Sunday, 23 October 2016 00:00

ለፖለቲካዊ ችግሮች - ፖለቲካዊ ውይይት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

በአገሪቱ ለተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ ምሁራን፣ፖለቲከኞች፣ ዕውቅ ግለሰቦችና የአገር ሽማግሌዎች የመፍትሄ ሃሳብ የሚሉትን መሰንዘራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ሃሳባቸው ጆሮ
አግኝቷል ወይ ለሚለው እርግጠኛ መልስ መስጠት አይቻልም፡፡ ውጤቱን በሂደት የምናየው ይሆናል፡፡ አንድ ነገር ግን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ የመፍትሄ ሃሳቦቹ
ቀውሱ እልባት እስኪያገኝ ድረስ መቀጠል አለባቸው፡፡ መንግስት በአዲሱ ዓመት ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ መስጠት በመጀመር፣ሰላምና መረጋጋት ያሰፍናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡
፡ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህላችንም በሂደት እንደሚጎለብት እምነታችን ጽኑ ነው፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ለዛሬ የፖለቲከኞችን እንዲሁም
ጋዜጠኞችን አስተያየት አጠናቅሯል፡፡
የዚህ ውይይት ዓላማ፣በአገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ችግሮች ዙሪያ ሃሳቦችን በማንሸራሸር መፍትሄ ማፈላለግና መጠቆም ነው፡፡ በአገራችን ለተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ መፍትሄ
የሚሆን ሃሳብ ወይም አስተያየት አለን ለምትሉ ወገኖች መድረኩ ክፍት ነው፡፡


“ኢህአዴግ ያወጣቸውን ህጎች መለስ ብሎ ይፈትሽ”
እንግዳወርቅ ማሞ (የቀድሞ “አንድነት” ፓርቲ አባል)

የአሁኑ ችግር መነሻዎች ለህገ መንግስቱ ትኩረት ያለ መስጠት ጉዳይ ነው፡፡ ህገ መንግስቱ ላይ ያሉት ነገሮች መሬት ወርደው ቢታዩ ኖሮ፣ ለተፈጠረው ችግር ቀላል መፍትሄ ይገኝ ነበር፡፡ ህግ አውጪው፣ ህግ ተርጓሚውና ህግ አስፈፃሚው አካል አለመናበባቸው ሌላው ችግር ነው፡፡ በኔ እምነት ፍትህ የሰዎችን አኗኗር በማስተካከልና በማቃናት ረገድ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ ኢህአዴግ ባለፉት 25 ዓመታት ከተለያዩ ማህበረሰቦች ለሚነሱ ጥያቄዎች ወቅታዊና አግባብነት ያላቸው ምላሽ ቢሰጥ ኖሮ፣ ለወራት የማያባራ ተቃውሞ፣ አመጽና ሁከት አይከሰቱም ነበር፡፡ ሌላው የምርጫ ስርአቱ የፈጠረው ችግር ነው፡፡ ተቃዋሚዎች የሚከተላቸው ህዝብ እንዳለ ኢህአዴግ አይገነዘብም፤በዚህ የተነሳ በርካቶችን ሲያስኮርፍ ቆይቷል፡፡ ከሱ ውጪ ይህቺን ሀገር የሚመራ ሊኖር እንደማይችል ሲያስብ መቆየቱ፣ በሚከሰቱ ችግሮች መፍትሄ ፍለጋ ላይ ክፍተቶች እንዲፈጠሩ አድርጓል፡፡
በኔ እምነት ከዚህ በኋላ ችግሮችን ዘላቂ ጉዳት ሳያደርሱ በአጭሩ ለመቅጨት ከተፈለገ፣ ኢህአዴግ ያወጣቸውን ህጎች መለስ ብሎ ይፈትሽ፡፡ ህግ አውጪው፣ ህግ ተርጓሚውና ህግ አስፈፃሚው በስርአቱ መናበብ የሚችሉበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ በዚህ በኩል ጥልቅ ግምገማ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ በሌላ በኩል ፓርላማ ውስጥ ምንም የተቃውሞ ድምጽ የለም፡፡ በኢህአዴግ አባላት የተሞላ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት አመራሩ ስህተቶችን የሚያርምበት እድል አያገኝም፡፡ ይህ እድል ቢኖረው ኖሮ፣ይሄን ያህል ችግሮች አይገዝፉም ነበር የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከላይ ያለው አመራርና ከህዝቡ ጋር በቀጥታ ይገናኛል ተብሎ የሚታሰበው ከታች ያለው አመራር አለመናበብም ሌላው መፍትሄ የሚሻ ችግር ነው፡፡ ከላይ ያለው ለተፈጠሩ ጥፋቶች ይቅርታ ሲጠይቅ፣ከታች ያለው ይበድላል፡፡ ከታች ያሉት ከህዝብ ጋር የልብ ቁርኝት የላቸውም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እንዲሁም የመሬት ፖሊሲ ጉዳዮችም እንደገና መታየትና መፈተሽ አለባቸው፡፡

