Sunday, 04 September 2016 00:00

‘በሩ’ ወደ ብርሀን አቅጣጫ…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው ማጨስ ለማቆም ቃል ገብቷል፡፡ ታዲያ የአዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ እየተዝናና እያለ ጓደኛውን ሲጋራ ይጠይቀዋል፡፡ ጓደኝየውም…
“አላጨስም ብለህ ቃል ገብተህ አልነበረም!” ይለዋል። እሱዬውም…
“አዎ ቃል ገብቻለሁ፣ ደግሞም እያቆምኩም ነው፡፡ አሁን መጀመሪያ ምዕራፍ ላይ ነኝ፣” ይላል፡፡ ጓደኛውም ግራ ይገባውና…
“የመጀመሪያው ምዕራፍ ማለት ምን ማለት ነው?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
“የመጀመሪያው ምዕራፍ ማለት ሲጋራ መግዛት አቁሜያለሁ ማለት ነው…” ብሎት አረፈ፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ የበዓል ሰሞን ጨዋታም አይደል… ቃል የመግባትን ነገር ካነሳን ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው ይቺን ዓለም ሊሰናበት ጥቂት ጊዜ ነው የቀረው፡፡ እሱን በማስታመም ስትሰቃይ ለኖረችው ሚስቱ…
“በምሞትበት ጊዜ ገንዘቤን በሙሉ ይዤ መሄድ እፈልጋለሁ፣ በትንሽ ሳጥን አድርገሽ ሬሳ ሳጥን ውስጥ ከበድኔ ጋር አብረሽ እንደምትከቺው ቃል ግቢልኝ…” ይላታል፡፡ እሷም ቃል ትገባለች፡፡
ሰውየው እንደተጠበቀው ብዙም ሳይቆይ ይቺን ዓለም ይሰናበታል፡፡ የሽኝት ስነ ስርአት ሲደረግም ሚስቱ አንዲት የተቆለፈ አነስተኛ የብረት ሳጥን ሬሳ ሳጥን ውስጥ ከተተችው፡፡
ነገሩን የምታውቀው ጓደኛዋ ትደነግጣለች፡፡
“ብቻ እሱ እንዳለሽ ገንዘቡን ሁሉ ሳጥኗ ውስጥ ከትቻለሁ እንዳትዪኝ!” ትላታለች፡፡ ሚስትም…
“ቃል ስለገባሁለት ቃሌን አላጥፍም…” ትላለች፡፡ ጓደኛዋ ግን ልታምናት አልቻለችም፡፡
“እውነት ገንዘቡን ሳጥኗ ውስጥ ከተሽለታል!”…ትላታለች፡፡ የሙት ሚስቷ ምን ብላ ብትመልስ ጥሩ ነው…
“ገንዘቡን በሙሉ እስከ መጨረሻዋ ሳንቲም ባንክ በስሜ አስገባሁት፡፡ ከዛም በፈለገ ጊዜ አውጥቶ እንዲጠቀምበት ቼክ ጻፍኩለትና ቼኩን በትንሿ ሳጥን ውስጥ ከተትኩለት…” ብላት አረፈች፡፡
የምር ግን ይሄ ጦስ ጥምቡሳሳችንን ይዞልን እንዲሄድ የረገምነው ዓመት በምንም መለኪያ መልካም ዓመት አልነበረም፡፡ አይደለም መልካም…አለ አይደል…“ምንም አይል…” የሚባል አይነት ዓመትም አልነበረም፡፡ እንኳንም ‘ጫፍ’ ደረሰ፡፡ ‘በሩ’ ወደ ብርሀን አቅጣጫ ይከፈትልንማ!
