Sunday, 28 May 2017 00:00

የኢትዮጵያ ፋሽን ሳምንት በቅርቡ ይካሄዳል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

 በሚቀጥለው ዓመት የአፍሪካ ዲዛይነሮችና ሞዴሎች ጭምር ይሳተፋሉ

     ባደጉ አገሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ‹‹የፋሽን ሳምንት›› በሚል ርዕስ የፋሽን ትርዒትን ጨምሮ ኤግዚቢሽንና ባዛር ይካሄዳል፡፡ ለአብት፣ የኒውዮርክ-አሜሪካ፣ የፓረስ-ፈረንሳይ፣ የሚላን- ኢጣሊያ፣ የቶኪዮ- ጃፓን፣…. የፋሽን ሳምንት መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ ባዛርና ኤግዚቢሽኖች ለአገር ኢኮኖሚ ማደግና መበልፀግ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡
በፋሽን አንዲስትሪው የተሰማሩ ዲዛይነሮች፣ አርቲስቶች፣… ምርቶቻቸውን ይዘው ባዛርና ኤግዚቢሽኑ ወደሚካሄድበት አገር ይጓዛሉ፡፡ ‹‹በኤግዚቢሽኑ ላይ ምን ዓይነት አዲስ ዲዛይናና ፋሽን ቀረበ›› በማለት ለማየት፣ ለማድነቅ አዳዲስ ምርቶችን ለመግዛት የሚሄዱ ሰዎችና ቱሪስቶች፣… ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ሁሉ ሆቴል ይይዛሉ፣ ምግብ ይመገባሉ፣ ውሃ (መጠጥ) ይጠጣሉ፤ ከተማውን ይጎበኛሉ፤ ከባዛርና ኤግዚቢሽኑ ዕቃ ይገዛሉ፣ የልምድ ልውውጥ ያደርጋሉ፣ የገበያ ትስስር ይፈጥራሉ፣…. መስተጋብሩ ብዙ ነው፤ ተቆጥሮ አያልቅም፡፡ ሆቴል ሲያዝ፣ ምግብና መጠጥ ሲገዛ፣ ከተማው ሲጎበኝ - ለትራንስፖርት፣ ከባዛር ዕቃ ሲገዛ…. ገንዘብ ያወጣሉ፡፡ ያ ገንዘብ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ለዚህ ነው የፋሽን ኢንዱስትሪው እንደ አንድ የኢኮኖሚ ዘርፍ የሚቆጠረው፡፡
በዚህ ረገድ አገራችን ገና ናት- ብዙ መሥራት ይጠበቅባታል፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት በ2006 ዓ.ም የተመሠረተውና ‹‹ዳዴ›› እያለ የሚገኘው የፋሽን ዲዛይነር ማኅበር፤ እንደ በለፀጉት አገሮች በሳምንት ሳይሆን ከግንቦት 27 እስከ 28 ለሁለት ቀን ‹‹የኢትዮጵያ የፋሽን ሳምንት›› ለማካሄድ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ መሆኑን ማኅበሩ፣ በሳምንቱ መጀመሪያ፣ በዮዲ አቢሲኒያ ኢንተርናሽናል ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታወቋል፡፡
“የኢትዮጵያ ፋሽን ሳምንት” የሚካሄደው በታሪካዊው የምድር ባቡር ጣቢያ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ከ3 ዓመት በፊት በ11 ዲዛይነሮች  የተመሠረተው የፋሽን ዲዛይነር ማኅበር፤ በአሁኑ ወቅት 102 አባላት እንዳሉት የጠቀሱት የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ዲዛይነር እጅጋየሁ ኃ/ጊዮርጊስ፣ ዝግጅቱ የኢትዮጵያ ዲዛይነሮች ሳምንት ስለሆነ የማኅበሩ አባል ያልሆኑ ዲዛይነሮችም በትርዒት እንዲሳተፉ ተጋብዘዋል፡፡ በሁለቱ ቀን ቅዳሜና እሁድ የራሳቸው አዲስ የፈጠራ ውጤት የሆነ የቆዳና የሸማ፣ ዲዛይንና ፋሽን የሚያቀርቡ 30 ዲዛይነሮች ተመርጠዋል ብለዋል፡፡
