳስብ እወዳለሁ፡፡ በተለይ ምሁራን በሀገራቸው የፖለቲካ ጉዳይ  ባይተዋር መሆን የለባቸውም ብዬ አምናለሁ፡፡  

Read 1845 times