Sunday, 05 February 2017 00:00

የአሌክስ - የበርሌክስ መንገድ

Written by 
Rate this item
(8 votes)

ርዕስ - በፍቅር ስም
ደራሲ - ዓለማየሁ ገላጋይ
የሕትመት ዘመን - 2009
የገጽ ብዛት - 216
የመሸጫ ዋጋ - 71.00 ብር
ማተሚያ ድርጅት - Eሪቴጅ ኅትመትና
ንግድ ኃ/የ/የግል ማህበር
የታተመበት ቦታ - አዲስ አበባ
             (ቅኝት - መኩሪያ መካሻ)

    በፍቅር ስም የዓለማየሁ ገላጋይ የአእምሮ àማቂው ስድስተኛ ልብ - ወለድ ነው፡፡  ዘንድሮ ለጥበብ አድባር ያቀረበው ግብር መሆኑ ነው፡፡  ጥበብ ምሷን አገኘች፡፡ ስራዎቹ የአዳዲሶቹ ደራሲዎቻችን አዲስ ማዕበላዊ (new  wave) አጻጻፍ አካል ነው፡፡ እኛም አዲስ የአጻጻፍ ስልት ወደ ያዘው በፍቅር ስም ድርሰት ስናመራ ፍጹም ወደ አልተጠበቀ የከተማ ዳርቻ እንደርሳለን፡፡  በመጀመሪያ ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ የቤተሰብ አባላትን እናገኛለን፡፡  ፍጹማዊው ድህነት ቀይዶ ይደቃቸዋል፡፡  መቸቱ ግልጽ ነው - የምናውቀው የጉለሌው የሩፋኤል ሠፈር ስለሆነ።  ጊዜው ከደርግ ዘመን ጀምሮ እስከ መጀመሪያው የኢህአዴግ ድል ማድረጊያ ወቅት የትረካ መስመሩን ይዞ ይጓዛል፡፡  ማህበራዊ አካባቢው በጊዜው በነበረ አንባገነናዊ ሥርዓት ውስጥ ይካሄዳል፡፡  በመሠረቱ የሩፋኤል ሠፈር ለኢትዮጵያ የሥነ -ጽሁፍ ታሪክ አዲስ አይደለም፡፡ በሀዲስ ዓለማየሁ፤ በብርሃኑ ድንና በሌሎችም ሥራዎች የትወና መድረክ ነበር።  በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የከተማችን ኋላ ቀር አካባቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡  የተረሱ፤ የተገፉ - የተገፊዎች ሠፈር መሆኑን እንገነዘባለን፡፡
የዓለማየሁ ድርሰቶች በደምሳሳው ሲታዩ የደስተዮቭስኪ፤ የቼሆቭና የላቲን አሜሪካው ገብርኤል ጋርሻ ማሪኩዝ ተጽዕኖ ይታይባቸዋል፡፡  ዓለማየሁ ልክ እንደ ማርኩዝ ሁሉ “የራሱን ዓለም“ ፈጥሯል፡፡  ይህ የራስ ዓለም ከገጽ ወደ ገጽ በተለያየ መንገድ የሚገለጽና አንባቢን ባልተለመደ ጉራንጉር ይዞ የሚነጉድ መገነጢሳዊ ልጓም አለው፡፡ የአእምሮ ምግብነቱም (መገብተ-አእምሮነቱ) እንደተጠበቀ ሁኖ፡፡
