Sunday, 28 May 2017 00:00

“ለኔ ሙያዬ ሰው መሆን ነው”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

    • የሰለጠነ በእውነትና በእውቀት ላይ የቆመ ፖለቲካ ያስፈልገናል
                     • ሀገር ልታድግ፣ ልትሰለጥንና ልትቀጥል የምትችለው፣በጎ ሰዎችን ስታከብር ነው

     ከ25 በላይ ሃይማኖታዊ፣ ታሪክ ነጋሪና የወጎች መፅሐፍት አሳትሟል፡ ፡ በማህበራዊ፣ ሐይማኖታዊና ሰዋዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በሚያቀርባቸው መጣጥፎችና ወጎች ይታወቃል። ለተለያዩ መጽሄቶች በአምደኝነት ይጽፍ የነበረው ዲ/ን ዳንኤል ክብረት በአሁኑ ወቅትም በአዲስ አድማስ ጋዜጣ በአምደኝነት በመጻፍ ላይ ይገኛል፡፡ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት፤ ”የበጎ ሰው ሽልማት” ፈጣሪና መስራች ሲሆን ዘንድሮ 5ኛው “የበጎ ሰው ሽልማት እንደሚካሄድ ሰሞኑን በተሰጠው
ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተነግሯል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ ከዲ/ን ዳንኤል ክብረት ጋር በ”በጎ ሰው ሽልማት” ዙሪያ፣ በሙያው፣ በፖለቲካና በአገሩ ጉዳይ ላይ አጭር ቃለምልልስ አድርጓል።

     ዘንድሮ ለ5ኛ ጊዜ “የበጎ ሰው ሽልማት” ይካሄዳል። እስከ ዛሬ የነበሩ ሽልማቶች ምን ውጤት አስገኙ?
ሶስት ዋና ዋና ነገሮች አስገኝቷል፡፡ አንደኛ፤ በዚህ ሽልማት የተሸለሙ ብዙ ሰዎች ተጨማሪ እውቅና አግኝተዋል፡፡ በተለይ ባልታዩ ዘርፎች ላይ የነበሩ ሰዎች በህዝብም፣ በመንግስትም በአለማቀፍ ተቋማትም በድጋሚ ተሸልመዋል፡፡ ለላቀ ሽልማት ሁሉ የበቁ አሉ፡፡ የተወሰኑት ከዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዶክትሬት አግኝተዋል፡፡ ይሄ አንዱ የዚህ ሽልማት አስተዋፅኦ ነው፡፡ ሁለተኛ እነዚህ ሰዎች ታሪካቸው እንዲታወቅ ሆኗል፡፡ በኛ ሀገር ልማድ እስከ ዛሬ ወይ ወደ ፖለቲካው አሊያም ወደ ኪነጥበቡ፣ ከዚያ ካለፈ የወታደር ታሪክ ነው የሚፃፈው፡፡ የነጋዴ፣ የተመራማሪና ሳይንቲስት ወይም የሌሎች ባለሙያዎች ታሪክ አይፃፍም፡፡ ስለዚህ ቢያንስ በዚህ ሽልማት የእነዚህን ሙያ ባለቤቶች ታሪክ በማሰባሰብ፣ አንድ ውጤት ላይ የሚደርስ ክምችት ሊፈጥር ችሏል፡፡ ሶስተኛው ውጤት ደግሞ ሰዎች ስለ ሽልማቱና ማን ጥሩ ሰራ የሚለውን እንዲያስቡ ሆኗል፡፡ ራሳቸውም ሊሸለሙ ይገባቸዋል ያሏቸውን ሰዎች በእጩነት ማቅረባቸው በጎ ነገር ነው፡፡
ይሄን የሽልማት መርሃ ግብር ምን ያህል ትዘልቁበታላችሁ? የማስፋፋት እቅዳችሁስ?
የኛ ሃሳብ ከዚህ አልፎ እንደ የኖቤል ሽልማቶችና ሌሎች ታላላቅ ሽልማቶች በአለም ላይ ታዋቂ የሆነ ኢትዮጵያዊ የሽልማቶች ድርጅት እንዲኖር ነው የምናስበው፡፡ ባሰብነው ልክ ለመስራትም እቅዱ አለን፡፡
ለሽልማት ድርጅቱ ዋነኛው ተግዳሮት ምንድን ነው?
