Monday, 13 March 2017 00:00

ሰተቴ - ያልዘመርንለት ሌላኛው ጀግና

Written by 
Rate this item
(24 votes)

ሰተቴ - ያልዘመርንለት ሌላኛው ጀግና
በቁም ለገደሏት ለሞተች ሀገሬ
ባንድ አይኔ አነባለሁ አንዱን አሳስሬ፡፡
(“ሰተቴ”፣ ገጽ 58)
“ሰተቴ”፣ በቅርቡ ለንባብ የበቃ አዲስ መፅሐፍ ነው፡፡ እንደ መነሻ በአንድ ግለሰብ ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጥን የታሪክ ጥናትና የምርምር ውጤት ነው፡፡… ሐገራችን ላይ ሰተቴን ጨምሮ በተለያየ ዘርፍ ውስጥ ያልዘመርንላቸውና ጨርሶም ያልተረዳናቸው ጀግኖቻችን ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ …ከሰተቴ ጋር በተያያዘም ከእስከዛሬው ቁርጥራጭና የተዛባ  አቀራረብ በተለየ መንገድ ከሰሞኑ ጠብሰቅ ብሎ የቀረበ የሚመስለው “ሰተቴ” መጽሐፍ ስለ ሰተቴ ማንነትና ስራዎች የተሻለ ምላሽ ይዞ መጥቷል።
“ሰተቴ” የተሰኘውን መጽሐፍ ያበረከቱልን ደራሲ ዲራዓዝ፣ በባለታሪኩ ሕይወት  ዙሪያ  ጥናታዊ  ምርምር  እንዲያካሂዱ  ያነሳሳቸውን ምክንያት በመፅሃፉ (ገፅ 20 ላይ) እንዲህ በማለት አስፍረዋል፡-
“ስለ ትናንት  ማንነታችን  የተሟላ   ምስል   እንዲኖረን ብቻ  ሳይሆን   እንድንማርበትም ካስፈለገ፣  ትናንትን  የምንመረምርበት የታሪክ  መነፅር  ከአንድ አይናነት  ወደ   ሁለት፣ ሶስት፣ አራት… አይናነት ሊሸጋገር፤  እንደ አዳኙ ሁሉ ከታዳኙም ግንባር፣  እንደ መሪው ሁሉ ከተርታው ሕዝብም አንፃር ሊጠና፣ ሊመረመር፣ ሊፃፍና ሊነበብ ይገባል፡፡ በምርጫ የተቀላቀልኩትንና  እስከ  መመረቅ  ድረስ    ታላቅ  ዋጋ  ሰጥቼ  የተከታተልኩት  የታሪክ ትምህርት፣ ይህን ሽግግር በሚደግፍ ጥናት  ማክተም እንዳለብኝ በማመን የመመረቂያ ጥናት  ፅሁፌን እጅግም ታሪክ   ትኩረት ባልሰጠውና ባልተዘመረለት   የጅማው   ከድር ሰተቴ ሕይወት ዙሪያ እንዲያጠነጥን የወሰንኩት በዚህ የተነሳ ነበር፡፡”
መልከ ብዙው ሰው…
