Sunday, 21 August 2016 00:00

ባሕልና የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ

Written by  በሚፍታ ዘለቀ (የሥነ-ጥበብ አጋፋሪ)
Rate this item
(1 Vote)

የዚህ ዓምድ ትኩረት ሥነ-ጥበብ፡ በዋነኝነትም የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ነው። በተለይም ዘመንኛው (Contemporary) የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ላይ አጽንኦት በመስጠት ወቅታዊና በመታየት ላ ይ ያሉ ትርዒቶችን ይዳስሳል፡ ገለጻ ያቀርባል፡ ያትታል፡ ይመረምራል፡ ሂስ ያቀርባል። ግለሰቡን ሳይሆን ስራውን በመተቸት የሂስ ባሕልን ለማዳበር ይጥራል፡፡ የዓምደኛውን እይታ መሬት በያዙና ሚዛን በሚደፉ አመክንዮች በማስደገፍ፣ ግለሰብ አንባቢ ስለ ሥነ-ጥበብና ስለ ኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ግንዛቤ እንዲጨብጥ፡ የዕይታ ባሕሉ (Visual Culture) እንዲዳብር፡ የሥነ-ጥበብ አድናቆቱ ከፍ እንዲል፡ ሥነ-ጥበብን የሕይወት ዘዬው(Life Style) አድርጎ እንዲወስደው መንገድ ለመክፈት ይጥራል።በማኅበረሰብና በሃገር ደረጃም ልክ እንደ ኤኮኖሚያዊ፡ ፖለቲካዊ፡ ማኅበራዊ፡ ባሕላዊና ትውፊታዊ እንዲሁም ታሪካዊ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ሥነ-ጥበብን የሰፊው የሕይወት መር (Mainstream) አካል እንዲሆን ይተጋል።

“የባሕል ፖሊሲያችን ለሁለት አስርት አመታት ገደማ ተጋድሞ ለሽ ያለ እንቅልፉን ነው ያጣጣመው ወይስ በእንቅልፍ ልቡም ቢሆን ማሳካት አሊያም መከሠት የቻለው የባሕል ምርት ይኖር ይሆን?”

ክፍል አንድ
መነሻ፡ በዚህ ተከታታይ ክፍል ያለው ጽሑፍ፤ ወቅታዊውንና ዘመነኛውን የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ እንቅስቃሴ አንስተን ስንወያይ ባሕል፣ የባሕል ምርት፣ ባሕልና ልማት፣ የባሕል አብዮት፣ የባሕል ፖሊሲና የእይታ ባሕልን  መሠረት በማድረግ ጽንሠ-ሃሳባዊ (Conceptual)፣ ቲዎረቲካል (Theoretical) እና ተግባራዊ (Practical) ደጀን በማበጀት፣በተለይ ዘመነኛ የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብን (Contemporary Ethiopian Art) ጠቅለል ካለ ማዕቀፍ (general framework)  መረዳት እንዲያስችለን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ይህ የመጀመሪያ ክፍል ለምንጠቀማቸው ቁልፍ ቃላቶች ትርጓሜ (definition) እንዲሁም ትንታኔ በመስጠት ለመነጋገሪያ ነጥቦች በር በመክፈት ይጀምራል፡፡
ባሕል፡- ‘ባሕል የአንድ ማሕበረሰብ ታሪክ፤ አኗኗር፤ ኤኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊና ፖለቲካዊ ማንነት መገለጫ ነው!’ የሚለው የባሕል ትርጓሜ እጅግ የተለመደና ጭፍልቅ አንድምታ እንዳለው ግልጽ ይመስለኛል፡፡ ግለሰብ፣ ተቋም፣ ማሕበረሠብም ሆነ ሀገር ስለ ባሕል ዓውዳዊ (Contextual) ትርጓሜ ሊሠጥ ይችላል። እ.ኤ.አ በ1982 የዓለም አቀፉ ድርጅት ዩኔስኮ (UNESCO) ጠቅላላ ጉባኤ በሜክሲኮ ሲቲ ተሰብስቦ ስምምነት ላይ የደረሠበት የባሕል ትርጓሜና ድምዳሜ እንዲህ ይላል፡-
“የሰው ልጅን ምክንያታዊ ማንነት ሊገልጹ የሚችሉ ባሕሪያትን በአዕምሮአዊ ብስለት፣ በግብረ ገባዊ፣ በአካላዊ፣ በቴክኒካዊና በሌሎች እንቅስቃሴዎች የሚያቅፍ ጽንሠ-ሃሳብ ባሕል ይባላል”
አንድ ሰው በሞራል፣ በቴክኒክና በሌሎች የዕውቀት ማዕቀፎች ራሱን እንዲያስተምርና እንዲያሰለጥን ባሕል አቅም የሚፈጥር መሆኑንም ያብራራል፡፡ ባሕል የአንድ ማሕበረሠብ የሕይወት ዘዴዎች፣ እምነቶች፣ በትውፊቶች እንዲሁም ቁሳዊና መንፈሳዊ ሃብቶች አማካኝነት ከሌሎች ልዩ የሚያደርጉትን ባሕሪያት የሚያጠቃልል ሠፊ ጽንሠ ሃሣብ እንደሆነም ስምምነቱ ይገልጻል። ይህንን ሠፋ ያለ ትርጓሜና ድምዳሜ ተንተርሶ የተቀረጸው የኢፌዲሪ (FDRE) የባሕል ፖሊሲስ ምን ይመስላል?
