Monday, 05 December 2016 09:37

ቦብ ዳይላን በፕሬዚዳንት ኦባማ ግብዣ ላይ አልተገኘም

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የኖቤል ተሸላሚዎችን አነጋግረዋል
     የአመቱ የኖቤል የስነጽሁፍ ተሸላሚ በመሆን የተመረጠውና “ስራ ስለሚበዛብኝ በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ አልገኝም” በማለቱ የዓለማችን መገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተው አሜሪካዊው ድምጻዊና የሙዚቃ ግጥም ደራሲ ቦብ ዳይላን፣ ባለፈው ረቡዕ ከፕሬዚዳንት ኦባማ ጋር በዋይት ሃውስ እንዲገናኝ የቀረበለትን ግብዣ ባለመቀበል በስነስርዓቱ ላይ ሳይገኝ መቅረቱ ተዘግቧል፡፡
ኦባማ የዘንድሮ የኖቤል ተሸላሚ አሜሪካውያንን ከሽልማት ስነስርዓቱ በፊት በዋይት ሃውስ ለማግኘት ባለፈው ረቡዕ በያዙት ቀጠሮ፣ ሌሎች ተሸላሚዎች በስፍራው ቢገኙም ልማደኛው ዳይላን ግን ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ የውሃ ሽታ ሆኖ በመቅረት ዳግም የመገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ ሊሆን እንደበቃ የአሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ ይጠቁማል፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ ዳይላን ተሸላሚ መሆኑ ይፋ የተደረገ ሰሞን፣ “ከምወዳቸው ገጣሚያን አንዱ የሆነው ዳይላን ሽልማቱ ይገባዋል” በማለት የእንኳን ደስ አለህ መልዕክት ያስተላለፉለት ሲሆን  እ.ኤ.አ በ2012 ታላቁን የአገሪቱ የነጻነት ሜዳይ ሽልማት አበርክተውለት እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡
ምንም እንኳን ዳይላን ባይገኝም፣ ኦባማ በዕለቱ የፊዚክስ ኖቤል ተሸላሚዎቹን ዳንካን ሃልዳኔን  ማይክል ኮስተርሊዝን፣ የኢኮኖሚክስ ተሸላሚውን ኦሊቨር ሃርትን እንዲሁም የኬሚስትሪ ተሸላሚውን ሰር ጄ ፍሬዘር ስቶዳርትን  በዋይት ሃውስ በክብር ተቀብለው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈውላቸዋል፤ ለስራቸውም እውቅና ሰጥተዋቸዋል፡፡

Read 856 times