Sunday, 13 November 2016 00:00

አቢሲኒያ ለተቀዳሚ ደንበኞች ማስተናገጃ ልዩ ቅንጫፍ ከፈተ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

    የተመሠረተበትን 20ኛ ዓመት እያከበረ ያለው አቢሲኒያ ባንክ፣ ረዥም ጊዜ አብረውት ለተጓዙ ቀደምት ደንበኞቹ ክብርና ላቅ ያለ አገልግሎት ለመስጠት ‹‹ሐበሻ›› የተሰኘ ልዩ ቅርንጫፍ ከፈተ፡፡ ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ ሌሎች ሁለት ቅርንጫፎችንም ለመክፈት በዝግጅት ላይ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
የዛሬ ሳምንት በቦሌ መንገድ ከሜጋ ሕንፃ ፊት ለፊት፣ ሐንሰም ኦፊስ ፓርክ ሕንፃ ላይ የተከፈተው የተቀዳሚ ደንበኞች ማስተናገጃ ‹‹ሐበሻ›› ቅርንጫፍ፤ ውብና ማራኪ ከመሆኑም በላይ አገልግሎት መስጫ፣ ልዩ የእንግዳ ማስተናገጃ፣ ሦስት የስብሰባ አዳራሾች ከተሟላ ቁሳቁስ ጋር፣ ምቹ የእንግዶች መቆያ፣ ማብሰያና መመገቢያ ክፍሎች አሉት፡፡
ቅርንጫፉ በተቀማጭ ሂሳብ፣ በብድርና በውጭ ምንዛሪ ለባንኩ የተሻለ ጥቅም የሚያስገኙ ተቀዳሚ ደንበኞችን በይበልጥ ለማገልገል የተቋቋመ መሆኑን የጠቀሱት የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ መሠረት ታዬ፤ በተጨማሪም ከባንኩ ጋር የረዥም ጊዜ ግንኙነት ያላቸው ደንበኞች፣ በመልካም ምግባራቸው በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነትና እውቅና ያላቸው ግለሰቦች፣ ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ እንዲሁም ከባንኩ ጋር የማደግ ቅን ፍላጎት ያላቸው ባለሀብቶችና ሌሎች ልዩ ጥቅም የሚገባቸው ደንበኞች ይስተናገዱበታል ብለዋል፡፡
‹‹ሐበሻ›› ቅርንጫፍ፣ ተቀዳሚ ደንበኞች በልዩ ሁኔታ እንዲጠቀሙበት የተቋቋመ በመሆኑ፤ ደንበኞች የስልክ ጥሪ በማድረግና በቅድሚያ በማሳወቅ የስብሰባ አዳራሾችን ለግል የሥራ ውይይት ሊጠቀሙ ይችላሉ ያሉት አቶ መሠረት፤ ባንኩ አስፈላጊ የሆኑትን እንደ ሻይ ቡና፣… የመሳሰሉ አገልግሎቶች ያቀርባል፡፡ ደንበኞች ለግል ሥራ እንቅስቃሴያቸው የሚያስፈልጋቸውን የኢንተርኔት፣ የስልክ፣ የፋክስና የመረጃ አገልግሎት ወደ ቅርንጫፉ በመጡበት በማንኛውም ጊዜ በነፃ መጠቀም እንዲችሉ ያመቻቻል ብለዋል፡፡ ቅርንጫፉ ተቀዳሚ ደንበኞች ወደ ባንኩ ማምጣት ሳያስፈልጋቸው ባሉበት ሆነው (ለምሳሌ በሥራ ቦታቸው ወይም በመኖሪያ ቤታቸው) የባንኩ አገልግሎት ሰጪ መኮንኑ በስፍራው በመገኘት አገልግሎት እንደሚሰጥ የጠቀሱት ሊቀመንበሩ፤ ገንዘብ የመሰብሰብ ወይም የመክፈል አገልግሎት በጥንቃቄና ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ ይሰጣል ብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ደንበኞች ወደ ቅርንጫፉ ከገቡበት ሰዓት አንስቶ እንግዶች መቀበያ ወይም መቆያ ክፍል ሆነው የግል ሥራቸውን እያከናወኑ፣ የቅርንጫፉ አገልግሎት ሰጪ መኮንን ያሉበት ሄዶ የሚፈልጉትን አገልግሎት ይሰጣቸዋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ተቀዳሚ ደንበኞች ስልክ ደውለው አዳራሽ እንዲዘጋጅላቸው በማሳወቅ ከባልደረቦቻቸው ጋር የስራ ውይይት፣ ከቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጁ፤ ከደንበኞች ግንኙነት ሥራ አስኪያጁና ከአገልግሎት ሰጪ መኮንኑ ጋር በፈለጉት ጊዜ የግል ውይይት ማድረግ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም አቢሲኒያ ባንክ ለደንበኞቹ ያለውን ተደራሽነት ለማስፋትና አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ባለው ቁርጠኝነት፣ ለገሀር በሚገኘው የባንኩ ዋና መስሪያ ቤትና ቦሌ በሚገኘው ቅርንጫፍ ሕንፃ ላይ እንደ ‹‹ሐበሻ›› ቅርንጫፍ ያለ የተቀዳሚ ደንበኞች አገልግሎት መስጫ ለመክፈት በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ቅርንጫፉ ከተገለጹት አገልግሎቶች በተጨማሪ ተቀማጭ ገንዘብ መቀበል፣ ሂሳብ መክፈት፤ ገንዘብ ወጪ ማድረግ፣ የሐዋላ አገልግሎትና የተለያዩ ክፍያዎችን መፈጸም፣…. የመሳሰሉ መደበኛ የባንክ አገልግሎቶችንም እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡

Read 1625 times