Monday, 05 December 2016 09:12

“ክፉ ቀን በሰጠኝ” የሚያስብል ጭንቀት አይድረስባችሁ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

  የሶማሌ ክልል ጉዞ - ከ ጉምራ ዙምራ
     (ክፍል- 2)
“አንድ ቀን  ስራ በዛብኝና ጫት ሳልቅም ውዬ ገብቼ ተኛሁ፡፡ እንደፈራሁት ሌሊት ዱካኮች መጥተው ሲጫወቱብኝ አደሩ”
“ምን አደረጉህ?”
“ሦስት ሆነው መጡና ልብስህን አውልቅ አሉኝ”
“እሺ ከዚያስ!”
“ሁለቱ እግሬን ወደ ላይ ይዘው ጭንቅላቴን ወደ መሬት ዘቀዘቁትና---የሶማሌ ጊርጊራ ታውቃለህ?”
“አዎ አውቃለሁ”
“ጊርጊራ ሙሉ ፍም ሆኖ፣ ትርክክ ብሎ የበሰለ የሺሻ እሳት ይዘው መጡና፣ በመቆንጠጫ እያነሱ በቂጤ ይከቱብኝ ጀመረ፤ ኡኡኡ እያልኩ ብጮህ ሊለቁኝ ነው፤ሲያሰቃዩኝ አደሩ.....” (ሳቅ)
***
በክፍል አንዱ የጉዞ ማስታወሻ፣ በወዳጃችን አብዱልአዚዝ ቤት እየተጫወትን እያለ ነበር ያቆምነው፡፡ እንቀጥል፡፡ አብዱል አዚዝ ምስራቅ ሓረርጌ በምትገኘው በጉርሱም ከተማ ከስራ ባልደረባዬ ቤተሰቦች ጋር በጉርብትና ያደገ ልጅ ነው፡፡ ጉርሱም ከጅግጅጋ ከተማ ጋር የምትዋሰነው የምስራቅ ሐረርጌ ዞን የመጨረሻዋ ከተማ ናት። ስለ ጉርሱም ከተማ የስራ ባልደረቦቼ ከነገሩኝ ውጭ አፈንዲ ሙተቂ የተባለው ጸሃፊ፤ “ኡመተ ፈናን ኡመተ ቀሽቲ ዲሬ ዳዋ” በሚለው መፅሃፉ ላይ እንዲህ እያለ ያነሳሳታል፡-
“ከሐረርጌ ከተሞች መካከል በጣም የሚበዙት ከመቶ ዓመት  የበለጠ እድሜ የላቸውም፡፡ ከጥንት ዘመናት ጀምሮ ለክፍለ ሃገሩ ህዝብ የንግድ፣ የትምህርትና የባህል ማእከል ሆና ስታገለግል የቆየችው ሐረር ናት፡፡ ከሐረር በመለጠቅ እድሜ ጠገብ ከተማ መሆኗ የሚነገርላት ደግሞ ጉርሱም ናት፤ “ፉኛን ቢራ”  ትባላለች በኦሮምኛ፡፡ “ከአፍንጫው አጠገብ” እንደ ማለት ነው፡፡ ከተማዋ ስያሜውን ያገኘችው ከታዋቂው “የቁንድዶ ተራራ” ጥግ የምትገኝ በመሆኗ ነው፡፡ ይህን ተራራ ከተማዋ ካለችበት ተኹኖ ሲታይ የሰው አፍንጫ የመሰለ ቅርጽ አለው፡፡ ለዚህም ነው ከግርጌው ያለችው ከተማ “ፉኛን ቢራ” (ከአፍንጫው አጠገብ ያለችው ከተማ) ተብላ የተጠራችው፡፡”
ጉርሱም የአውራጃ ከተማ በነበረች ጊዜ በወቅቱ የጃንሆይ ተወካይ አስተዳዳሪ የነበሩት መኳንንት፤ “ይህ ከተማ ሴቱም፣ ጥብሱም፣ ጉርሱም (ጉርሻው) ጣፋጭ ነው” አሉ ይባላል፡፡ ጉርሱም ቃሉ “ከጉርሻ” ተገኘ እንደ ማለት ነው፡፡ ይሔኛው እንግዲህ ባልደረቦቼ ስለ ከተማዋ ስያሜ ያሉት ነው፡፡
ታዲያ እነ አብዱልአዚዝ አብረው ሲያድጉ ወላጆቻቸው በቤቶቹ መሃከል ያለው አጥር እንዲፈርስ አድርገው፤ የአንዱ ቤት ልጅ ወደዚያኛው ቤት እየገባ የሚበላበት፣ የሚጫወትበት፤ የአንደኛው ቤት ወላጅ የዚያኛውን ቤት ልጅ ልክ እንደ ልጁ የሚመክርበት የሚቆጣጠርበት ዘመን ነበር ይላሉ- ሁለቱም ስለ ልጅነት ጊዜ ትዝታዎቻቸው መለስ ብለው ሲያወሩ፡፡
“የእነ አብዱልአዚዝ እናት ከሞተች በኋላ የእኔ እናት ነበረች እኛ የምንበላውን ለእነሱም እያበላች ያሳደገችን” አለኝ ባልደረባዬ፡፡ እውነትም የሚያስቀና የልጅነት ታሪክ ነው ያላቸው፡፡
አብዱል አዚዝ ጨዋታውን ቀጠለ፡፡ አንዱ ሱማሌ ጫት አቆማለሁ ብሎ የደረሰበትን የዱካክ ናዳ ሲናገር፡-
“አንድ ቀን  ስራ በዝቶብኝ ጫት ሳልቅም ዋልኩና ገብቼ ተኛሁ፤ ሌሊት ዱካኮች መጥተው ሲጫወቱብኝ አደሩ”
“ምን አደረጉህ?”