የኢፌዲሪ የባሕል ፖሊሲ በሚንስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ስራ ላይ የዋለው እ.ኤ.አ ጥቅምት 1997 ሲሆን በፖሊሲው የመጨረሻ ክፍል ፖሊሲውን ተግባራዊ ለማድረግ ሕጎችና ደንቦች እንደሚደነግጉ ያውጃል፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ ፖሊሲው ሥነ-ጥበብን ተግባራዊ ማድረግን በተመለከተ ሕግና ደንብ አልወጣም፣ ሥራ ላይ አልዋለም፡፡
የባሕል ፖሊሲው “አለ” እንዲባል ብቻ የጸደቀ ሲሆን  ከጸደቀ በኋላም ረዥም እንቅልፉን እንደለጠጠ ነው፡፡ ለመሆኑ በተለይ ሥነ-ጥበብን ችላ ብሎ ሁለት ምዕተ ዓመታት ገደማ ያለ ቀስቃሽ ተኝቶ ያለው የባሕል ፖሊሲያችን ምን ይላል?”
ፖሊሲው፤ ባሕል የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን የተለያዩ ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊ፣ ሞራላዊ፣ ኃይማኖታዊና ሥነ-ልቦናዊ ሁኔታዎችን እንደሚያቅፍና ባሕል የየብሔሮቹን፣ ብሔረሰቦቹንና ሕዝቦቹን ቋንቋዎች፣ ታሪክ፣ አፋዊ ትውፊቶች፣ የቤት አሰራር፣ የምርት መገልገያዎች፣ የምግብ አዘገጃጀቶች፣ የአመጋገብ ልምዶች፣ አለባበሶች፣ ማጌጫዎች፣ የሥነ-ውበት ዋጋዎችና እሴቶች እንዲሁም አድናቆት፣ እምነቶችና የሃይማኖት ተግባራቶችን ሁሉ እንደሚያቅፍ ያትታል። ስህተት ቁጥር አንድ፡- ባሕልን የሚያክል ግዙፍ ጽንሠ ሃሣብን መሠረት ባደረገ በዚህ ብሔራዊ ሰነድ ቋንቋ፣ ታሪክ…ብሎ ከላይ የተዘረዘሩትን የባሕል ማዕቀፎች ነቅሶ ሲደረድር ኪነ-ጥበብ (art)ን ችላ ማለቱ የሚያስገርም ነው። ይህም ፖሊሲው ለኪነ-ጥበብ ያለውን ዝቅተኛ ቦታ ጠቋሚ ነው፡፡ ለኪነ-ጥበብ ትኩረት የሚሰጥ ቢሆን በደፈናው ብቻ ሳይሆን በዝርዝር ሥነ-ጽሑፍ፣ ሥነ ግጥም፣ ሥነ-ጥበብ፣ ቴአትር፣ ሙዚቃ፣ ዳንስ፣ ፊልም … ወዘተ እያለ መጥቀስ ነበረበት ባይ ነኝ፡፡ የሥነ-ውበት ዋጋዎችና አድናቆት በሚል በደምሳሳው ከማስቀመጥ ይልቅ በግልጽ ቢተነትናቸው ኖሮ ምናልባት ቀጥተኛ አትኩሮት ሊሠጠው ይችል ነበር፡፡ ይህንን ክፍተት ባይሞላም የኢፌዲሪ የባሕል ፖሊሲ በመግቢያው ማገባደጃ አካባቢ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቅርስ ታሪክ፣ ሥነ-ጥበብ፣ ዕደ-ጥበባትና ፎክሎር (ተረቶች፣ ምሳሌያዊ አነጋገሮች፣ ሕዝባዊ ግጥሞች፣ ዳንስ፣ ዘፈኖች… ወዘተ) ሁሉ ሊሠበሠቡ፣ ሊመዘገቡ፣ ሊመረመሩና ከማንኛውም አደጋዎች ሊጠበቁ የሚባበት ወሳኝ ጊዜ (ፖሊሲው የጸደቀው በ1990 መጀመሪያ ላይ እንደሆነ ልብ ይሏል) በመሆኑም በማስመር ሁሉም እኩል እውቅናና የመልሣት መብት እንዳላቸው ያስገነዝባል፡፡ ይህም የባሕል ፖሊሲያችን ሥነ-ጥበብንም ሆነ ሌሎች