እግር ጥሎት ጅማ የሄደ ሰው፣  ከቡናዋ ባልተናነሰ መልኩ ስለ አንድ ሰው ዝና ጎልቶ ይወራለታል፡፡ ስለ ሰተቴ የሰሙ ሰዎችም በአብዛኛው ከሳቅ የዘለለ ነገር ስለማትረፋቸው በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም፡፡ … ብዙዎች ሰተቴን እብድ፣ ጭራሽም በእውኑ ዓለም ያልኖረ፣ በብልግና እና ደርግን በሚወርፉ ግጥሞቹ ብቻ መስለው ሊያቀርቡት ይሞክራሉ፡፡ የተቀሩት ጥቂቶች ደግሞ ሰተቴ አንዳች ተልዕኮ ያለውና ሊመረመር የሚገባው ጥልቅ ሰው እንደሆነ ያምናሉ፡፡  አሁን ላይ ስለ ሰተቴ በተሻለ መንገድ ሰፋ ያለ ሀተታ ያቀረቡት ደራሲው ዲራዓዝም ባካሄዱት ምርምር፣ የሰተቴን ትክክለኛ ማንነትና የበዙ መልኮች በመረጃ ጭምር ለማስደገፍ እየሞከሩ ያሳዩናል፡፡
ጣሊያን ኢትዮጵያን  በወረረች በ3ኛው ዓመት በ1931 ዓ.ም አካባቢ በጅማ መንደራ ውስጥ  የተወለደው ባለታሪኩ `ከድር መሐመድ  ሐሠን  ቢላል` በብዙዎች አጠራር ከድር ሰተቴ፤ እናቱ ሳዲያ ሀቢብ ትባላለች፡፡ እናትና አባቱ ከወለዷቸው አራት ወንድና ሁለት ሴቶች መካከል ከድር ቀዳሚውና የመጀመሪያ ልጅ ነው፡፡ ከድር ሁልጊዜም ዘናጭና እጅግ በተሳካ የንግድ ህይወት ውስጥ ጭምር ያለፈ ሰው ስለመሆኑ ደራሲው በማስረጃ ጭምር እያስደገፉ ይነግሩናል፡፡  የከድር የልጅነት ሕይወቱ፣ የተጓዘበት  የሕይወት መንገድ፣  የጅማ ነባራዊ ሁኔታ፣ የጥበብ ሰው ወይም ፈላስፋ ለመሆኑ ፍንጮች  ቢሰጥም፣ ደራሲው ከምንም ነገር  በፊት  ከድር  ከዘመኑ ቀድሞ ስለመፈጠሩና ልዩ ችሎታን  የታደለ የጥበብ ሰው ስለመሆኑ ማስረጃ ተደርጎ በብዙዎች  የሚቀርበው  ሃሳብ፣ ተቀምጦ ይሁን   አልያም  ሲዘዋወር  በድንገት የሚያስተውለውን  ክስተት  በተዋበ  ግጥም  ከሽኖ ያለ አንዳች ፍራቻ እዚያው በዚያው ማቅረብ በመቻሉ ነው ይላሉ፡፡
አልችል ብዬ መርገጥ፤ነፍሴን በግሬ ዳና
ስቃዬን አያለሁ፤ዘንድሮም እንዳምና፡፡
(ሰተቴ፣ ገጽ 45)
አብዮተኛው …  
ብዙዎች ሰተቴ ሲባሉ ወደ አፋቸው ቀድሞ የሚመጣው ግጥሙ፡-
ኢሰፓኮ
ባዶ ፓኮ
የሚለው ነው፡፡ ሰተቴ መሰል ግጥሞቹን ምንም ላይ ሳያሰፍራቸው ድንገት ከማውረዱ ባሻገር በአደባባይ ላይ ጮክ ብሎ ነበር የሚላቸው፡፡ ታዲያ ጊዜውን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ጊዜው አይደለም የፈለጉትን እንዲህ በአደባባይ ለመናገር ቀርቶ፣ ዝም ብሎ መኖር እንኳን ያስፈራ የነበረበት የደርግ ዘመን ነው፡፡ ከድር ሰተቴ ደርጎች ስልጣን ይዘው ከተረጋጉና የህዝብ አገልጋይና ሀቀኛ ነን በሚል ካኪያቸውን መልበስ በጀመሩበት ወቅት እንደ ልማዱ ማንንም ሳይፈራ አደባባይ ላይ ወጥቶ ድምጹን ሳይቆጥብ፡-
