Sunday, 16 October 2016 00:00

ጂማ ዩኒቨርሲቲና ሉሲ አካዳሚ በጋራ ትምህርት መስጠት ሊጀምሩ ነው

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

ጅማ ዩኒቨርሲቲና ሉሲ አማካሪ ኢንጂነርስ ኃ.የተ.የግ.ማ በጋራ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት ዘመኑ በደረሰበትና ጊዜው በሚጠይቀው ዘዴ በኢንተርኔት (e-learning) መስጠት ሊጀምሩ ነው፡፡
የሁለቱ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከትናንት በስቲያ በሠራዊት መልቲ ሚዲያ ሲኒማ አዳራሽ በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ ወቅቱ በሚጠይቀው የማስተማር ዘዴ በመጠቀም የትምህርት ተደራሽነትን በማስፋት፣ በአነስተኛ ወጪ ጥራት ያለውና ለተማሪው ምቹ በሆነ መንገድ ትምህርት መስጠት ለአገራችን ፈጣን እድገት ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
የሉሲ አማካሪ ኢንጂነርስ ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ሀብታሙ ዘለለው፣ ተቋሙ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን በአገራችን የከፍተኛ ትምህርት መስክ ፈር ቀዳጅ በሆነ የማስተማር ዘዴ በ6 መሰረታዊ ዘርፎችና በ23 የኢንጂነሪንግ የትምህርት መርሐ ግብሮች ለሁለተኛ ምረቃ በማስተማር ሀገራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀዋል፡፡
ተቋሙ ትምህርቱን የሚሰጠው ከፊት ለፊት ማለትም ከገጽ ለገጽ ማስተማር ዘዴ በተጨማሪ በአብዛኛው  (e-learning) በመሆኑ ኢንተርኔት ያለው ማንኛውም ሰው ባለበት ሆኖ ሥራውን ሳይበድል፣ ከቤተሰቦቹ ከላይ፣ ባመቸው ጊዜ፣ በራሱ ፍጥነትና በዝቅተኛ ክፍያ ጥራት ያለው ትምህርት በውጭ አገርና በአገር ውስጥ ካሉ ልምድ ካካበቱ መምህራን እንደሚያገኝ ገልጸዋል፡፡
ትምህርቱ በቪዲዮ፣ በሚዲያ፣ በምስል፣ በአኒሜሽን፣ በኦንላይን ዳታ ቤዝ፣ በጆርኖሎች የሚቀርብ ሲሆን የዓለም አቀፍ ተደራሽነትን፣ ለማጎልበት በሁሉም የትምህርት ዘርፎች ፕሮፌሽናሎችና ኤክስፐርቶች በኢንተርኔት ሥልጠናዎችን፣ የአቅም ግንባታ ፕሮግራሞችን፣ ኮንፈረንሶችን፣ ሲምፖዚየሞችንና ሴሚናሮችን እንደሚሰጡ ታውቋል፡፡
በአሁን ወቅት ጅማ ዩኒቨርሲቲ ከ60 የማያንሱ የቅድመ ምረቃና (የመጀመሪያ ዲግሪ) ከ150 በላይ የድህረ ምረቃ (ሁለተኛ ዲግሪና ዶክትሬት) ፕሮግራም እየሰጠ ነው ያሉት የዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ልማትም ምክትል ዳይሬክተር አቶ ኮራ ጡሹኔ፣ ከሉሲ አካዳሚ ጋር ለመስጠት የተስማማነው ትምህርት ዓላማ የድህረ ምረቃ አቅምን ማሳደግና እያጋጠመ ያለውን የትምህርት ጥራት ችግር ለመፍታት ከተለመደውና ባህላዊ አሠራር ተላቅቀን፣ ዘመናዊ በሆነ ፈጠራዊ (Innovative) ስልት መውጣት ነው ብለዋል፡፡
የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚታወቀው በህክምናና በጤና ትምህርት ነው፡፡ አሁን እንጂነሪንግ ውስጥ ምን አስገባው? የሚሉ ካሉ ትክክል ናቸው የሚሉት አቶ ኮራ፤ ለአራት ዓመታት ኤቢኤች ከተባለ ድርጅት ጋር በቢዝነሱ ላይ ስንሰራ ነበር፤ አሁን ደግሞ ከሉሲ አማካሪ ኢንጂነርስ ጋር ለብዙ ዓመታት የካበተ ልምዳችንን በመጠቀም በኢንጂነሪንግ ዘርፍ ልንሠራ ነው፡፡ ወደፊት ደግሞ በሌላ ዘርፍ ከሚመጣ ድርጅት ጋር እንሠራለን ብለዋል፡፡
ትምህርት መስጠት የሚጀመረው በሚቀጥለው ዓመት እንደሆነም የጠቀሱት ዶ/ር ሀብታሙ፤ ምዝገባው የሚካሄደው በኢንተርኔት (ኦን ላይን) ቢሆንም ጅማ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ምዝገባ ልምድ ስላለው በዚያ በኩል ነው፡፡ የተመዘገበ ተማሪ ሁሉ እንቀበልም፡፡ የመግቢያ ፈተና እንሰጣለን፡፡ ያንን ያለፉትን ነው ተቀብለን የምናስተምረው በማለት አስረድተዋል፡፡
ጅማ ዩኒቨርሲቲና ሉሲ አማካሪ ኢንጅነርስ በጋራ ለመስራት የፈረሙት ስምምነት የግልና የመንግስት ክንፍ ግንኙነት ለማጠናከር ከፍተኛ ድርሻ አለው ያሉት ዶ/ር ሀብታሙ፣ በኦንላይን ትምህርት መስጠቱ ለትምህርት ጥራት ዋነኛ ግብአት ከመሆኑም በላይ መንግሥት የተያያዘውን የኢንጂነሪንግና የቴክኖሎጂ ትምህርት ያጠናክራል፡፡ በዘርፉም የመምህራንንና የምርምር አማካሪዎችን እጥረት ይቀርፋል፣ በርካታ ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት ይረዳል፡፡ የውጭ አገር ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው የመማር ፍላጎታቸው እንዲያድግ ከማድረጉም በላይ ምሩቃኑ የሚያገኙት ማስረጃ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው ስለሆነ በየትኛውም ስፍራ ተወዳዳሪ ለመሆን ያስችላቸዋል በማለት አብራርተዋል፡፡

Read 1732 times