ገጾቹን በገለበጥን ቁጥር የዚች ምስኪኖች ሠፈር ሰዎች ማን እንደሆኑ? ለምን እንደሚኖሩ፤ እንዴት እንደሚኖሩ? እንመለከታለን፡፡  በዚያ ፉርጎ ቤት ውስጥ የሚኖሩት አባላት ዥንጉርጉር ናቸው፡፡  ኢትዮጵያዊ ዥንጉርጉርነት፡፡  በመካከላቸው ግጭት አለ፡፡  ድርሰቱን ያቆመውም ይኸው ነው፡፡  የሥነ - ልቡናና የዕምነት አለመጣጣም ይስተዋላል፡፡  ልክ ቼሆቭ ሲጠቀምበት እንደነበረው ሁሉ ዓለማየሁም አንባቢው በግሉ እንዲያስብ ያደርጋል፡፡  በድርሰቱ እሱ ያላሟላውን አንባቢው እንዲያሟላ ዕድል ይሰጠዋል፡፡ ለዚህ ነው በአንዳንድ የድርሰቱ ክፍሎች የተንጠለጠሉ የሚመስሉንን ጉዳዮች ራሳችን በዕዝነ-ልቡናችን እንድናጠናቅቃቸው የምንገደደው፡፡
በድርሰቱ ውስጥ የሚታዩት “ትንንሽ ሰዎች“ በውስጣዊ ማንነታቸው “ትልቅነታቸው“ ይወጣል።  ትንንሽ እንዲሆኑ ኮድኩዶ የያዛቸውን ሰንካላ ጉዳይ ዓለማየሁ አንጥሮ ያሳያል፡፡  በቀድሞ የማንነት ኩራት ውስጥ ወደፊት የተስፋ ህይወት ይታሰባል። ግን ደግሞ ህይወታቸው ከእጅ አይሻል ዶማ ነው፤ ተለውጦ አናይም፡፡  በወንፊት ላይ የሚወርድ ውሃ ይመስል ምንም አይቋጥርም፡፡ ፀሐፊው በዘÈና በሚያስደምም መንገድ ለወታደራዊው ኦሊጋርኪ ያለውን ጥላቻም አስመስክሮበታል፡፡ በደሉን ያጋልጣል፡፡
ዓለማየሁ ከአሁን ቀደም ባሳተማቸው ድርሰቶቹ በኢትዮጵያዊያን አንባቢያን ዘንድ መልካም ሥፍራን አግኝቷል፡፡  የጥበብ አድባር እጣኗን አጢሳ፤ ሽቱዋን ነስንሳ ተቀብላዋለች፡፡  የአሳታሚን ክፉ ወጥመድ አልፎ ለዚህ መብቃት በራሱ መታደል ነው፡፡  ካለፉት ድርሰቶች ለእኔ በግል «አጥቢያ» እና «ቅበላ» ማርከውኛል፡፡  ጥልቀት አላቸውና፡፡
ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ደራሲው የጊዜውን አምባገነንነት ለማሳየት ቀጥታ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ አይከፍትም፡፡ እንደ ልብ - ወለድ ፀሐፊነቱ ሰዋዊ ሁኔታን (Human situation) ማሳየት ግዴታው መሆኑን በውል ተገንዝቧል።  ምንም እንኳ ግላዊ የፖለቲካ አቋም ሊኖረው ቢችልም “ትክክል“፤ “ስህተት“ በሚል የፖለቲካ አቋም ይዞ አይፈርድም፡፡  “የትናንሾቹ ሰዎች“ ህይወት እንዲህ በቀላሉ እንደማይከናወን በሰራተኛ ሠፈር ወጣቶች አሳይቷል፡፡ ገላጭ ቃላቶቹ፤ ፍልስፍናዊ ማነጻጸሪያዎቹ ወደር የላቸውም፡፡ የነፍስ ሲቃቸው ፍንትው ብሎ ይታየናል፡፡ በተለይ አንዳንድ የሚጠቀምባቸው ቃላቶቹ የቦረን ጎረምሳ የወረወረው ጦር ሆኖ ይሰማናል፡፡ አብዛኞቹ ደግሞ ሮማውያን የገነቡአቸው የዕብነበረድ ሀውልቶች ወይም እንደ ፋርስ ወላንሳ ትንቡክ ትንቡክ ስለሚሉ አይጎረብጡንም፡፡ ይዘው ያንፈላስሱናል፡፡ አቤት ምቾት - ጣ!