ልብሳቸው ሀቀኛ
ውስጣቸው ጠንቀኛ፡፡
ሲል ካኪ ለባሽ ደርጎችን በአደባባይ ያለ አንዳች ፍራቻ ሸንቁጧቸዋል፡፡  
በሃገራችን ረጅም  የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ በሃይል ተደግፎ፤ በአመፃ  ታጅቦ፣ አገርና ምድሩን ከብዶ ከተጫነውና ጎልቶ ከሚቀነቀነው ተረክና ዜማ በተለየ መልኩ ወይም በተቃራኒው … በአደባባይ ለእውነት ጠበቃ   መቆም፤ መንግስታዊ  ግፍን በመቃወም  ከተጠቁትና ልሳናቸው  ከተለጎመው ወገኖች ጎን በመቆም  አንደበታቸው መሆን የእውቀት ቀንዶች፣ የጥበብ ሊቆች ድርሻና ሞራላዊ ኃላፊነት ተደርጎ ቢወሰድም በተግባር መሬቱ ላይ የምናገኘው ተጨባጭ እውነታ ግን ከሚባለው የሚገጥም  አይደለም፡፡  አልፎ  አልፎ  በዚህ  ደረጃና  ቁመት   ሊሰለፉ  የሚችሉ   ዜጎች   ኖረው ማለፋቸውን  የምንክደው  ባይሆንም  የአመዛኞቹ  አካሄድ  በዝምታ  ተሸብበው፣ በአድርባይነት ተከበው ከራሱ ከአፄ ቴዎድሮስ  ገበሬ ባልተለየ መልኩ፡-
ልጅ አሳድግ ብዬ
ከብት አረባ ብዬ
ለወታደር ዳርኳት
ሚሽቴን እቴ ብዬ ---
በሚል ቅኝት ቄሱም ጭጭ መፃፉም ጭጭ ብለው ዘመን መሻገራቸውን እናውቃለን፡፡ በተለይም   መንግስትን  በአደባባይ  ቀርቶ  በጓዳም  መውቀስና  መቃወም ወንጀል  ሆኖ በሚያሳስር፣ በሚያስገርፍና  በሚያስገድልበት  በዚያ  የጨለማ   የደርግ ዘመን፣ ከድር ሠተቴ ተለይቶ እንደምን ሊበቅል ቻለ ? ያጠያይቃል፡፡
እንደምን ደፍሮ ደርጉን  እስከ ዶቃ  ማሰሪያው በአደባባይ  ሊያስታጥቀው ቻለ? ከምንም  ነገር  በላይ መጽሐፉን  ስናነብ  ቀድሞ  ወደ አእምሯችን  የሚገባ  ጥያቄ  ነው፡፡  ደራሲው   በቀጥታ ወደ ድምዳሜ የምናመራበትን  መረጃ ከማቀበል ይልቅ  በጅማ ቆይታቸው ከከድር ወዳጅ ዘመዶች፣ አብሮ አደጎችና የጅማ ነዋሪዎች ያሰባሰቡትን መረጃና  እጃቸው የገቡትን የከድር ሠተቴ ሥራዎች በፈርጅ በፈርጅ በመከፋፈል   የባለታሪኩን አንድም ሁለትም ሶስትም ገጽታ በግጥም ስራዎቹ በኩል ያቀርቡልናል፡፡
ትቅደም ኢትዮጵያ!
አላችሁ…  አላችሁ…  ጫማ ቀየራችሁ፤
ትቅደም ኢትዮጵያ!
አላችሁ… አላችሁ…  ሱሪ ቀየራችሁ፤
ትቅደም ኢትዮጵያ!