=============================

“የዲሞክራሲ አክራሪነት መፈጠር አለበት”

 አንሙት አብርሃም (ጋዜጠኛና ጦማሪ)

የችግሮቹ መነሻ በተለያየ መንገድ የሚገለፅ ነው፡፡ በዋናነት ሙሰኝነት የሀገሪቱ ችግር ነው፤ የመልካም አስተዳደር ጉድለት የሀገሪቱ አደጋ ነው ተብሏል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ በገዥው ፓርቲ በኩል አጋጥሟል የሚሉ ነገሮች አሉ፡፡ ከነዚህ ጋር ሊያያዙና ሊወራረሱ ችግሮች ዋነኛ ምክንት ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዘ የተከሰቱ ችግሮች አሉ፡፡
በዋናነት ትልቁ መሰረታዊ ተግባር ሊሆን የሚገባው የችግሮቹን መሰረታዊ መነሻ ማወቅ ነው። የሙስናና የመልካም አስተዳደር ወይም የአመራር ብልሽት ብቻቸውን ይሄን ችግር ላይፈጥሩ ይችላሉ። ስለዚህ መሰረታዊ ምንጩን በጥናት ማወቅ ወሳኝ ነው፡፡ የተከሰቱ ችግሮችን፣ የችግሩን ስፋትና የችግሩ ተሳታፊዎችን ማጥናትም ጉዳዩን ለመረዳት ይጠቅማል፡፡
የችግሩን ስፋት ለመረዳት ስንሞክር ከሞላ ጎደል የሁለት ክልሎች ችግር ነው፡፡ በሁለቱ ክልሎች ላይ የሚታየውም ሙሉ ለሙሉ ክልሎቹን የሸፈነ አይደለም፡፡ ለምሳሌ አማራ ክልል 10 ዞኖች አሉት፤ ችግሩ የሸፈነው ግን 4 ዞኖችን ነው፡፡ ስለዚህ ምክንያቶቹን በደንብ መረዳት ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ በኔ ግምት አክራሪ ብሄርተኝነት ባለባቸው አካባቢዎች ላይ ይሄ ችግር የለም፡፡ ስለዚህ እነዚህ አካባቢዎች ከሌላው በተለየ ለምን እንደዚህ ሆኑ? የችግሮቹ ተሳታፊዎችስ እነማን ናቸው? የሚለውን ማየቱ የችግሩን ምንጭ ተረድቶ ወደ መፍትሄ ለመድረስ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡
ከዚህ ቀደም የመልካም አስተዳደር ንቅናቄ ከተጀመረ በኋላ በእነዚህ አካባቢዎች በርካታ አመራሮች ከኃላፊነት ተነስተዋል፡፡ በእርግጥ ከስልጣናቸው የተነሱት ዋነኛ የመልካም አስተዳደር ችግር ፈጣሪዎች ናቸው ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ ችግሩ የመልካም አስተዳደር ነው ከተባለ ይሄ በሚገባ መጠናት አለበት፡፡ ይሄን ችግር በዋናነት ማን ነው የሚያንቀሳቅሰው? የሚለውንም በደንብ መለየት ያስፈልጋል፡፡ ተሳታፊው የትኛው የህብረተሰብ ክፍል ነው? የሚለውም ጥናት የሚያስፈልገው ነው፡፡ በኔ መረዳት ግን የችግሩ ዋነኛ መነሻ የአመራር ብልሽት ነው፡፡ የውጭ ኃይል ነው ብለን ጉዳዩን ወደ ውጪ አካላት መግፋት መልካም አይመስለኝም፡፡ መጀመሪያ ችግሮቹን በደንብ እንለያቸው፤ ያኔ መፍትሄውን ማግኘት ይቀላል። ለምሳሌ የአመራር ብልሽት አለ ከተባለ፣ ለህዝብ የቆመ አመራር መፍጠር ያስፈልጋል ማለት ነው። ለህዝቦች መብት የሚታገል አመራር ሙሰኝነትን ይዋጋል፡፡ ህዝብን ለማገልገል ይተጋል፡፡ ከዚህ አንጻር የአመራር ብልሽትን ማከም ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡
 በገዥው ፓርቲ በኩል የልማት አክራሪዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ የዲሞክራሲ አክራሪዎች ሊኖረው ይገባል፡፡ ከገዥው ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ከተቃዋሚዎችም፣ ከብዙኃን ማህበራትና ከሌሎች አካላትም መፍትሄዎች ሊመጡ ይገባል። ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከተሳዳቢነት ወጥተው ወደ አማራጭነት መምጣት አለባቸው፡፡ በሌላ በኩል ልዩነትን የሚያስተናግድ ሚዲያ ያስፈልጋል፡፡ ያኔ ልዩነትን በንግግር መፍታት ይቻላል ማለት ነው፡፡ ይህ ሲሆን ህዝብ የጉዳዩ ባለቤት ሆኖ ይንቀሳቀሳል፤ መፍትሄ ከውጭ መሻት አያሻውም፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሰከነ መንገድ ችግሮቹና መፍትሄዎቹ የሚጠኑበት፣ በጋራ የምንወያይበት ጊዜ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ ሀገር ሰፊ የችግር ውርስ ያለበት ሀገር ነው፤ ከውርሱም በላይ ደግሞ ሰፊ ዘመን አመጣሽ ችግር አለበት፡፡ ችግሮቻችንን ለመፍታት መነጋገር፣ መወያየት መሰረታዊ ጉዳይ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

