Monday, 03 October 2016 08:08

የአሜሪካ 4 የጫማ አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች በኢትዮጵያ ጉብኝት አደረጉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

     በአሜሪካ 80 ከመቶ የጫማ ፍላጎት የሚያሟላው የጫማ አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች ማኅበር (ኤፍ ዲ አር ኤ) በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት ያደረገ ሲሆን ከትናንት በስቲያ በኢሲኤ አዳራሽ በቆዳ ዘርፍ ከሚመለከታቸው ኃላፊዎች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
ኤፍዲአርኤ የጫማ ምርቶችን የሚገዛው ከምስራቀው ኤዥያ አገሮች ከካምቦዲያ፣ በርማ፣ ላኦስ፣ … ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የሜድ ኢን ኢትዮጵያ ኩባንያ ባለቤት ወ/ሮ ቤተልሄም ጥላሁንና ኢንተርፕራዝ ፓርትነርስ ባደረጉት ያላሰለሰ ጥረት መሆኑን የኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ የኮሙኒኬሽን አማካሪ አቶ ዳዊት ከተማ ገልጸዋል፡፡
175 አባላት ያሉት ማኅበሩ ባለፈው ማክሰኞ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ጣቢያ ሲደርስ በውጭ ጉዳይ ሚ/ር አቀባበል የተደረገለት ሲሆን፣ 11 የታወቁ ብራንድ ያላቸው አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች ከፍተኛ የስራ አመራሮች ከቡድኑ ጋር መምጣታቸው ታውቋል፡፡ ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው በአገሪቱ ያለውን የጫማ ሁኔታና ከኢትዮጵያ ጫማ ቢገዛ ምን ጥቅም እንደሚያገኝ ለማጥናት ሲሆን ባለፈው ረቡዕ የቆዳ አምራቾችን፣ የቆዳ ማልፊያ ፋብሪካዎችን፣ የጫማ ፋብሪካዎችን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን የጭነት ተርሚናል መጎብኘቱ ታውቋል፡፡
በጉብኝታቸው ወቅት ባዩት ነገር፣ በተደረገላቸው አቀባበልና መስተንግዶ መደሰታቸውን የገለጹት የኤፍ ዲ አር ኤ የመንግስትና የተቆጣሪ ጉዳዮች ዳይሬክተር ሚ/ር ቶማስ ክሮኬት ባለፈው ዓመት አሜሪካ 2.4 ቢሊዮን ጥንድ ጫማዎች ከውጭ መግዛቷን ተናግረዋል፡፡
አሜሪካኖቹ የጫማ ነጋዴዎች ኢትዮጵያን የወደዱበትን ምክንያት አቶ ዳዊት ሲገልጹ ወደ አሜሪካ ጫማ ሲገባ ትልቁ ወጪ ቀረጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአጉዋ አባል ስለሆነች ምንም ቀረጥ ሳትከፍል ታስገባለች፡፡ በከፊልና በሙሉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ስላል ተወዳዳሪ የሆነ የጉልበት ዋጋ በኢትዮጵያ ስላለና በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ዋጋ እጅግ በጣም ርካሽ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ ኢንተርፕራዙ ከአንድ ወር በፊት በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ያለውን የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ለመቅረፍ 60 ሺህ ሰዎች ለማሰልጠን መፈራረሙን ጠቅሰው ወደ ጫማ ኢንዱስትሪ የሚገቡ የአሜሪካ ኩባንያዎች ካሉ፣ ሊገጥማቸው የሚችለውን የሰው ኃይል እጥረት ለመቅረፍ ኢንተርፕራይዙ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱትሪ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ጥሬ ቆዳ መላክ አቁሞ እሴት እየጨመረ ያለቀለት ጫማ፣ ጓንት፣ ቀበቶ፣ የቆዳ አልባሳት፣ … ወደ ውጭ እየላከ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ዳዊት፣ በኤፍ ዲ አር ኤ በኩል ወደ አሜሪካ ገበያ መግባት በጣም ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ስለዚህ ሁኔታዎችን የበለጠ ማመቻቸትና ጠንክረን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

Read 1209 times