ልቤ ተሸበረ ከሩቁ ስትጣሪ ሰማሁሽ ሀገሬ
ስንቱን ብሶት ላውራሽ እናቴ ዘርዝሬ
ብሏል ዮሐንስ አድማሱ፡፡ መልካም ነገሮች መስማት እየናፈቀን…“ስንቱን ብሶት ላውራሽ እናቴ ዘርዝሬ…” ስንል የከረምንበት ዓመት ነበር፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን ለከርሞ ህይወት ከአምና እንደምትሻል ተስፋ የሚሆኑ ነገሮች ማየት እንኳን ብርቅ የሆነበት ዓመት ነበር፡፡
ምን የሚባል ነገር አለ መሰላችሁ…ተስፈኛ ሰው ‘አዲስ ዓመትን ለመቀበል’ እስኪነጋ ይቆያል፡ ጨለምተኛ ሰው ግን አሮጌው ዓመት መውጣቱን ለማረጋገጥ እስኪነጋ ይቆያል’ የሚሏት ነገር አለች፡፡ ብዙዎቻችን ‘ጨለምንም፣ በራንም’… እስኪነጋ የምንጠብቀው መውጣቱን ለማረጋገጥ ነው፡፡ ይሉኝታ ባይዘን ኖሮ እንደውም…“ድራሹ ይጥፋ!” እንል ነበር  ቂ…ቂ…ቂ… ‘በሩ’ ወደ ብርሀን አቅጣጫ ይከፈትልንማ!
እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ሰውየው ምን አለ መሰላችሁ…
“በየዓመቱ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ‘ራሴን እለውጣለሁ’ የሚል ቃል እገባለሁ፡፡…ከእንግዲህ ግን ‘ራሴን እሆናለሁ’ ብዬ ነው ቃል የምገባው፡፡”  
ምን ያድርግ…ራስን መለወጥ አልተቻለማ! እዚቹ ክፍለ ዓለማችን ላይ ህይወት “አደርጋለሁ…” “አላደርግም…” በሚሏቸው ቃላት መመራት ከቆየች ከርማለቻ! ማድረግም፣ አለማድረግም የሚወሰነው በእኛ ጥንካሬና፣ ቁርጠኝነት ሳይሆን በሌሎች ‘በጎ ፈቃድ’ እየሆነ ነዋ! እናማ…ቢያንስ፣ ቢያንስ የሆነ ነገር ሳይባባስ ባሉበትም መቆየት መቻል ‘ስኬት’ ነገር ስለሆነ ምንም እያማረብን ባይሆንም….‘ራሴን እሆናለሁ’ ማለት መቻልም ትልቅ ነገር ነው፡፡
አንዲቷ ከተሜ ምን አለች መሰላችሁ… “የአዲስ ዓመት ዕቅዴ ጥሩ፣ ጥሩ ምግብ መብላት ነው፡ ስለዚህ ደህና ሆቴል ከሚወስዱኝ ጋር ብቻ ለመውጣት አቅጃለሁ።” እንዲህም ሁሉንም ነገር አላይም፣ አልሰማም ብለው የሚደላቸው መአት አሉላችሁ፡፡ አንድ ሰሞን ምሳ ለመብላት ባህር ዳር በአውሮፕላን ሄደው ስለሚመለሱ ከተሜዎች ስንሰማ ነበር፡፡ እንደ እነሱ አይነት አሁንም አሉ ወይስ ከሚጢጢ አውሮፕላን ወደ ድሪምላይነር ተሻገሩ!
በልካችን ከተሰፋው ልብስ በላይ ‘የሰፋንና የሰባን’ ከማስመሰል የምንድንበት ዘመን ይሁንልንማ! ‘በሩ’ ወደ ብርሀን አቅጣጫ ይከፈትልንማ!
እንባውን ረጫት ሽቅብ ወደላይ
ድንገት ዝናብ ሆና ትወርድ ይሆን ወይ
አለ ነቢይ መኮንን፡፡ እውነት ለመናገር ከሆነ…በተለያዩ ምክንያቶች ዕንባውን ሽቅብ የሚረጭ እየበዛ ነው፡፡
ህጻኑ ልጅ ወደ ፖሊስ ይሄድና፤ “ፖሊስ እርዳኝ…አባቴ እኩል ሰዓት ሙሉ ከአንድ ሰውዬ ጋር እየተደባደበ ነው…” ይለዋል፡፡ ፖሊሱም…
“ታዲያ እስካሁን ዝም ብለህ አሁን የምትነግረኝ ለምንድነው?” ይለዋል፡፡
“እስካሁን የሚደበድበው አባቴ ነበራ!”