ዋነኛው ተግዳሮት የገንዘብ አቅም ነው፡፡ ሌላው ትልቁ ችግር እኛ ሃገር ታሪካቸው የተመዘገበላቸው ሰዎች ማጣት ነው፡፡ ብዙ ሰዎች የራሳቸው የህይወት ታሪክ ሰነድ የላቸውም፡፡ በሌላው አለም ትንሽ ስራ የሰራ ሰው በድረገፆች ቢፈለግ ታሪኩ ይገኛል፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ግን እንዲህ በቀላሉ ታሪኩ አይገኝም፡፡ የተጠናቀረ የኢትዮጵያውያንን ስራ የሚገልፅ ሰነድ ማጣት ነው ሌላው ትልቁ ተግዳሮት፡፡
የገንዘብ ምንጫችሁ ምንድን ነው?
በአብዛኛው ከአንዳንድ በጎ አደራጎት ግለሰቦች ነው የምናገኘው፡፡ ስፖንሠር አድራጊዎች በብዛት የሉንም፡፡ አንዳንዶች ግን አይጠፉም፡፡ እንደ ሌላው ዘርፍ በብዛት ስፖንሰር አይገኝም፡፡ እኛም ይሄን ስለምናውቅ፣ በጥቂት ጉልበትና የገንዘብ አቅም ለመስራት የሚያስችለን ስልት ነው የምንነድፈው። ከመጀመሪያው ዓመት ጀምሮ አብረውን እየሰሩ ያሉ ግለሰቦችና ጥቂት ተቋማት አሉ፤ የነሱ ድጋፍም አልተለየንም፡፡
ለሽልማቱ ለመታጨት የእድሜ ገደብ አለው?
የለም! ምንም የእድሜ ገደብ የለውም፡፡ ዋናው ለሽልማቱ የሚያበቃውን መስፈርት ማሟላት ነው የሚጠበቀው፡፡  
ተሸላሚዎች በህይወት ያሉ ብቻ ነው ወይስ?
አዎ! በህይወት ያሉ ብቻ ናቸው፡፡ ነገር ግን በህይወት የሌሉ ሰዎች በልዩ ሁኔታ ተመርጠው ይሸለማሉ፡፡
እንዴት ሽልማቱ ላይ ፖለቲካ አይጫናችሁም? ምን ያህል በድፍረት ነገሮች ታከናውናላችሁ?
የኛ ዋናው መስፈርት ኢትዮጵያዊ መሆን ብቻ ነው፡፡ ዘር፣ ቋንቋ፣ ፖለቲካ፣ ሃይማኖት አይደለም፡፡ ተቃዋሚም ሆነ ሌላው ብቁ እስከሆነ ድረስ ይሸለማል፡፡ ምንም የሚጫነን ነገር የለም። በተቃውሞ ፖለቲካው ጎራ የሚታወቁት ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ ባለፈው ዓመት ተሸልመዋል፡፡ ከሶስቱ የመጨረሻ የመምህርነት ዘርፍ እጩዎች አንዱ ሆነው ተሸልመዋል፡፡ ይሄን መንግስት በመተቸት የሚታወቁትና አሜሪካን ሀገር የሚኖሩት ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ፤ ተሸልመዋል፡፡ ለኛ ዋናው ጉዳያችን፣ ሰውየው ኢትዮጵያዊ መሆኑና ለኢትዮጵያ መስራቱ ላይ ነው፡፡
ይሄን የሽልማት ድርጅት ስታቋቁም በምን ራዕይ ነው?
አንድ ሀገር በጎ ሰዎችን ካላገኘች እንደ ሀገር መቀጠል አትችልም፡፡ በጎ ሰሪዎች የምንላቸው ራሳቸው በግላቸው ሊጠቀሙበት ከሚችሉት ያለፈ ትውልድና ሀገርን የሚጠቅም ስራ የሰሩ ሰዎች ማለት ናቸው፡፡ እዚህ ጋ ሁለት ምሳሌዎች ላንሳ፤ ለምሳሌ የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የሰሩት ሰዎች፤ እነሱ ካገኙት ጥቅም በበለጠ በየዘመናቱ የነበሩ ትውልዶች እያስጎበኙ ያገኙት ጥቅም ይበልጣል፡፡ እነዚያ ሰዎች ዛሬ አልፈዋል የሉም፤ግን እኛ በታሪኩም እየኮራን፣ በገንዘቡም ጥቅም እያገኘን ነው፡፡ አክሱምን የሰሩትም በተመሳሳይ ታቦተ ፅዮንን እያስጎበኘን፣ ሃውልቶቹን እያስጎበኘን፣ እኛ ነን እየኮራንበትና እየተጠቀምንበት ያለው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ በጎ ዜጎች ከሌሉ ሀገር አትኖርም፡፡ ሀገር ልታድግ፣ ልትሰለጥንና ልትቀጥል የምትችለው፣ በጎ ሰዎችን የምታከብር፣ ሀገር ስትሆን ነው፡፡
ለሀገርህ ምን ትመኛለህ?
