Sunday, 23 October 2016 00:00

የህትመት ኢንዱስትሪው በከፍተኛ አደጋ ውስጥ ነው ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

ለሚዲያዎች መስፋፋትና እድገት ማነቆ ሆኗል

በሃገሪቱ ያለው የህትመት ኢንዱስትሪ በከፍተኛ አደጋ ውስጥ መሆኑን አንድ ጥናት ያረጋገጠ ሲሆን ለሚዲያዎች መስፋፋትና እድገትም ማነቆ እየፈጠረ ነው ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ አሳታሚዎች አታሚዎች ማህበር ከትናንት በስቲያ በሸራተን አዲስ ሆቴል ባዘጋጀው የግማሽ ቀን ወርክሾፕ ላይ በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር የቀድሞው ፕሬዚዳንት በአቶ ጌታቸው በለጠ የቀረበ ጥናት እንዳመለከተው፤መንግስት ለህትመት ኢንዱስትሪው ምንም አይነት ድጋፍ ስለማያደርግ ዘርፉ ከማደግ ይልቅ እየቀጨጨ ነው፡፡  
በጥናቱ ላይ ተሳታፊ ከነበሩ የኢንዱስትሪ አንቀሳቃሾች በተሰባሰበ መጠይቅ፣ለህትመት ኢንዱስትሪው የሚደረግ የመንግስት ድጋፍ 0 % መሆኑ ተመላክቷል፡፡ መንግስት በሁለቱም የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዶቹ ኢንዱስትሪውን በተመለከተ ያስቀመጠው እቅድ፣ ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል ብለዋል - ጥናት አቅራቢው፡፡
የህትመት ኢንዱስትሪው ትልቁ ተግዳሮት፣ ተደራራቢ ታክስ እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡ በንጉሡ፣ በደርግና በአሁኑ መንግስት በህትመት ኢንዱስትሪው ላይ የታዩ ለውጦች በጥናቱ የተዳሰሱ ሲሆን በንጉሡ ዘመን የተሻለ የህትመት ኢንዱስትሪ መስፋፋት ታይቶ ነበር ተብሏል፡፡
በተለይ እንደ ማክሚላን ቡክስ፣ ኦክስፎርድ የመሳሰሉ የውጭ ትላልቅ የህትመት ኩባንያዎች በኢንዱስትሪው ተሳታፊ የነበሩ መሆናቸው መልካም አጋጣሚ እንደነበር በጥናቱ ተጠቁሟል። በደርግ ዘመን ትልቁ የኢንዱስትሪ ማነቆ ሳንሱር ቢሆንም ለማተሚያ ቤቶች ስራ ማስኬጃ በልዩ ትኩረት ከፍተኛ በጀት ይመደብ ነበር ያሉት ጥናት አቅራቢው፤ መፃህፍትና ጋዜጦችም በብዙ ኮፒ ታትመው ይሸጡ እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡  
በደርግ ስርአት “አዲስ ዘመን” እና “ሄራልድ” ጋዜጦች በቀን ከ40 ሺህ እስከ 50 ሺህ ኮፒ ይታተሙ የነበረ ሲሆን ዛሬ እነዚህ ጋዜጦች ከ10 ሺህ እስከ 16 ሺህ ኮፒ ብቻ እንደሚታተሙ ተጠቅሷል፡፡ በደርግ ዘመን አንድ መፅሐፍ እስከ 30 ሺ ኮፒ ይታተም ነበረ፤ በአሁኑ ወቅት 95 በመቶ የሚሆኑ መፅሐፍት በአማካይ ከ1ሺህ - 3ሺህ ኮፒ ብቻ እንደሚታተሙ ጥናቱ አመልክቷል፡፡ ለዚህ ደግሞ የማተሚያ ቤቶች አቅምም ሆነ ጥራትም አለመጎልበት፣ በወረቀትና በሌሎች የማተሚያ ግብአቶች ላይ የተጣለው ከፍተኛ ታክስና የባለሙያዎች እጥረት ለኢንዱስትሪው መቀጨጭ አስተዋፅኦ ካደረጉ ጉዳዮችተጠቃሽ ናቸው፡፡  የህትመት ዋጋ መናርና መንግሥት ዘርፉን አለመደገፉ፣ በአንድ ወቅት በርካታ መፅሐፍትን በማሳተም የሚታወቁ ታላላቅ የህትመት ኩባንያዎችን ከስራ ውጪ እያደረገ መሆኑን ጥናት አቅራቢው ጠቆመዋል። በምሳሌነትም ሻማ ቡክስ የተሰኘው አሳታሚ ድርጅት፣ከፊሎቹን የመፅሐፍት መደብሮቹን እስከ መዝጋት መድረሱን፣ ሌሎችም ከማተሚያ ቤትነት ወደ ፎቶ ቤትነት የተቀየሩ እንዳሉ ተጠቁሟል፡፡
መንግስት ፊት የነሳው የሀገሪቱ ኢንዱስትሪ የህትመት ዘርፍ መሆኑን በአፅንኦት የጠቆሙት አጥኚው፤ የትምህርት ሚኒስቴርን የመማሪያ መፅሀፍት እንኳ ለማሳተም በወጣው አለማቀፍ ጨረታ በሀገሪቱ አሉ ከሚባሉ 400 ያህል ማተሚያ ቤቶች አንዱም እንኳ በስራው መሳተፍ ባለመቻሉ ከእንግሊዝ፣ ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ከህንድ፣ ከቻይና እና ኡጋንዳ የመጡ ኩባንያዎች ጨረታውን አሸንፈው መፅሐፍቱን እንዳሳተሙ ጠቁመዋል፡፡ በአለማቀፍ ደረጃ የህትመት ኢንዱስትሪ 15 ቢሊዮን ዶላር በማንቀሳቀስ፣ መሪ ከሆኑ ኢንዱስትሪዎች አንዱ መሆኑን የጠቆመው ጥናቱ፤ ኢትዮጵያ እንኳን በአለም በአፍሪካ የህትመት ኢንዱስትሪ እንኳ ተጠቃሽ ሳትሆን መቅረቷን አመልክቷል፡፡
የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ተካ አባዲ “የኢትዮጵያ የህትመት ኢንዱስትሪ በመከራ ላይ ያለ፣ ያልሞተ፣ ለመዳን ግን መድሃኒት የሚያስፈልገው ሆኖ አግኝተነዋል፡፡” ያሉ ሲሆን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው፤ በዘርፉ ያሉት ማነቆዎች ተለይተው መፍትሄ የሚሹ መሆናቸውን በመግለፅ፣ መንግስት ኢንዱስትሪውን ከውድቀት ለመታደግ የተቻለውን ያደርጋል ብለዋል፡፡

Read 1236 times