ውበት በሰውነት ቅርፅ ብቻ አይለካም ብለን ስለምናምን፤ የእኛ ማኅበር አካል ጉዳተኞችን ያሳትፋል፡፡ ውበት በራስ መተማመንና ራስን ሆኖ መቅረብ ነው፡፡ አካል ጉዳተኞች ደግሞ በራሳቸው ይተማመናሉ ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ ከ10 ቀናት በኋላ በሚቀርበው ‹‹የኢትዮጵያ ዲዛይነሮች ሳምንት›› 8 የአካል ጉዳተኛ ሞዴሎች፣ ከጀማሪና ልምድ ካላቸው 30 ፕሮፌሽናል ሞዴሎች ጋር እኩል ትርዒት እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል፡፡
ዲዛይነር እጅጋየሁ፣ ከሸማኔዎች ጋር የጠበቀ ቁርኝት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ “ማኅበሩ ከ3 ዓመት በፊት በ11 አባላት ሲቋቋም፣ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር ነበረበት፡፡ ሜዳ (ሜኖናይት ኢኮኖሚክ ደቬሎፕመንት አሶሴሽን- (Menonight economic Development Association) የተባለ የካናዳ ድርጅት፣ ያኔ በጨርቃጨርቅ ዙርያ ከሸማኔዎች ጋር ይሠራ ስለነበር፣ ዲዛይነሮችን፣ ከሸማኔዎች ጋር በማገናኘት የገበያ ትስስር እንድንፈጥር አድርጓል፡፡”
“የፋሽን ዲዛይነሮች ለሸማ የሚሆን ጥሬ ዕቃ የምናገኘው ከሽማኔዎች ስለሆነ በጥብቅ ትስስር ነው አብረውን የምንሠራው፡፡ እንደተመሠረትን በኦሮሞ ባህል ማዕከል፣ አምና ደግሞ ከባህልና ቱሪዝም ሚ/ር ጋር በመተባበር ባቀረብነው ትርዒት፣ ሽማኔዎች እንዴት እንደሚያመርቱ፣ ምን ዓይነት ጥሬ ዕቃ እንደሚጠቀሙ፣ የምንለብሰው ሸማ የጥራት ደረጃ ምን እንደሆነ፣ እየሠሩ እንዲያሳዩ አድርገናል።” ብለዋል፡፡ ባህልና ኢንዱስትሪ ሚ/ር፣. የፋሽን ኢንዱስትሪ አድጎና ታውቆ ለአገር ኢኮኖሚ የበከሉን ድርሻ እንዲያበረክት ድጋፍ እያደረጉልን ነው፡፡ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛን ለመከላከል ከማኅበራዊ ጉዳይ ሚ/ር ጋር እየሠራን ነው፡፡ የእኛ ዲዛይነሮች የጉልበት ብዝበዛ ውጤት እንዳይጠቀሙ እየሠራን ነው፡፡ በሁለቱ ቀን፣ ከጧት 3-12 ሰዓት ኤግዚቢሽንና ባዛር፣ ማታ ደግሞ የፋሽን ትርዒት ይቀርባል በማለት አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፋሽን ሳምንት ዘንድሮ የሚካሄደው ለመጀመሪያ ጊዜ ቢሆንም በቀጣይ በየዓመቱ እንዲደረግ ተወስኗል ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ቀንና ወሩ በባዛሩ ወቅት ይገለጻል ብለዋል፡፡ በዘንድሮው ኤግዚቢሽንና ባዛር ኢትዮጵያውያን ዲዛይነሮች ቢቀርቡም ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ የአፍሪካ አህጉር ዲዛይነሮችና ሞዴሎች ጭምር እንዲሳተፉ ይደረጋል ብለዋል፤ ዲዛይነር እጅጋየሁ ኃ/ጊዮርጊስ፡፡    

Read 1698 times