“ሦስት ሆነው መጡና ልብስህን አውልቅ አሉኝ”
“እሺ ከዚያስ!”
“ሁለቱ እግሬን ወደ ላይ ይዘው፣ ጭንቅላቴን ወደ መሬት ዘቀዘቁትና -- የሶማሌ ጊርጊራ ታውቃለህ?”
“አዎ አውቃለሁ”
“በጊርጊራ ሙሉ ፍም ሆኖ ትርክክ ብሎ የበሰለ የሺሻ እሳት ይዘው መጡና እሳቱን በመቆንጠጫ እያነሱ በቂጤ ይከቱብኝ ጀመረ፡፡ ኡኡኡ እያልኩ ብጮህ ሊለቁኝ ነው፡፡ ሲያሰቃዩኝ አደሩ.....” (ሳቅ)
“ሌላ ጊዜ ደግሞ እንዲህ ሆንኩላችሁ”
“ምን ገጠመህ?”
“እንዲሁ ስባዝን ዋልኩና ጫት ሳልቅም ቀኑ መሸ። ዱካክ እንደማያስተኛኝ እያወቅሁ በፍርሃት ገብቼ ተኛሁ”
“እና ዱካኮቹ መጡ?”
“መጡ?! መጡ ብቻ ሊያውም የተሳለ መጥረብያ ይዘው ነው እንጂ”
“እና ምን አደረጉህ?”
“አንዱ መጣና በዛ መጥረቢያ ጭንቅላቴን ቷ! አድርጎ ከፈተውና አንድ ፈረሱላ ሙሉ በርበሬ በአናቴ ጨመረና ሁለቱን ጆሮዎቼን ሲጠመዝዛቸው እንደ ወፍጮ ታታታታ እያለ ሞተሩ ተነሳ”
“ከዛስ? በናትህ የሚያዝናና ገጠመኝ ነው”
“ከዛማ በአፍና በአፍንጫዬ የተፈጨ የበርበሬ ዱቄት ይንቦለቦል ጀመረ፡፡ ኡኡኡ... ብዬ ብጮህ ማን ሊሰማኝ፡፡ እንደምንም ተፈጭቶ አለቀና እፎይ ተገላገልኩ ብዬ ስል--”ገና ነው ቁጭ በል!!”  አለኝ የዱካኮች አለቃ ጦሩን ይዞ --”
“ምን ቀረ ደግሞ?”  
“ሽርክት ነው እና አንድ ዙር መፈጨት አለበት” ብሎ ድጋሚ ሽርክቱን በርበሬ በአናቴ ጨመረብኝ። ወንድሜ ይሄ ሁሉ መዘዝ ከሚመመጣብኝ እንደምንም ቀዳዳ እየፈለኩ ብቅም ይሻለኛል” ብሎ እንደ አጫወተው ነገረን።
የአብዱልአዚዝ ጨዋታው አያልቅም፡፡ ነገር ግን ምሽቱ እየተጋመሰ መጣና መተኛት ግድ ሆነብን። ስለ ነገ ስራችን መቃናት ጸሎት ቢጤ አድርሼ ተኛሁ። በማግስቱ በጥዋት ገስግሰን ቢሮ ስንደርስ አንድም ሰራተኛ የለም፡፡
“ስራ የለም እንዴ?” ዘበኛውን ጠየቅን፡፡
“ሁሉም ሰራተኛ ፕሬዝዳንቱ ጽ/ቤት በአስቸኳይ እንዲገኙ ትላንት በሜሴጅ ስለተነገረ ሁሉም ወደዚያው ሄደዋል” መለሰ ጥበቃው፡፡
“እና ስንት ሰዓት ይገባሉ?”
“ዛሬ አርብም ስለሆነ ከሰዓት በኋላ ብትሞክር ይሻላል”
በዚህ መሃል ትላንት አግኝተነው የነበረ ኤክስፐርት ሲበር መጣና፤ “ቢሮ ኃላፊዋን ማግኘት ከፈለጋችሁ የፕሬዝደንቱ ስብሰባ 4፡00 ሰዓት ስለሚጀምር አብረን እንሂድና እኔ ላገናኛችሁ” አለን።
“ጥሩ ግባና እንሂድ”
“ስንት ወረዳ ላይ ነው የምትሄዱት?” በጉዞ ላይ ጠየቀን፡፡
“18 ወረዳዎች ላይ እንደርሳለን”
“ምን ያህል ቀን ትቆያላችሁ?”