አላችሁ… አላችሁ…  ሹራብ ቀየራችሁ፤
አቤቱ ወጋችሁ፤
ኢትዮጵያ ተረስታ፣ አየን ፊት ቆማችሁ፡፡
*   *   *
በአስተዳዳሪ፤  
ሁሉ ሆነ ታሳሪ፡፡
በኢሰፓ  ተጠሪ፤
ወላጅ አጣ ጧሪ፡፡
በወታደር  ኮሚሳር፤
ወጣት ታፍሶ ለአሳር፡፡
ያልተፈቱ እንቆቅልሾች    
እንዲህ ያለውን ከእውነት ይልቅ ለተረት የቀረበ የሚመስለውን ታሪክ ሰምተው ግራ የተጋቡ ሰዎች ናቸው ሰተቴን በምድር ላይ ኖሮ ያለፈ ሰው መሆኑን የሚክዱት፡፡ በተለያየ ማስረጃ በምድር ላይ ኖሮ ማለፉን ቢያምኑ እንኳን ሌላ ተቀጽላዎችን ይለጥፉበታል፡፡ እብድ፣ የጎዳና ተዳዳሪ፣ የኔ ቢጤ፣… ሲሉ ወደ ራሳቸው ድምዳሜ ለመድረስ ይቸኩላሉ፡፡
እኛው ራሳችን በተሳፈርንበት የጊዜ ታንኳ አብሮን ተሳፍሮ የነበረ ዜጋችንን   በምን ምክንያት ይህን ያህል ልናጣው ቻልን፣ ያጠያይቃል፡፡ የመገንባት ያህል ማፍረስ ባልተለየው ታሪካችን እንጂ ሌላ  ማንንም ተጠያቂ አድርገን ልንወስድ የምንችልበት መንገድ የለም፡፡ ማስረጃዎችን በዝርዝር የሚያቀብሉን ደራሲው ዲራዓዝ፤ ለከድር የተሰጠው ዥንጉርጉር ገፅታ ግራ ቢያጋባቸው፣ በአንድ ዘመን፣ በአንድ ከተማ ውስጥ ኖሮ ያለፈን ስጋ ለባሽ ፍጡር በምን ምክንያት አንድ ትውልድ ሶስት መልክ ሊሰጠው ቻለ? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ (ገጽ 55)
በጣም የሚደንቀውና በዘመንም ላይ እንድናዝን  የሚያደርገን  የሠተቴ  መታወቂያ አሻራ  ሆነው የዘለቁት  ግጥሞቹ የላይኞቹ  አይደሉም።  በተቃራኒው  በሞት  ጥላ የተከበቡ፣ የኖረበትን ጊዜ  መራራ ግፍና በደል፣ ተስፋ መቁረጥና ሀዘን የሚያንፀባርቁ ናቸው፡፡ የጅማ  ነዋሪዎችም  ሠተቴን  የሚያውቁት  በአመፃ ግጥሞቹ እንጂ  ከላይ በሰፈሩት ግጥሞች እንዳልሆነ መጻፉ ከመተረኩ በተጨማሪ ለዚህ ያበቃውን ምክንያት የአብዮቱ  የጨለማ  ዘመኖች  በርካታ  የቅርብ  ወዳጅና  ተማሪ  ጓደኞቹን  በሞት የተቀማው ከድር ሰተቴ፣  ቀድሞ ከሚታወቅበት የወግ ግጥሞች በመውጣት፤ በደርግ ላይ እስከ ሕይወቱ ፍፃሜ የዓመፃ ግጥሞች ማውረድ የጀመረው `ከዚህ ጊዜ አንስቶ ነው` ይላሉ -  የሚያውቁት፤ ሲሉ ሹክ ይሉናል ደራሲው - በዚያ ሀዘንና ምሬት ከተጻፉ ግጥሞቹ ውስጥ አንዱን እንዲህ መዞ በማውጣት፡፡
ደምህን ላይልሰው፣  ስጋህን ላይበላ፤
ግፉ ልክ የለውም፣  ሰው ሰውን ሲጠላ፡፡
ደራሲው ለጥናትና ምርምራቸው የመረጡት የታሪክ ግንባር አዲስ ባይሆንም  መጽሐፉን ያቀረቡበት የጥበባዊ  ደረጃ    ከፍታ  ማለትም  የጠራ  የቋንቋ  አጠቃቀማቸው፣  መልዕክቱን  ለማስተላለፍ የተከተሉት የምዕራፍ አደረጃጀት፣ የማይደነቃቀፍ የሃሳብ ፍሰት፣… ልክ ልብወለድ የምናነብ ያህል አንዴ ከጀመርን ሳንጨርስ የማናስቀምጠው እንዲሆን ብርቱ አቅም አላብሶታል፡፡
ትንቢተኛው ሰተቴ
ሰተቴ አትመለሱም ብሎ በግልጽ የነገራቸው ሰዎች ሳይመለሱ በወጡበት ቀርተዋል፡፡ በግጥሞቹም መጪዎቹን ጊዜያት መተንበይ ችሏል። አቅጣጫዎችንም አመላክቷል፡፡ ለምሳሌም አንድን አጋጣሚ ለመጥቀስ ያህል ሰተቴ የ1977ቱ ድርቅ ከመከሰቱ ዓመታት ቀደም ብሎ ገጠመ የተባለውን ግጥም ብዙዎች የከድር መገለጫ አድርገው ያነሱታል፡፡
ሰባ ሰባት ፣
አንድ እንጀራ ለሰባት፤
እሱም ከተገኘ ምንአልባት!
