Monday, 03 October 2016 00:00

በሦስት ዘርፎች መጻሕፍት ተወዳድረው ሊሸለሙ ነው

Written by 
Rate this item
(9 votes)

     ኖርዝ ኢስት ኢንቨስትመንት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና ከብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ ጋር በመተባበር በየዓመቱ የሚካሄድ ‹‹ሆሄ የኢትዮጵያ የሥነ ጽሁፍ ሽልማት›› ፕሮግራም ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡
የሽልማት ዝግጅቱ ዓላማ በሀገራችን የንባብ ባህል እንዲጎለብት ማስቻል፣ በየዓመቱ የሚታተሙ መጽሐፍትን እንዲተዋወቁና የተሻሉት ደግሞ በተሸላሚነት እውቅና እንዲያገኙ እንዲሁም በልጆች ንባብ ላይ የተለየ ትኩረት በማድረግ ድጋፍ መስጠት ነው፡፡
የፈጠራ ፅሁፍ ስራዎቻቸውን ላበረከቱ ደራሲያንና ጸሐፍት እውቅና ከመስጠት ባለፈ የንባብ ባህል እንዲስፋፋ፣ በተፃፉ መፅሃፍት ላይ ህብረተሰቡ እንዲወያይባቸው ሁኔታዎችን የሚያመቻቹ የንባብ ክበባት እንዲፈጠሩ እንዲሁም በየጊዜው የሚታተሙ መፅሀፍት ላይ ሂስና ትንታኔ በመስጠት ለመላው ህብረተሰብ የንባብ ትሩፋቶችን በማጋራት ለሚሰሩ ሀያሲያን የሽልማት ፕሮግራሙ እውቅና የሚሰጥ ይሆናል፡፡
“ሆሄ የስነፅሁፍ ሽልማት” ፕሮግራም በዋነኛነት ሶስት የውድድር ዘርፎች የሚኖሩት ሲሆን እነዚህም የረጅም ልብ ወለድ መጻህፍት፣ የስነ ግጥም መድበሎችና የልጆች መጻህፍት ናቸው። ተወዳዳሪ መፃህፍት በዳኞች ኮሚቴ አማካይነት በተዘጋጀላቸው መስፈርቶች መሰረት የሚመዘኑ ሲሆን ውድድሩ በዳኞች ኮሚቴ ከሚሰጠው ውጤት በተጨማሪ በአንባቢያን ነፃ የስልክ መልእክትና በድረ ገፅ ኦን ላይን ከአንባቢያን የሚሰጠው ድምፅ ተደምሮ አጠቃላይ ውጤቱ የሚታወቅ ይሆናል፡፡
የውድድሩ አሸናፊዎች የዋንጫና የገንዘብ ሽልማት የሚያገኙ ሲሆን በተጨማሪም በአለም አቀፍ የኪነ ጥበብ ጉባኤዎች ላይ የመሳተፍ እድል እንዲያገኙ ይደረጋል። በሽልማት ፕሮግራሙ በንባብ ባህል፣ በመጻሕፍት አቅርቦት፣ በትምህርት ቤቶች የንባብ ክበባት ዙሪያ የሚዘጋጁ አውደ ጥናቶችና የኪነ ጥበብ ምሽቶች የሽልማት ፕሮግራሙ አካል ይሆናሉ፡፡ የሽልማቱ መርሀ ግብር ከመስከረም 15 ጀምሮ ተወዳዳሪ መፅሐፍት ምዝገባ የተጀመረ ሲሆን መጋቢት 2 ቀን 2009 ዓ.ም የመዝጊያ ፕሮግራም ይካሄዳል፡፡


Read 2051 times