ዋናው ገፀ - ባህርይ ሆኖ የሚቀርበው አባቱ (ቢዘን) ህዝባዊ ብሔርተኛ ነው፡፡ “ብዜን በሰሜን ኢትዮጵያ በኩል የገንጣይና አስገንጣይ ጫና ተቋቁሞ ኤርትራን ለጓድ መንግሥቱ ያስረከበ ተራ ኢትዮጵያዊ“ ሲል ይገልፀዋል፡፡  ይህን ሰው የዚያን ዘመን ብሔራዊነት የተጎናጸፈ ነውና የጎሳ ወይም የመንደር ልጅነት አይበግረውም፡፡  የሀገር ጉዳይ ዋነኛው የህይወት እሳቤ የሆነባቸው እልፍ አእላፍ ሰዎች ተምሳሌት ነው፡፡  በተቃራኒው ሌሎች በየመሸታ ቤቱ አሸሼ ገዳሜ ሲሉና ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ (እሱ ልጆቹን በትኖ) እንደ ቢዘን ያሉ ሰዎች ብቻ ሞተው እንዲያኖሯቸው የሚጥሩ ስግብግብ ዜጎች መኖራቸውንም እንመለከታለን፡፡ “የሞተልሽ ቀርቶ፤ የገደለሽ በላ“ ይባል የለ? ለዚህም ነው ቢዘን ለሁለተኛ ጊዜ እንዲዘምትላቸው (እንዲሞትላቸው) የሚላከው፡፡  እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ስለ ሀገር ጉዳይ ዕዳ የመክፈል ጣጣ በእነዚህ ልዩ በሆኑ “ትናንሽ ሰዎች“ ጫንቃ ላይ የወደቀው፡፡  ዓለማየሁ በዝምታ አልተመለከታቸውም፡፡ በስስ ብዕሩና በአሽሙራዊ አፃፃፉ ወጋ፤ ወጋ ያደርጋቸዋል፡፡
የዓለማየሁ ቀልዶችና ገለፃዎች ሠርሥረው ደም ስር ውስጥ የሚቀሩ ናቸው፡፡  አልፎ አልፎ ለማዋዣነት ስለሚያገለግሉ ጣዕም ያለው ዜማ ሆነው ይሰሙናል፡፡  የታሪክ መስመሩን ተከትለን እንድንጓዝ የሚያደርጉ ፊት ለፊታችን የተወረወሩ የወርቅ ሣንቲሞች ናቸው ብንል ማጋነን አይሆንም።  ለምሣሌ ጥሩንባን እንውሰድ፤ - “የፀበኛ በሬ ቀንድ ይመስላል፡፡  ከቅርብ አይቼው አላውቅም፤ ጉርብርብ መዳብ ነው፡፡ ፈንጣጣ ውግ የመሰሉ ጉድጓዶቹ በዕድፍ ጠቁረዋል፡፡ አፉ በክርና በፕላስቲክ ተጠቅልሎ ወፍሯል …”
ባልና ሚስቱ መሓል ዕውነተኛ የትዳር መሠረት ተጥሏል፡፡  የማይሰበር ግንኙነታቸው ጥሩና መጥፎን አሳልፎ ቆይቷ    ል፡፡  ባለቤቱ የባዕድ አምልኮና የቤተክርስቲያን ሰው ናት፡፡  ሁለቱን በአንድ ላይ ታራምዳለች፤ እንደ ማንኛውም የሰፈር ባልቴት። እናት የቤተሰቡ ዋና የህይወት ድልድይ፤ ለፍቶ አዳሪና የቤቱ ዋልታ ናት! ወጥዋ ከሩቅ የሚጣራ ባለ ሙያ፡፡
የበፍቅር ስምን የአጻጻፍ ስልት ደግሞ ለማየት እንሞክር፡፡  የዓለማየሁ የአጻጻፍ ስልት እምን ላይ እንደሚወድቅ ለመለየት አስቸጋሪ ሆኗል።  