==============================

“አገራችን ሰፋፊ ልቦች ያስፈልጓታል” ደሳለኝ ሥዩም ደራሲ

እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ፣ እናት ሀገራችን አሁን ስላለችበት ሁኔታ አስባለሁ፡፡ ሕዝብ መንግሥትና ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ደጋግመው እንደሚሉትና ብዙዎቹም እንደሚስማሙበት፣ለዚህ ዓይነቱ ተቃውሞና ቁጣ ዋነኛው መነሾ ዘርፈ ብዙ የሆነ የሕዝብ ፍላጎትና ጥያቄ አለመሟላት ነው። የፍትህ እጦት፣ የዴሞክራሲ እጦት፣ የነጻነት እጦት፣ የሥራ እጦት፣ የእኩልነት እጦት፣ የእውቅና እጦት፣ የሥልጣን እጦት፣ የሚዲያ እጦት ወዘተ--ሕዝብን ያማረሩ ችግሮች መሆናቸውን ገዥውም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይስማሙበታል፡፡ የእነዚህ ሁሉ ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች ከሥር ከሥር መልስ አለማግኘት ሰፊ ለሆነ ሕዝባዊ ቁጣ መከሰት አይነተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
ሕዝብ ብሶቱን ለመግለጽና ቁጣውን ለማሰማት ሰልፍ ወጥቷል፣ በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ አድርጓል፣ መንገድ ዘግቷል፣ መኪና አቃጥሏል፣ ፋብሪካ አውድሟል፣ የግለሰቦችን ቤት አፍርሷል፣ ወዘተ፡፡ ብሶቱን መግለጹ ስህተት ባይሆንም የግልም ሆነ የመንግስት ንብረት ሲያወድም በቀጥታ የሚጎዱት ሀገርና ህዝብ ናቸው፡፡ አንድ ወዳጄ እንደሚለው፤ “የመኪና ፋብሪካ በሌለበት ሀገር ውስጥ መኪናን ማቃጠል ኪሳራው ብዙ ነው።” በሌላ በኩል መንግስት፤ የህዝብ ቁጣዎችን ለመቆጣጠር የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅሟል፡፡ ማሰር፣ በአስለቃሽ ጭስ መበተን፣መሳሪያ መተኮስ ----- አሁን ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ፡፡ ልክ በህዝቡ በኩል እንደታየው በመንግስትም በኩል የሚጎዱ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡
እኔ እንደሚመስለኝ ሀገራችን አሁን ሰፋፊ ልቦች ያስፈልጓታል፡፡ መንግስት ሰላምና መረጋጋት በማስፈን ለህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁን አስረድቷል፡፡ የሚሰጠው ምላሽ ሰፊ ልብን ይጠይቃል፡፡ ብዙ ብልሃትን ይጠይቃል። ብዙ ጥበብን ይጠይቃል።  በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሰፊ ልብ ያስፈልጋቸዋል፤ ሀገርን ወደ አንድነት፣ ህዝብን ወደ ፍቅር መምራት የሚያስችል ሰፊ ጥበብ፣ ሰፊ ብልሃት። የአገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶችም ከአድርባይነትና ከፖለቲካ ቁማር ወጥተው ህዝብን በሃቅና በጥበብ ለመምራት ሰፊ ልብ ያስፈልጋቸዋል፡፡ መንጋው በበረት እያለ ያንቀላፋ እረኛ፣ መንጋው በረቱን ጥሶ ከወጣ በኋላ መልሶ መሰብሰቡ ፈተና ይሆንበታል፡፡ ሕዝብም ቢሆን በጭፍን መንጎድ የለበትም፡፡ ጥያቄውን በሰከነና በሰለጠነ መንገድ ከማቅረብ ባሻገር የገዛ አገሩን ለማውደም መንቀሳቀስ አይገባውም፡፡   