ኢትዮጵያውያን እርስ በእርሳችን ተግባብተንና ተገነዛዝበን፣ ከመገፋፋቱ ይልቅ መተባበሩን አብዝተን፣ አንዲት ጠንካራ ሁላችንንም የምታስከብር፣ ሁላችንም የምንወዳት፣ ማንም የማይገለልባት፣ ማንም ደግሞ የበላይ የማይሆንባት፣ ለሁላችንም የምትሆን፤ ሀዘኗንም ደስታዋንም፣ ጥጋቧንም ረሃቧንም ለሁላችን ማካፈል የምትችል ኢትዮጵያ እንድትኖረን ነው የምመኘው፡፡
ስለ አገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ምን ትላለህ?
እኔ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በጣም ነው የሚያሳዝነኝ፤ በጣምም ነው የሚያሳስበኝ፡፡ ፖለቲካ ራሱ እንደ ሳይንስ አለን ለማለት ይከብደኛል፡፡ ፖለቲካ አሁን በዓለም ላይ አድጎ፣ አድጎ ልክ እንደ ሳይንስ በኮሌጆች የሚጠና፣ ራሱን የቻለ እውቀት ሆኗል፡፡ እኛ ሀገር ግን ምን እንደምንፈልግ አይታወቅም፡፡ ውይይቱም ክርክሩም ፍፁም ኢትዮጵያዊ ጨዋነት የተለየው፣ ከየት እንደወሰድነው ሁሉ ለማወቅ የሚከብድ ነው፡፡ የምዕራብ አለምን ስናይ እንደኛ አይደለም። የምስራቁንም ብንመለከት እንደኛ አይደለም። እንደማን ነን ብሎ ለመናገር ራሱ የሚከብድ የፖለቲካ ጨዋታ አለን ብዬ ነው የማምነው፡፡ አሁን ያለው የፖለቲካ ጨዋታ ለሁላችንም አይጠቅምም። በጣም የሰለጠነ በእውነትና በእውቀት ላይ የቆመ ፖለቲካ፣ ያስፈልገናል ብዬ ነው የማምነው፡፡
እንዲህ አይነት አስተሳሰብ የዳበረበት የሠለጠነ ፖለቲካ ይኖረናል የሚል ተስፋ አለህ?
ወተት ተንጦ….ተንጦ ቅቤ መውጣቱ ስለማይቀር፣ አሁን ያለው ሁኔታም ተንጦ… ተንጦ ሁላችንም እንደማይጠቅመን ሲገባን፣ ያኔ ወደ ትክክለኛው መስመር የምንመጣ ይመስለኛል፡፡
ብዙ ጊዜ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የእውቀት ስፋት ሳይገድብህ፣ አስተያየቶችና ትንታኔዎች ትሰጣለህ? ከየት የመጣ ነው? ጊዜውንስ እንዴት ነው የምታብቃቃው?
