Sunday, 13 November 2016 00:00

ተቃዋሚዎች የትራምፕ መመረጥ ትርጉም ያለው ለውጥ አያመጣም አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

    የሪል እስቴት ከበርቴው ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ 45ኛው ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጣቸው በኢትዮጵያ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ እንደማያመጣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ገለፁ፡፡ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው፤ ለተመራጩ ፕሬዚዳንት ባለፈው ረቡዕ በመንግሥታቸው ስም የእንኳን ደስ ያለዎት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በምርጫው ብዙዎችን ያስደነገጠ ውጤት ያመጡት ዶናልድ ትራምፕ፤ በንግግሮቻቸው ዘረኝነትን የሚሰብኩ በመሆናቸውና በስደተኞች ላይ በያዙት አቋም በአብዛኞቹ የኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ለትችት ተጋልጠዋል፡፡
“ሰውየው በንግግሩ ቆጠብ ያለ አይደለም፣ የስደተኞችን ጉዳይ የሚገልፅበት መንገድ የጥላቻ ነው፡፡” የሚሉት የመድረክና የኦፌኮ አመራር አባል አቶ ሙላቱ ገመቹ፤ ምናልባት ከዚህ በኋላ የፖለቲካ ጥገኝነት ጠይቀው ወደ አሜሪካ የሚሄዱ ተቀባይነት ላያገኙ ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡
“ኢትዮጵያ በነፃ የቀረጥ ተጠቃሚነት ፕሮግራም ከዚህ በኋላ ምርቷን ወደ አሜሪካ ላታስገባ ትችላለች፤  እርዳታም እንደበፊቱ ላይኖር ይችላል” ብለዋል፤ አቶ ሙላቱ፡፡
በኦባማ ዘመን አሜሪካና ኢትዮጰያ በነበራቸው ወዳጅነት ልክ አጋርነታቸው ላይቀጥል እንደሚችል የጠቀሱት አቶ ሙላቱ፤ “በዲሞክራሲ ስም የሚገኘው እርዳታም ሊቆም ይችላል” በማለት ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡
ትራምፕ በአጠቃላይ ለአሜሪካ ቅድሚያ ሰጥተው የሚሰሩ አይነት መሪ ስለሆኑ ሌሎች አገራትን ለመርዳት ፍላጎት ላይኖራቸው ይችላል ብለዋል፡፡
“ትራምፕ እንደሚያሸንፍ ከመጀመሪያም ጠብቄ ነበር” ያሉት ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው፤ “ሰውዬው በተለይ ይዟቸው በመጣው አዳዲስ አስተሳሰቦች ተጎድተናል የሚሉ አሜሪካውያንን ቀልብ በመግዛት ተሳክቶለታል” ብለዋል፡፡
ከዚህ በኋላ ስደተኞች ላይ ጠበቅ ያለ ቁጥጥር ሊደረግ እንደሚችልና ህጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸው ሰራተኞች ከሀገሪቱ ሊባረሩ እንደሚችሉ የገመቱት አቶ ልደቱ፤ እርምጃው ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚጎዳ ቢሆንም ነገሩ መታየት ያለበት ከአሜሪካውያን ጥቅም አንፃር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት በበኩላቸው፤ ሪፐብሊካኖች ለኢህአዴግ የሚመቹ አይሆኑም፤ የሚመቸው የዲሞክራቶች ፀባይ ነው ይላሉ፡፡ በዲሞክራቶቹ የስልጣን እርከን ላይ የተቀመጡት አብዛኞቹ የአፍሪካ ጉዳይ ፖለቲከኞች የኢህአዴግ ወዳጅ እንደነበሩ የጠቆሙት ፖለቲከኛው፤ አሁን ሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ መመረጣቸውን ተከትሎ ኢህአዴግ እነዚህን ወዳጆቹን ሊያጣ ይችላል ብለዋል፡፡
“ትራምፕ ዘረኛ አስተሳሰብ ያለው ሰው ነው” የሚሉት የመኢአድ ፕሬዚዳንት ዶ/ር በዛብህ ደምሴ፤ የፖለቲካ እውቀትም የለውም ሲሉ ተችተዋል፡፡
“በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ዲሞክራቶችም ሆኑ ሪፐብሊካኖች እምብዛም ልዩነት ያለው አቋም የላቸውም ያሉት ዶ/ር በዛብህ፤ መጪው ጊዜ ምን ይሆናል የሚለውን በዝግታ ማየት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የመንግስት ኮሚኒኬሽን ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ፤ በግላቸው በሰጡት አስተያየት፤ ሪፐብሊካኖች በታሪካቸው ለኢትዮጵያ መልካም መሆናቸውን ጠቅሠው በትራምፕ ዘመን ኢትዮጵያን የሚጎዳ ነገር ይመጣል ብዬ አልጠብቅም ብለዋል፡፡

Read 1394 times