=================================

“ያኮረፉ አካላት እርቅ ማውረድ አለባቸው”
አጥናፍ ብርሃኔ (ጦማሪ

 የችግሮቹ መነሻዎች በርካታ ቢሆኑም የፍትህ እጦት አንዱ ይመስለኛል፡፡ የኢኮኖሚ ፍትሃዊ ተጠቃሚ አለመሆን ሌላው መነሻ ነው፡፡ “ወረዳ ተወሰደብኝ” የመሳሰለው ጉዳይ እንደ መነሻ ምክንያት ሆነ እንጂ ዋናው ጥያቄ አይደለም፡፡ ጥያቄው ታፍኖ በመቆየቱ ነው በዚህ መልኩ መተንፈስ የጀመረው። ገዥው ፓርቲ ደግሞ ችግሩን በጊዜው መፍታትና መልስ መስጠት አልቻለም ነበር፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከ ማወጅ የደረሰውም አስቀድሞ ጥያቄዎችን ከስር ከስር መፍታት ባለመቻሉ ነው፡፡
አሁንስ ከዚህ በኋላ ምን እድል አለን? ምን ብናደርግ ነው ከዚህ አዙሪት መውጣት የሚቻለው? ወደ መፍትሄ የሚወስደንን አቅጣጫ ስናማትር፣ ከየትኛውም ወገን በቅንነት የሚሰነዘሩ የመፍትሄ ሃሳቦችን የሚቀበል አካል መኖር አለበት። መፍትሄው ግልፅ ነው፡፡ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ መሆን፡፡ እነዚህ የመፍትሄው መጀመሪያዎች ናቸው፡፡ ዲሞክራሲያዊ የሆነ ውይይትና ድርድር ብቻ ነው ወደ ዘላቂ መፍትሄ የሚወስደን፡፡ ይሄ ደግሞ ያለ ምንም አፈና ነው መደረግ ያለበት፡፡ ሃሳብን የሚገድብ ምንም ነገር ሊኖር አይገባም፡፡ የምርጫ ስርአቱ መሻሻል አለበት ተብሏል፡፡ ለእኔ ደግሞ ከምርጫ ስርአቱም በላይ የምርጫው ሂደት ነው መስተካከል ያለበት፡፡ የውይይት መድረኮች ሲዘጋጁም የሚፈለጉ ሰዎችን ብቻ አቅርቦ፣ ሌላውን አግልሎ ከሆነ፣ ብዙ ያኮረፉ አካላትን ወደ መድረኩ ማምጣት አይቻልም፡፡ በመጀመሪያ ሁሉም ያኮረፉ አካላት እርቅ ማውረድ አለባቸው፡፡ ከዚያ በኋላ ለሀገሪቱ የሚጠቅማትን የጉዞ አቅጣጫ፣በውይይትና በድርድር መተለም ይቻላል፡፡





Read 1735 times