Sunday, 30 October 2016 00:00

ዘንድሮ በሜዲትራንያን ባህር ከፍተኛው የስደተኞች ሞት ተመዝግቧል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

                - ባለፉት 10 ወራት ብቻ 3 ሺህ 740 ስደተኞች ባህር ሲያቋርጡ ሞተዋል

      ሊጠናቀቅ የሁለት ወራት ጊዜ የቀሩት የፈረንጆች አመት 2016፣ የሜዲትራንያን ባህርን ለማቋረጥ ሲሞክሩ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉ ስደተኞች ቁጥር በታሪክ ከፍተኛው ደረጃ ላይ የደረሰበት መሆኑን አለማቀፉ የስደተኞች ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ባለፈው ማክሰኞ ጄኔቫ ውስጥ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ባለፉት አስር ወራት ብቻ 3 ሺህ 740 የተለያዩ አገራት ስደተኞች ሜዲትራንያን ባህርን ለማቋረጥ ሲሞክሩ ለሞት መዳረጋቸውንና ይህም ቁጥር በታሪክ ከፍተኛው መሆኑን ጠቁሟል፡፡
ባለፉት አስር ወራት ብቻ 327 ሺህ 800 ያህል የተለያዩ አገራት ስደተኞች በአስቸጋሪ የባህር ጉዞ አልፈው ወደ አውሮፓ መግባታቸውን የጠቆሙት የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ዊሊያም ስፒንድለር፤ሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመግባት የሚሞክሩ ስደተኞች ለሞት የመዳረግ እድላቸው በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩንም ገልጸዋል፡፡
ስደተኞች ባህር የሚያቋርጡባቸው ጀልባዎች ጥራታቸውን ያልጠበቁ መሆናቸውና ከመጫን አቅማቸው በላይ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ስደተኞች አሳፍረው መጓዛቸው እንዲሁም አስቸጋሪ የአየር ጸባይ የስደተኞቹን ለሞት የመዳረግ እድል ከፍ እንዳደረገው ተነግሯል፡፡ ቀሪዎቹ ወራት ለባህር ላይ ጉዞ ፈታኝ ወቅቶች ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በአመቱ ለሞት የተዳረጉ ስደተኞች ቁጥር በቀጣይም በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅም ኮሚሽኑ አክሎ ገልጧል፡፡

Read 1101 times