Sunday, 09 October 2016 00:00

“ኤክሰል አሬንጁስ” እና “ማርች ማንጎጁስ” ለጤና ጎጂ መሆናቸው ተገለጸ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(7 votes)

   ፓሲፊክ ኢንዱስትሪዎች ኃ.የተ.ማ የሚያመርታቸው “ኤክሰል አሬንጅ ጁስ”ና “ማርች ማንጎ ጁስ” ለጤና ጎጂ መሆናቸውን የኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
ባለሥልጣኑ ሰሞኑን ለዝግጅት ክፍላችን ለድርጅታችን በላከው ደብዳቤ፣ ከኅብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሠረት፤ ምርቶቹ ላይ በተደረገ የላቦራቶሪ ፍተሻ ለጤና ተስማሚ አለመሆናቸው በመረጋገጡ፣ ለኅብረተሰቡ ጤና ጎጂ መሆናቸውን ጠቁሞ፣ ድርጅቱ ከዚህ በፊትም በተመሳሳይ ችግር ምርቱ ገበያ ላይ እንደይውል መደረጉንና ከገበያም እንዲሰበሰብ መደረጉን፣ አሁንም ተመሳሳይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን አመልክቷል፡፡
አምራች ድርጅቱ ከባለሥልጣን መ/ቤቱ ምንም ዓይነት የብቃት ማረጋገጫ ያልተሰጠው በመሆኑ ምርቱ ተመርምሮ የሀገሪቱን የምግብ ደህንነትና የጥራት መስፈርት የማያሟላ፣ እንዲሁም ለጤና ጎጂና አደገኛ መሆኑን በማረጋገጥ እነዚህን ምርቶች ማንኛውም ሰው እንዳይጠቀም አበክሮ አሳስቧል፡፡ ባለሥልጣን መ/ቤቱ በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት፤ እነዚህን የተከለከሉ ምርቶች ሲሸጥ፣ ሲያጓጉዝ፣ ሲያከፋፍል የተገኘ ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ድርጅት ላይ እርምጃ እንደሚወስድና አጥፊዎቹን በሕግ የሚጠይቅ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ኅብረተሰቡ ይህን መሰል ሕገ-ወጥ ተግባራትና ማንኛውም ሕገ ወጥ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና አገልግሎቶች ሲያጋጥሙት፣ በአካባቢው ላለ የሕግና የጤና ተቆጣጣሪ አካላት እንዲጠቁም ያሳሰበው ባለስልጣን መ/ቤቱ፤ በፌደራል ደረጃ በነፃ የስልክ መስመር 8482 በመደወል፣ ሕገ-ወጦችን በጋራ እንከላከል ብሏል፡፡

Read 4046 times