Saturday, 20 May 2017 12:24

የቄሳርን ለቄሳር

Written by  እዮብ ተስፋዬ
Rate this item
(0 votes)

   (‹‹…ሙዚቀኝነትና ኢትዮጵያዊቷን ቤተ - ክርስቲያን…›› ለሚለው ፅሁፍ የተሰጠ ፍልስፍናዊ ያልሆነ መልስ)
‹‹ቤት ያጣው ቤተኛ፤ ሙዚቃ ሙዚቀኝነትና ኢትዮጵያዊቷ ቤ/ክርስትያን›› በሚለው የአቶ ዮናስ መፅሐፍ ላይ በተደረገው ውይይት ላይ ባልገኝም አቶ ብሩህ ዓለም የተባሉት ፀሃፊ በዚህ ጋዜጣ ላይ ሚያዚያ 14 ቀን 2009 ዓ.ም ባወጡት ፅሁፍ ላይ አስተያየት ለመስጠት እሞክራለሁ፡፡
ከፀሐፊው እንደተረዳሁት፤ ውይይቱ ያተኮረው በዜማዎች ላይ ቢመስልም አቶ ብሩህ ግን በውይይቱ ላይ ተመርኩዘው በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የ2000 ዓመት ጉዞ ላይ አንዳንድ ትችት ለመሰንዘር ሞክረዋል፡፡ ስለዚህ እኔ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን አስመልክቶ በተሰነዘረው ሀሳብ ላይ አተኩራለሁ፡፡
የውይይቱ ጭብጥ ሙሉ ለሙሉ በጋዜጣው ላይ ተዘግቦ ከሆነም መልካም፤ የኔ ፅሁፍ ለሁሉም የተበረከተ ይሆናል፡፡ በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በሉተር ምልከታ ላይ በተሰነዘረው ሀሳብ ላይ  የፀሐፊው አረዳድ ትክክል ነው ብዬ ባላስብም ብዙ ማለት አልፈልግም፤ ነገር ግን የፕሮቴስታንት መምህር የሆነው ማይልስ “Understanding your Potential” በሚለው መፅሐፍ ላይ ከእዝቅኤል 28፡17 ላይ ጠቅሶ እንዲህ ብሎ ፅፏል፡-
“Before the fall, zucifer’s responsibility in heaven was to be the music and worship leader. He was designed with the potential not only to lead in music and worship, but also to produce it.››
 ቀጥለውም ሰይጣን በሰማይ ያሉትን መልዓክት በመምራት አምላክን ለማመስገን በዜማው ላይ ይመራ እንደነበረ፤ ይገልፃሉ፡፡ ነገር ግን ከአምላክ ተለይቶ ከገነት ከተባረረ በኋላ የሆነውን እንዲህ ያብራራሉ፡- “But that wisdom became corrupted. It was not taken form him. It just got corrupted. …”
ቀጥለውም እንዲህ ይላሉ:-
“That’s why music is such an important part of our world today. The guy who is running the spirit of the world is a cheap musician. The amounts of money the devil uses to support the music ministry of the world is amazing.”
ለዚህ ነው እንግዲህ በፕሮቴስታንቱም ጉዳይ ያልተስማማሁት፡፡ ሌላው የመፅሐፉ ደራሲ በመፅሃፋቸው ላይ ጠቅሰውታል የተባለውና አቶ ብሩህ እንደ ፅሁፋቸው ማጠናከሪያ የተጠቀሙበት ደካማ ሀሳብ በአንቀፅ 4 ላይ የጠቀሱት ነው፡፡ “የጥንት ግሪካውያንና ሮማውያን ለሙዚቃ ከፍተኛ ክብር የነበራቸው ቢሆንም የክርስትና ዘመን ላይ ግን ይሄ ተቀዛቅዟል፡፡ ክርስትና ሲመጣ መንፈሳዊና አለማዊ በሚለው ተቃርኖሽ ክፍፍል ውስጥ ሙዚቃው በዓለማዊ መደብ ላይ በመውደቁ የመጀመሪያውን ውግዘት አስተናገደ”