የኪነ-ጥበብ ዘርፎችን ከባሕል ምንነት መገለጫዎች አንጻር ሳይሆን መመዝገብ፣ መመርመርና መጠበቅ ካለባቸው የባሕል እሴቶች አንፃር እንደፈረጀው መመልከት ይቻላል፡፡ ምንም እንኳ የባሕል ፖሊሲያችን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ባሕል መሠረት ያደረገ ዓውዳዊ የባሕል ትርጓሜና ድምዳሜ መስጠቱ ስህተት ባይኖረውም፣ የቀደሙት ሥርዓቶችም ሆኑ በስልጣን ላይ ያለው ሥርዐት ሥነ-ጥበብንም ሆነ ኪነ-ጥበብን ከባሕልነት ያለመቁጠር፣ ያለማካተትና ያለማልማት ቸልተኝነትን በግልጽ ይታይባቸዋል፡፡  
ፖሊሲያችን ሁለት ምዕተ ዓመታት ገደማ እንቅልፉን ሲለጥጥ ሕልም የሚባል ነገር እንዳለመም በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ። ምክንያቱም ሕልም ለማየት ቢያንስ ምስል ያስፈልጋል፡፡ ስለ ሥነ-ጥበብ አንዳች ሃሳብ የሌለው ፖሊሲ እንኳን ተኝቶ ይቅርና ቆሞ በእውኑም ሊታየው የሚችል ራዕይና እይታ ሊኖረው እንደሚችል እጠራጠራለሁ፡፡ የባሕል ፖሊሲያችንን እንከኖች በዚህ ጽሑፍ ተንትኜ መዝለቅ አይቻለኝም። ስለዚህ የፖሊሲው ሙሉ ሰነድ በwww.mysc.gov.et በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተጽፎ ታገኙታላችሁ፡፡ ቋንቋን ከባሕል መገለጫ አንዱ ያደረገ ፖሊሲ፤ ብሔራዊ ቋንቋን ችላ ብሎ በእንግሊዝኛ መቅረቡ ትንሽ ገርሞኛል። ለማን ነው የተጻፈው? ያሰኛል፡፡  
ከሙያዬ አንጻር በሃገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሥነ-ጥበብ በየትኛውም ሁኔታ ‘ገፋ’ እና ‘ኮርኮም’ መደረጓ የሚያበሳጨኝና የሚያሳስበኝ በመሆኑ ችክ ብዬ አሠመርኩበት እንጂ ፖሊሲያችን ለዘረዘራቸውም ይሁን ችላ ላላቸው የባሕል መገለጫዎችና ንጥረ-ነገሮች የነፈገው ትኩረትና የልማት አቅጣጫዎቹ አካል ባለማድረጉ ያጣቸውን ጥቅሞች ከመዳሰሴ በፊት እንዲሁም የባሕል ምርት መካን እንድንሆን ያደረጉትን አሉታዊ አስተዋጽኦዎች ከማተቴ አስቀድሞ የባሕል ተግባራትን Perspective: The Muse of Modernity and the Quest for Development ከተሠኘው የAli A.Mazrui ጽሁፍ በመዋስ እቀጥላለሁ፡፡ (ዋነኛ ትኩረቴ ሥነ-ጥበብ በመሆኑም የባሕልን ተግባራት ስናወራም ሥነ-ጥበብንም እያሰባችሁ እንዲሆን እጠይቃለሁ)