እኔ ባለኝ ጊዜ እና ሁኔታ ሁሉ እነዚህን ነገሮች ለመከታተል እሞክራለሁ፡፡ ያን ያህል ከሌሎች የተለየ ንባብ፣ ከሌሎች የተለየ ሁኔታ ኖሮኝ አይደለም፡፡ እርግጥ ሳነብ የማነበው ለጥቅም ነው። ይሄ ማለት የማነበው መጀመሪያ ምንድን ነው የምሰራበት የሚለውን አስቤ ነው፡፡ እኛ ከተጠቀምን ለሰው መስጠት አለብን ብዬ አስባለሁ፡፡ ትልቁ ንፍገት የእውቀት ንፍገት ነው፡፡ የምናውቀውን ለሌላው አለማሳወቅ ትልቁ ንፉግነት ነው፡፡ አባቶቻችን በአለም ሲዞሩ እውቀት ቀድተው፣ በመፅሃፍ ፅፈውልናል፣ ላሊበላ እየሩሳሌም ሄደው፣ እየሩሳሌምን አስመስሎ፣ ላሊበላን ኢትዮጵያ ላይ ሰራ፡፡
እነ አቦነህ እዝራ በውሃ የሚሰራ ወፍጮ አዩ፤ ኢትዮጵያ አምጥተው ሰሩ፡፡ በጣም ብዙ ሰዎች ውጪ ያዩትን ወደ ኢትዮጵያ እያመጡ ለሃገራቸው እውቀት አሸጋግረዋል፡፡ ‹‹ጃፓን እንዴት ሠለጠነች?››፣ “ማደግ እንደ እንግሊዝ ነው” እያሉ መፅሃፍ ይፅፉ የነበረው ለሃገራቸው በማሠብ ነው፤ ስለዚህ ሰው ያለውን እውቀት መስጠት አለበት፡፡ አንድ ሻማ መጠኑ አይደለም ወሣኙ፤ እሳት ከተለኮሰበት ትልቅ ብርሃን መስጠት ይችላል፡፡ ያንን ስለማምን በተቻለኝ አቅም ባለኝ ጊዜ ያለኝን ለማከፋፈል ወደ ኋላ አልልም፡፡ እኔ በታክሲ ተሣፍሬ ስጓዝ፣ እዚያ ውስጥ የማየውን የምሰማውን በማስታወሻ ደብተሬ እመዘግበዋለሁ፡፡ በዚያ በዚያ የማገኛቸውን መልሼ ስለማከፍል ነው ለሰዎች የማውቅ የምመስላቸው እንጂ የተለየ ነገር ኖሮኝ አይደለም፡፡
ብዙ ጊዜ ጸሐሃፊ፣ የታሪክ ተመራማሪ፣ የሃይማኖት አስተማሪ፣ የባህል ተቆርቋሪ ሆነህ ትቀርባለህ፡፡ ትክክለኛው የሙያ መስክህ የትኛው ነው?
እኔ መጀመሪያ ሰው ነኝ፡፡ ለኔ ሙያዬ ሰው መሆን ነው፡፡ ሰው ከመሆን ውጪ ሙያ የለኝም፡፡ ባለኝ ሁሉ የምችለውን አበረክታለሁ፤ ብዙ ድንጋይ የወረወረ ሰው ደግሞ አንዱ ሳይመታለት አይቀርም ይባላል፡፡
ወደ ብዙ የባህር ማዶ አገራት ትጓዛለህ?… እንደውም ጉዞ በጣም ታበዛለህ ይባላል፡፡ ተጓዥ  የሆንከው ለምንድን ነው?
ብዙ ጊዜ በየሃገራቱ የምሄደው ለቤተክርስቲያን አገልግሎት ነው፡፡ አልፎ አልፎ ለተለዩ የግል ስራዎች እሄዳለሁ፡፡ እኔ በምሄድበት ሃገር ህንፃው ወይም ሱቁ አይደለም የሚያስደስተኝ፤ የህዝቦቹን ፍልስፍና፣ አስሳሰብ፣ ታሪካቸውን፣ ተረቶቻቸውን፣ አባባሎቻቸውን፣ ከጀርባ ያሉ ነገሮቻቸውን ማየት የምችልበት ቦታ ነው መሄድ የምፈልገው፡፡ ምንድን ነው የነሱ ስልጣኔ? እነሱ በምንድነው ከኛ የተለዩት? እኛ ከነሱ የጎደለን፣ እነሱ ከኛ የጎደላቸው ምንድን ነው? የሚለውን ለማየት ነው የምሞክረው፡፡ ያየሁትንና የሰማሁትን ደግሞ ለሃገሬ ሰው ለመንገር እሞክራለሁ፡፡
አሁን መደበኛ ሥራህ ምንድ ነው?
አሁን አጊዩስ ህትመት እና ንግድ ድርጅት የሚባል አለ፤ የሱ ሥራ አስኪያጅ ነኝ፤ አብዛኛውን ጊዜ እዚያ ነው የምሠራው፡፡ ከዚያ ውጪ ባለኝ ጊዜ ደግሞ ማህበራዊ አገልግሎት እሠጣለሁ፡፡

Read 6666 times