ረሀቡን ተከትሎ በሚመጣው እልቂት የተነሳም የመቀበሪያ ቦታ ችግር እንደሚሆን በዚሁ ግጥም ላይ መጠነኛ ማሻሻያ በማድረግ ትንቢቱን እንደሚከተለው አስፍሯል፡፡
ሰባ ሰባት ፣
አንድ ጉድጓድ ለሰባት፤
እሱም ከተገኘ ምንአልባት!
ተጫዋቹና አሽሙረኛው ሰተቴ
ኮሎኔል ተድላ የተባሉ የጅማ ፖሊስ አዛዥ ነበሩ፡፡ ሰውዬው ከአብዮቱም በላይ ለሚስታቸው ቃል ታማኝና ታዛዥ ነበሩ ይባላል፡፡ ታዲያ ይህንን የተረዳው ሰተቴ እንደሚከተለው ይሸነቁጣቸዋል፡፡
የፍርድዎ ውሳኔ፣
በጓሮ በር በኩል
ከጓዳ ከመጣ፤
ዳኛ ቤትዎ ይቅሩ!
ሚስትዎ ችሎት ትምጣ፡፡
በሌላኛው ቀን አንድ ምሽት ላይ የደርግ ባለስልጣናት በልዩነት ከሚቀማምሱበት መሸታ ቤት ድንገት ሰተት ብሎ የገባው ሰተቴ፤ ባዶ እጁን በሽጉጥ ቅርጽ አስመስሎ “እጅ ወደላይ!” ብሎ ያዝረከርካቸዋል፡፡ በዚህ ምሽት ህዝብን ሲያሸኑ የከረሙ ቱባዎች ሁላ ሽንታም ሆኑ፡፡… ከቆይታ በኋላ ሽጉጥ አለመያዙን ሲረዱ እያዳፉ ወደ እስር ቤት ይወስዱታል፡፡  በእለቱ ቃል ይቀበል የነበረው ተረኛ ፖሊስ፤ “ዛሬ ደግሞ ማንን ተራግመህ መጣህ?” ቢለው፣ ሰተቴም ከአፉ በፍጥነት ቀበል ያደርግና ፡-
እኛ ያልነው ለፉገራ ፤
እነሱ የሚሉት የመግደል ሙከራ፡፡
ብሎ ይመልስለታል፡፡
በመነሻዬ ለመግለፅ እንደሞከርኩት “ሰተቴ” ልቦለድ አይደለም፡፡ በእውኑ ዓለም ኖሮ ያለፈን ሰው ታሪክ የሚመረምር እውነተኛ ታሪክ ነው፡፡ ሆኖም እንደ አንድ የታሪክ ጥናትና ምርምር ፅሁፍ ስንመዝነው፣ ከተዋበ መግቢያና መረጃ ማሰባሰብ ውጭ ወደ  ድምዳሜ ማድረስ የሚያስችል ምርመራና ትንተና ተካሂዶበታል ማለት አስቸጋሪ  ነው፡፡ የባለታሪኩ ናቸው የተባሉትን  ግጥሞች  በማሰባሰብ ለንባብ ማቅረብ መቻሉ ታላቅ  እርምጃ  ቢሆንም  ከቀረቡት  መሃል  የሰተቴን  ትክክለኛ  የአሻራ  መገለጫ  መስፈርት በማዘጋጀት የመለየት  ምርመራ  አለመካሄዱ የመጽሀፉ  ክፍተት  ተደርጎ  የሚወሰድ ነው፡፡  ቤተሰቦቹን በቀላሉ ማግኘት ተችሎ በማናገሩ ረገድ ግን እንዳልተሳካው ጥረት ሁሉ፣ ባለቤቱን እንዲሁም  በሕይወት ያሉ የደርጉ ፖሊሶችን፣ ዳኞችን አፈላልጎ በማነጋገር እይታቸውን ለማካተት ጥረት አለመደረጉ ሌላው የመጽሐፉ ተጨማሪ ድክመት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡  ምንግዜም ቢሆን ባለታሪኩን   ያለ ስሙ ስም  ላለመስጠት የምናደርገው ከፍተኛ ጥንቃቄ ለምርምራችን ውጤት ተዓማኒነት  ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል፡፡
ደራሲ  ዲራዓዝ    በ”ሰተቴ”  ሊያስተላልፉልን  የፈለጉትን  መልዕከት  በግልፅ  አስቀምጠው ነው ወደ ጥናትና ምርምር ስራቸው የገቡት፡፡ በመፅሃፉ  ገፅ 15 ላይ ያሰፈሩት መልዕክት እንደሚያስረዳው፤ ሀሳባቸው   የቀድሞውን  ትውልድ ከመውቀስና ከማውገዝ ባሻገር በልኩና በመጠኑ እርሳቸውና የርሳቸው ትውልድ ታሪካችንን ለማቅናት ተጨባጭ እርምጃ ለመጓዝ ያደረገውን  ትግል በመረጃ ለማስደገፍ ከራስ ጋር የተገባ ቃል ነው፡፡
በእርግጥ ደራሲው ታሪክ ከገዢዎቻችን ግንባር ብቻ ሳይሆን ከተገዢዎችና ከተራ ተርታው ሕዝባችንም ሕይወት አንፃር ሊፃፍ መቻሉን በተዋጣለት ጥበባዊ መንገድ አስመስክረዋል፡፡…    ከምንም በላይ ግን፤ በዘርና ቀለም ተሳስበን፣ በእምነትና ፖለቲካ ተቧድነን ካልሆነ በቀር እንደ አንድ ዜጋ፣  እንደ አንድ ነጠላ ነፍስ ውጤቱ ምንም ሆነ ምን፣ ለእውነት መቆም ከእውቀት ቀንዶች ከጥበብ ሊቆች ዜጎች የሚጠብቁት ጥብቅና መሆኑንና በተዳከመው ሞራላዊ መሠረታችን ላይ ነፍስ ለመዝራት የተደረገ ጥረትና ሙከራ ሆኖ ይታየኛል፡፡ በመጨረሻም “ሰተቴ” ከዚህም በላይ በመጓዝ የትናንት  ታሪካችንን የምንፈትሸው  የዛሬን አብሮነት የሚያፈርስ  ቂም ለመቆፈር  ሳይሆን  አብሮነታችንን  በላቀ   ሚዛናዊ  መሠረት  ላይ ለማኖር  መሆን  እንዳለበት አስተማሪም  አድርገን ብንቀበለው ያስኬዳልና ተደጋግሞ  ሊነበብ ይገባል።
በመጨረሻም ከድር ሰተቴ የማያልፉት ፈተና የሆነባቸው ደርጎች፣ እብድ በሚል ፍረጃ በ1981 ዓ.ም ከእብዶች ጋር ቀላቅለው ይረሽኑታል፡፡ እርግጥ ነው ከድር በራሱ ሞት ላይም ይተነብይ ነበር፡፡ ሞቱ እውን ሊሆን በተቃረበበት ሰሞን እንደሚከተለው ገጥሞ ነበር፡-
መቼ ነው የሞትኩት፣
ማነው የቀበረኝ
ምድር ቀረች ሲኦል፣
ከእንግዲህ ግድ የለኝ፡፡ (ገጽ 101)  

Read 6937 times