የሚገርም ቁጭት ነው፡፡ ታዲያ ቤተ ክርስቲያን ጣኦት አምላኪዎች ያቀናበሩትንና ለጣኦት አምልኮ ይውል የነበረን ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተቀብላ እንድታበለፅገው ወይስ እንድታከብረው ተጠብቆ ነበር፡፡ ጣኦት አምላኪዎች ጣኦታትን ከስሜታቸው፣ ከውስጣቸው አውጥተው፣ በእጃቸው ገንብተው እንደሚያመልኳቸው ሁሉ አንድ ሙዚቃዊ ድርሰትም ከሰው ውስጣዊ ስሜት የሚመነጭ የዚያ ሰው ነፀብራቅ ነው፡፡
ስለዚህ ነው ክርስቶስ ለግሪካዊቷ ሴት፤ የልጆቹን ለውሾች አልጥልም ያላት፣ ውሻም በተመሳሳይ ከውስጡ አውጥቶ ያስመለሰውን ይመገባልና፣ እንግዲህ ይሄን የአሸዋ ግንብ እየናድነው እንሂድ፡፡ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያነጣጠረው የአቶ ብሩህ ፅሁፍ ሲጠቀለል፤ ሁለት የተያያዙ ጉዳዮች ላይ ያነጣጥራል፡፡
ይሄውም በአቶ ብሩህ እይታ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዝግ መሆን ምክንያት  በመንፈሳዊው አለምና በአለማዊው መሀል ያለውን ቅራኔ (ልዩነት) ለማስታረቅ ባለመቻሏ፣ አንደኛ በመንፈሳዊው ዜማና በአለማዊው ሙዚቃ መሀል ልክ እነ ሉተር እንዳደረጉት፤ (ይህ የፀሐፊው እይታ ነው) አዋህዳ ወደ አንድ ለማምጣት ባለመቻሏ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ሊያድግ አልቻለም፡፡ ሁለተኛው በዚሁ ከላይ በተገለጸው ቅራኔ (ልዩነት) ምክንያት፤ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ይሄንን ማስታረቅ ባለማካሄዷ፣ ፕሮቴስታንቶችና ካቶሊኮች በየሀገራቸው ያገኟቸውን ታላላቅ ፈላስፎች፣ ሳይንቲስቶች የመሳሰሉትን ልናገኝ አልቻልንም የሚል  (ሁሉንም በሳቸው አስተሳሰብ ድክመቶቻችን ያሏቸውን ነገሮች ሁሉ) በቤተክርስቲያን ላይ የማላከክ ደካማ አስተሳሰብ ነው፡፡
እነዚህን ከላይ የተገለፁትን የፀሃፊውን ትችቶች፤ ፀሀፊው እራሳቸው እንዴት እንደለገጿቸው ከብዙ በጥቂቱ አንድ ሁለቱን እንይ፡፡ ‹‹ቅዱስ ያሬድን በኢትዮጵያ ሆነ በዓለም የኪነጥበብ መድረክ ላይ እንዳይወጣ ያደረግነው ደግሞ በመንፈሳዊው ሆነ በዓለማዊው ህይወት መካከል ያለውን ቅራኔ መፍታት ባለመቻላችን ነው፡፡ ከዚህ የቅራኔ አዙሪት መውጣት ባለመቻላችን ቅዱስ ያሬድን አምክነነዋል››
 ሌላው ደሞ እንዲህ  ይላል፡-
‹የዘርዓያዕቆብና የወልደ ህይወት ጥረት ቢሳካ ኖሮ፣ 1300 ዓመታት እንደ ኩሬ ውሃ አንድ ቦታ ረግቶ እየበሰበሰ የነበረውን የኢትዮጵያ ባህል፤ አዲስ እስትንፋስና አዲስ ህይወት ይዘረቡት ነበር››
በጣም አስደንጋጭ ቢሆንም አቶ ብሩህ ይህንን ስደብ በድፍረት መፃፋቸው (እንደ የቅዱስ ያሬድ መምከንና በሰበሰ ስለተባለው ባህላችን ማለቴ ነው) ከየትኛው አቅጣጫ ቆመው ተመልክተውን እንደሆነ ግራ አጋብቶኛል፡፡ በእርግጥ ትምህርቱ እራሱ መሰረቱ የራስን መናቅ ከሆነ፣ መልካም ፍሬ ወይም ቅን እይታ ሊያፈራ አይችልም፡፡
ለማንኛውም የኔ አስተያየት የጥቂቶች አይደለምና ሀሳቤን ላሰፍር፡፡ አስተያየቴን አጠርና ፈርጠም ያደርገዋልና ከእነዘርዓያዕቆብ ልጀምር። ይህ የኢ.ቤ.ክ ሊቅና ደቀመዝሙር ወልደ ህይወት፤ ነጮቹ እንደነገሩን፤ ከዓለማዊ ፈላስፎች የሚመደቡ አይደሉም፡፡ ልክ የሀገራችን መንግስት ተቃዋሚዎችን “በህገመንግስቱ ላይ ከተስማማን መወያየት እንችላለን” እንደሚለው፤ አንድ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ከመፅሀፍ ቅዱስ ሀሳብ ሳይወጣ በቤተ ክርስቲያኗ አካሄድ ላይ ጥያቄ ሲያቀርብ ስህተት አለ ሊል ይችላል፡፡ ጥያቄዎችን ማንሳቱና በቤተክርስቲያኒቷ ላይ የማይስማማባቸው አመለካከቶችን ማቅረቡ ፈላስፋ አያሰኘውም፡፡ ወይም ቤተክርስቲያኒቷን ከመንገዷ አስቶ ከአለማዊ ህይወት ውስጥ አይከታትም፤ ምክንያቱም ሊቁና ቤተ ክርስቲያኒቷ በመፅሀፍ ቅዱስ ጥላ ስር ሆነው ነው ሊወያዩ የሚችሉት፡፡ ስለዚህ ማንኛውም የቤተ ክርስቲያን ሊቅ፤ ጥያቄው ቤተ ክርስቲያኑ ከመፅሐፍ ቅዱስ መንገድ እንድትወጣ የሚጠይቅ ከሆነ፣ ይህ ሰው ጥያቄውን ካቀረበበት ግዜ ጀምሮ ከቤተ ክርስቲያኗ ይገለላል፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ደሞ ይህንን የሊቁን ጥያቄ ተቀብላ ከመፅሐፍ ቅዱስ መንገዷ ከወጣች ከዛ ቀን ጀምሮ ያቺ ቤተ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን አትባልም፡፡ስለዚህ ለፀሀፊው ለመግለፅ የምፈልገው፣ በአለማዊ እይታ እድገት መለወጥ መሻሻል የሚባል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚካሄድ ነገር የለም፤ ጭራሽ ከአለማዊ አኗኗርና ብልፅግና ጋር የሚገናኝ ወይም የሚዋሃድ ነገር የለም (በግለሰብ ደረጃ መንፈሳዊ እድገት ቢኖርም ፍፁም ከፀሀፊው ሀሳብ ጋር የሚሄድ አይደለም)
ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ስለ አለማዊ ጉዳይ የሚፈላሰፉ ፈላስፎች አያስፈልጓትም፡፡ እነሱንም ለመፍጠር ሰርታ አታውቅም፤ ከነሱም ጋር አንዳች ውህደት የላትም፡፡ ይህም ሲባል የቤተ ክርስቲያን ተከታዮች አለማዊ ፈላስፎች የሚጠይቋቸውን ጥያቄዎች አይነኳቸውም ለማለት አይደለም፤ ነገር ግን በአለም ላይ ያሉ ፈላስፎች ሲጠይቋቸው ለኖሩባቸው ጥያቄዎችና ግራ መጋባቶቻቸው፣ ክርስቲያኖች በታላቁና ቅዱስ መፅሃፋቸው ላይ መልስ ስለተሰጣቸው እንጂ፡፡ ለምሳሌ በመፅሐፈ ኢዮብ ውስጥ አለማዊው ሳይንስ በ19ኛውና በ20ኛው ክፍለ ዘመን ያረጋገጣቸው እውነቶች የክርስቲያኖቹ መፅሀፍ ከ3000 አመት በፊት የመዘገባቸው ነበሩ። ከነሱ ውስጥ ‹‹ምድር በህዋው  ላይ ያለመያያዣ እንደተንጠለጠለች የሚገልፀውና›› በውቅያኖስ ስር የምንጭ ውሃ እንዳለ የገለፀበት ሌሎች ከ50 የሚበልጡ አለማዊው ሳይንስ እውነታዎቹን ለማረጋገጥ ከ3000 አመት በላይ ፈላስፎቹና ሳይንቲስቶቹ የተወዛገቡባቸው እውነቶች፤ የተመዘገቡበት ታላቅ መፅሐፍ የተሰጣቸው ክፍሎች ናቸው፤ ስለዚህ ግራ የተጋቡ አለማዊ ፈላስፎች ለቤተ ክርስቲያን ምዕመን አያስፈልጉትም፡፡ ቅዱስ ያሬድ በታላቅ መንፈሳዊ መመሰጥ የደረሰው ዜማ ዋና አላማው አምላክን ለማመስገኛና ለቤተክርስቲያኗ አገልግሎት እንደመሆኑ ቤተክርስቲያኑ በክብር ተይዞ አምላክ ሲመሰግንበት ስለኖረ እንደመከነ መቆጠሩ አስገራሚ ነው፡፡ ይህ መንፈሳዊ ዜማ በቤተክርስቲያኗ ሳይበረዝና ሳይከለስ ተጠብቆ መኖሩ ቤተ ክርስቲያኗም ሊያስከብራት ይገባል እንጂ ግራ በተጋቡ በጠፉና በአለም ብዥታ በተወሰዱ ልጆቿ ሊያስተቻት ባልተገባ ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሀሳብ ለመቀባበል ዝግጁ ነኝ፡፡

Read 1194 times