በምናባዊና በዕውኑ አጻጻፍ ስልት መሃል እንጎቻ ትረካዎች እንደ ሰንሰለት ተያይዘው የሚቀርቡ ናቸው፡፡ በሀገራችን አልተለመደም፡፡ ባለፉት 300 ዓመታት የተፈጠረውን የበርሌክስን የሥነ-ጽሁፍ (Burlesque Literature) መንገድ የተከተለ ይመስለኛል፡፡ በኋላም በ1960ዎቹ የተፈጠሩ new waves::  በርሌክስን “ወዘበሬታ አጻጻፍ“ እንበለው ይሆን? (የሥነ - ጥበብ ጠበብት አስተያየት ቢሰጡበት መልካም ይመስለኛል)፡፡ የበርሌክስ  ዋናው መለያው ህይወትን በቧልታይና አቋራጭ መንገድ ማቅረብ ነው፡፡ አጻጻፉ ያልተለመደና በፈጠራውና በድርጊቱ  መካከል አለመመሳሰል ይታያል፡፡ በድርሰቱ ውስጥ የቀረቡት ገፀ-ባህሪያትም “በአጭር ቁመት፤ በጠባብ ደረት” እንዲሉ እጥር ምጥን ያሉ ናቸው።  ወለፈንዳዊነትም ይታይባቸዋል፡፡ እንደነ ቹቹ ወይም እንደነ ቻይና ሆነው ሲቀርቡ እንመለከታለን።  አይነኬ አባባሎች ወይም ልምዶች ወደ አደባባይ ይወጣሉ፡፡
“በፍቅር ስም“  የትረካ ሰንሰለቱ ክፍል ሁለት ላይ ሲደርስ ውጥረቱ ጥልቀት ያገኛል፡፡  ታለ በመጀመሪያ መደብ (እኔ) ውስጣዊ የባህሪያት ግጭት ውስጥ የወደቀ ነው፡፡ የሚወዳት ሲፈን ስለምትወልድለት ብቻ የሚጠላት ትሆናለች፡፡  
ልክ እንደ ካፍካ ሜታሞሪፎሲስ ከአንድ አካልነት ወደ ሌላ ልዩ  አካልነት የመለወጥ አባዜም ይጠናወተዋል፡፡  በአንድ ጊዜ ከአልአዛርነት (ታለ) ወደ ቹቹነት ይለወጣል፡፡ ነፀብራቅነት ይገለጣል። ያ ከጉለሌ የተነሳው ፍቅር፤ ሠራተኛ ሠፈር ድረስ ተጋግሎ ይዘልቅና መጨረሻው ግን ፍሬ አልባ ይሆናል፡፡  ፍቅር ሲደምቅ፤ እንደ አበባ ሲፈካና  ፍሬነቱ ሲጎመራ አናይም፡፡  ፍሬው በመፈጠሩ ወይም በማርገዟ ምክንያት ከጉለሌ ላትመለስ ትወጣለች፡፡  መጥፎ ቆሌ ሆና ትቀራለች፡፡
በፍቅር ስም ከአንዳንድ ህፀፆች የፀዳ አይደለም።  በተለይ አንዳንድ ቦታ ላይ የንባብ ፍሰቱን የሚያዘናጉሉ፤ ትርጉሙን የሚያደበዝዙ አሉበት (ገፅ 133)፡፡  በክፍል አንድ የተዘጋ ፋይል በክፍል ሁለት ካለ ምክንያት ሲደገም ትኩረትን ይፈታተናል።  አንዳንድ የሰደራቸው መጠይቆችና ምልልሶች  ወደ ተራ - ፈላስፋነት እንዳያወርደው መጠንቀቅ አለበት።
ክፍል ሦስት በትንቢተ ኢሳያስ ይደመደማል። ይደመደማል ከማለት ይልቅ ንግር (foreshadow)  ሆኖ ይጠናቀቃል፡፡ ምናልባትም ደራሲው ወደፊት ጀባ ሊለን የፈለገውን የፈጠራ ሥራ ጠቁሞን ይሆን? ጊዜ መልስ ይሰጠናል። Jean-Paul Sartre የተባለው ደራሲ፤ “ለምን እንጽፋለን?“  በሚለው ጽሑፍ አንድ ገጠመኙን ያጋራናል። አንድ ጀማሪ ሰዓሊ አስተማሪውን፤ “መቼ ይሆን ስዕሌ መጠናቀቁን የማውቀው?” ሲል ይጠይቀዋል።  አስተማሪውም፤ “በመደመም ስሜት ውስጥ ሆነህ ስዕልህን ስትመለከትና ለራስህ እኔ ነኝ ይህን የፈጠርኩት! ማለት ስትችል ነው” ብሎ መለሰለት ይለናል፡፡  ስለዚህ ዓለማየሁም “ፈጠርኩ እንጂ” “አላደርገውም!” እንዳይል የጥበብ አድባር ትታደገው።    

Read 4570 times