“ቢያንስ አንድ ወር አካባቢ እንቆያለን”
“ታዲያ እኔ አብሬአችሁ እንድሄድ ለአለቃዬ ንገረውና እኔ የሁለት ወር አበል አሰርቼ አብሬ እሄዳለሁ”
እንደ መደንገጥም እንደ መገረምም እያሰኘኝ፤ “እኛ እንኳን በጀት የለንም፡፡ የምችል አይመስለኝም” አልኩ የአበሉ ክፍያ ጉዳይ ወደ እኛ እንዳይመጣ በመስጋት፡፡
“ስለ በጀት አትጨነቅ፤ የእኛ ቢሮ አለው፤ አንተ ብቻ ለአለቃዬ ንገረው”
እምቢ ብለው ስራዬን ያደናቅፍብኛል ብዬ ሰጋሁና “እሞክራለሁ” አልኩት “አሁን ግን ኃላፊዋን ታገናኘኘለህ አይደል?” ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡
“ምንም ሽግር የለም፡፡ ኢናንተ አቲገቡም ውጭ ቲጠብቃላችሁ ኢኔ ኢጠራታለው”
ይህን እያወራን ከከተማው ወጣ ብሎ ከተገነባው የፕሬዝዳንቱ ቤተመንግስትና ጽ/ቤት ደረስንና ወደ በሩ አቅጣጫ ስንመለከት መለዮ ከለበሱ ጥበቃዎች ውጭ በር ላይ ማንም የለም፡፡
“አንተ ገቡ እንዴ? ስንት ሰዓት ነው?” ጠየቀ፡፡
“3፡30 ሆኗል”
“ኡ... ምን ዋጋ አለው ገቡ ማለት ነው” አለ፡፡
“እና ምን ይሻላል?”
“ቆይ እስቲ እዚ ጋር አቁም አለ!!”
“መሃል መንገድ ላይ?” ጠየቅሁ፡፡
ሹፌሩ ዳር ለመያዝ የመኪናውን ፍጥነት ቀዝቀዝ ሲያደርግ በሩን በአየር ላይ ከፍቶ ወርዶ መንገዱን አቋርጦ ወደ በሩ ጉዞውን ቀጠለ፡፡ እኔም ሹፌሩም በመገረም በክላክስ ብንጠራውም “ሂዱ በቃ!!” ብሎን ነጎደ፡፡ ለካስ ተታለናል፡፡ አጅሬ ታክሲ አድርጎን ኖሯል። እየሳቅንም እየተናደድንም ከሰዓት በኋላ ከመመለስ ውጭ ሌላ አማራጭ ባለመኖሩ ወደ ማረፊያችን ተመለስን፡፡ ጭንቅ ሆነ።
የቢሮአችን የጥናቱ አስተባባሪ “ደብዳቤ አጽፎ ለመውጣት  ከሁለት ቀን በላይ መቆየት የለባችሁም!!” በማለት አጣብቂኝ ውስጥ ከቶናል። ቦታው ላይ በተጨባጭ ያለው ችግር ደግሞ በእኛ ችሎታ ብቻ የሚፈታ አይደለም፡፡ ነገና ከነገ ወዲያ ደግሞ ቅዳሜና እሁድ በመሆኑ ስራ የለም፡፡ ያለችን ብቸኛ ጊዜ አርብ ከሰዓት በኋላ ነች፡፡ ብቸኛ ዋስትናችን፡፡
“ዱአ ያስፈልጋል አሉ የቡድን አጋሮቼ!!” እውነት ሳይሆን አይቀርም አልኩ በልቤ፡፡ ለምሳ እረፍት ወደ አብዱልአዚዝ ቤት ጎራ አልንና 8፡00 ሲሆን ተመልሰን ወደ ቢሮ ሄድን፡፡
“አሁንስ ሀላፊዋ አልገቡም?” ጠየኩ፡፡
“እረ እንደውም”
“ምን ይሻለኛል ወይ ስልካቸውን ስጪኝና ልሞክር?”
“ትችላለህ” ብላ ሞባይል ቁጥሯን ሰጠችኝ። ቁጥሩን መትቼ ብደውል ስልኩ አይመልስም፡፡ ቢቸግረኝ የጽሁፍ መልእክት ላኩላት፡፡
ፈጣሪ ታረቀኝ መሰለኝ ለጸሃፊዋ ደውላ ከሌላ ባለሙያ ጋር እንድገናኝ አድርጋ ደብዳቤውን አስጨርሼ ወጣሁ፡፡ እፎይይይ.... አልኩ።
(ይቀጥላል)

Read 4299 times