እናማ… ነገሮች እኛ ላይ ካልደረሱ በስተቀር ምንም የማይመስለን ዘመን ላይ ነን፡፡ “ነግ በእኔ” የሚለው ነገር ተረስቶ፣ በሌላው ችግርና መከራ ስንስቅ እንከርምና መጨረሻ ችግሩ እኛ ዘንድ ሲመጣም… “እስካሁን ሲደበደብ የነበረው አባቴ ነበራ!” አይነት ነገር ማለት እንጀምራለን፡፡
“ነግ በእኔ…” ማለትን የምንለምድበት ዘመን ይሁንልንማ! ‘በሩ’ ወደ ብርሀን አቅጣጫ ይከፈትልንማ!
ባልና ሚስት በገንዘብ ጉዳይ ላይ እየተጨቃጨቁ ነበር፡፡ በመጨረሻ ባልየው ይናደድና…
“እኔ ገንዘብ ባይኖረኝ ኖሮ ይሄ ቤት አይኖርም ነበር…” ይላታል፡፡ ሚስትየው ምን ብላ ብትመልስለት ጥሩ ነው…
“የእኔ ውድ፣ ገንዘብ ባይኖርህ ኖሮ እኔም እዚህ ቤት አልሆንም ነበር፡፡”
ዝም ብዬ ሳስበው…አለ አይደል… “ገንዘብ ባይኖርህ ኖሮ እዚህ ቤት አልኖርም ነበር…” የሚሉ ‘የትዳር አጋሮች’ የፍቺ ችሎቶቹን ካጨናነቁት መሀል በብዛት የሚገኙ ይመስለኛል፡፡
ደግሞላችሁ… “ቤተሰቦችሽ ገንዘብ ባይኖራቸው እኔም እዚህ ቤት አልኖርም ነበር…” የሚሉ እንትናዎችም መአት እንደሆኑ ይሰማኛል፡፡ ልክ ነዋ… “አጅሬው ገንዘብ ካላት ተለጥፎ የሚሊዮን ብር መኪና ያሽከረክራል…” ምናምን ሲባል እንሰማለና!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ዘንድሮ ምንም እንኳን ጥናት ምናምን ነገር ባይኖርም…አለ አይደል… ብዙ ግንኙነቶች በገንዘብ ዙሪያ የተመሰረቱ ይመስላሉ፡፡ እናማ…እንደ እኔ አይነቱ ምስኪን…
“ሰዉ ሁሉ የማይጠጋኝ ለምንድነው?”
“ከበብ፣ ከበብ የሚያደርጉ ብዙ ጓደኞች የሌሉኝ ለምንድነው?” ምናምን እያለ እንቅልፍ ያጣል፡፡ መልሱ ‘ግልጥ’ ነው…ቺስታነት ነዋ! ውስኪ ማውረድ አንችልማ!  የእንትንን ቤት ክትፎ ከፈረንሳይ ዋይን ጋር መጋበዝ አንችልማ! ምናምን ሪዞርት ‘ዊክኤንድ’ ይዘን መሄድ አንችልማ! እናማ… የእኔ ቢጤ ወዳጆቼ እንቅልፋችሁን አትጡ፡፡
ገንዘብ ግንኙነትን የማይወስንበትን ዘመን ያምጣልንማ! ‘በሩ’ ወደ ብርሀን አቅጣጫ ይከፈትልንማ!
ሰውየው ገብጋባ ቢጤ ነው አሉ፡፡ ልጁ ያናድደውና ዱላ አንስቶ አናቱን ይለዋል፡፡ ይሄን ጊዜ ዱላው ይሰበራል። ሚስትየው ብው ትልና…
“ምን ነካህ…ያምሀል እንዴ!”   ብላ ትጮህበታለች፡፡ እሱም…
“ሳላስበው ነው ያደረግሁት…” ይላታል፡፡
“ምን ሳታስበው ነው! ሆነ ብለህ ነው እንጂ የመታኸው…” ስትለው ምን አለ መሰላችሁ…
“እሱን የመታሁት ሆነ ብዬ ነው፣ ዱላውን የሰበርኩት ግን ሳላስበው ነው…” እንዲህም አይነት ገብጋባነት አለ፡፡
ለገንዘብም፣ ለንብረትም ይሁን ሌሎች መልካም ነገሮችን ለማድረግና ለማሰብ የምንስገበገብበት ዘመን ይሁንልንማ! ‘በሩ’ ወደ ብርሀን አቅጣጫ ይከፈትልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!




Read 2789 times