Sunday, 04 September 2016 00:00

እስራኤል ዜጎቿ ተቃውሞ ካለባቸው አካባቢዎች እንዲርቁ አስጠነቀቀች

Written by 
Rate this item
(19 votes)

የሆላንዱ ኩባንያ በባህር ዳር ተቃውሞ የ11.1 ሚ. ዶላር የአበባ እርሻ ተቃጠለብኝ አለ

   የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዜጎቹ ተቃውሞ ወደተስፋፋባቸው የአማራና የኦሮምያ ክልል አካባቢዎች እንዳይጓዙና ህዝብ ከተሰበሰበባቸውና ተቃውሞ ከተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች እንዲርቁ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ አስጠነቀቀ፡፡
ተቃውሞ ወደተቀሰቀሰባቸው የአማራና የኦሮምያ ክልል አካባቢዎች መሄድ ለአደጋ ያጋልጣል ያለው ሚኒስቴሩ፤ ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከኤርትራ፣ ከሱዳን፣ ከደቡብ ሱዳንና ከኬንያ ጋር በምትዋሰንባቸው የድንበር አካባቢዎች በ10 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ውስጥ መገኘት እጅግ አደገኛ ነው ሲል ለዜጎቹ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ ባለፈው ሰኞ በባህር ዳር በተቀሰቀሰው ተቃውሞ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተቃዋሚዎች የአበባ እርሻ ኢንቨስትመንቱን በእሳት በማጋየት፤ ሙሉ ለሙሉ እንዳወደሙት “ኢስሜራልዳ ፋርምስ” የተባለው የሆላንድ ኩባንያ በድረገጹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡11.1 ሚሊዮን ዶላር ያወጣሁበት የአበባ እርሻ ኢንቨስትመንት በእሳት ወድሞብኛል ያለው ኩባንያው፣ ሌሎች በአካባቢው የሚገኙና ንብረትነታቸው የእስራኤል፣ ጣሊያን፣ ህንድና ቤልጂየም ኩባንያዎች የሆኑ ዘጠኝ ያህል የአበባ እርሻዎችም በተቃዋሚዎች ጥቃት ደርሶባቸዋል ብሏል፡፡ የኩባንያው ረዳት ስራ አስኪያጅ ሬምኮ ቤርካምፕ ለአልጀዚራ በሰጡት መግለጫ፣ ኩባንያው የተቃጠለውን እርሻ እንደገና አቋቁሞ፣ ኢንቨስትመንቱን ከማስቀጠል ይልቅ ኢትዮጵያን ለቅቆ የመውጣት እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

Read 3949 times