አንድ: ባሕል የመረዳት መነፅር ነው፡፡ ሰዎች ራሳቸውን እንዲያዩም ሆነ ስለ አካባቢያቸው የራሳቸው የሆነ መረዳት እንዲኖራቸው ያስችላል። ለምሳሌ ብዙ የአፍሪካ ማሕበረሠቦች ዘሩ እስከቀጠለ ድረስ የሰው ልጅ እንደማይሞት ነው የሚያስቡት፡፡ ይህም ብዙ እንዲወልዱ በማድረግ አፍሪካ በሕዝብ ብዛት ቁጥር መጨመር አንደኛ እንድትሆንና ይህ ደግሞ ለልማት በአዎንታም ሆነ በአሉታ የራሱ ተጽዕኖ እንዲኖረው አስችሏል። ስለዚህ የመዋለድ ባሕል ስለ ሞትም ሆነ ስለ ልማት የራሱ የሆነ ተጽዕኖ እንዲኖረው ያደርጋል ማለት ነው፡፡  ሁለት: ባሕል የተነሳሽነት መንደርደሪያ ነው። ለምሳሌ በሃገራችን ታላላቆችን ማክበር ባሕል ነው፡፡ ለዚህ ባሕል ተነሳሽነትን የፈጠረው የክብር መስጠት ባሕል ነው፡፡ በዚህ መንገድ ባሕል ባሕሪን ለማነጽ ይውላል ማለት ነው። ሦስት: የስራ ባሕሪ በባሕል ውስጥ ከዳበሩ አስተሳሰቦች ይመዘዛል፡፡ ባሕላችን ስለ ወንዶች የስራ ባሕል ነው ወይስ ስለ ሴቶች የስራ ባሕል ትኩረት የሚሰጠው? አራት፡- ባሕል ውሳኔ ላይ ለመድረስና ፍርድ ለመስጠት መለኪያ ይሆናል፡፡ ጥሩና መጥፎ ብለን ፍርድ የምንሰጠው ሁሉ የመጣንበት የባሕል ቅኝት ውጤት ነው፡፡ ከታነጽንበት ባሕል ጋር የማይጣጣሙ የሌሎች ባሕሎችን ተፅዕኖዎች መቋቋም ሲያቅተንና ሌላውን ባሕል በእኛ መለኪያ ስናስቀምጠውም አይደል የባሕል ግጭት የሚፈጠረው? አምስት፡- ባሕል የግንኙነትና የመግባቢያ መንገዶችን አመላካች ነው፡፡ አንድን ማሕበረሠብ ለማወቅ፣ ለመግባባትና ግንኙነት ለመፍጠር ባሕሉን መገንዘብ ያሻል፡፡ ከማሕበረሠቡ ጋር ተዋህዶ ለመኖር የሚያስፈልገንን ለማግኘትና ለመጠቀም ሁሉ ባሕል ወሳኝ ነው፡፡ ስድስት፡- ባሕል ስለምናመርተውና ጥቅም ላይ ስለምናውለው ምርት ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡ የምንኖረው አኗኗር የሚያስፈልገንን የምርት አይነት እንዲሁም ስለ አመራረታችን ይናገራል። ምርታማነታችን ደግሞ የምናመርተውን ምርትና አጠቃቀማችንን ይወስናል፡፡ ይህም ወደ መጨረሻው የባሕል ተግባር ይመራናል፡፡ ሰባት፡- ባሕል የማንነት መሠረት ነው፡፡ “እኛ” ማን ነን? “እነሱ” ማን ናቸው? የሚሉ ጥያቄዎችን ለመመለስ ባሕል ዋነኛው መሠረት ነው፡፡ በልዩነቶችም ሆነ በአንድነቶች የጋራ ማዕቀፍ ውስጥ የሰው ልጅ ሊጋራ የሚችላቸውን ሰብዓዊነቶች ማጋራት ማስቻል ብቻ ሳይሆን ተጠቃሚ ማድረግ የባሕል ተግባር ሆኖ ይከተላል፡፡
ታዲያ ባሕልን መሠረት በማድረግ የሚመረት የባሕል ምርት ምን ሊመስል ይችላል? ቀድሞውንስ የባሕል ምርት ምንድነው? የባሕል ምርት ሲባል በአስልቺነት ከሚደጋገመው (Cliche) ልማታዊ ቋንቋ የተመዘዘ ቃል እንዳልሆነ ልብ እንድትሉልኝ እጠይቃለሁ። ይልቅስ ከየባሕል ምርት ሃያኛውና ሃያ አንደኛው የሠብዓዊነት (humanity) ፍልስፍና የተወለደው እሳቤ ነው። የባሕል ምርትን ያለማቋረጥ ጥቅም ላይ የማዋል የሰው ልጅ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ነው፡፡ የባሕል መገለጫ የሆኑ ቁሶችንም ሆነ ምናባዊ የባሕል እሴቶችን ለምንፈልገው ተግባር እናውላቸዋለን፡፡ አለባበሳችን፣ አመጋገባችን፣ ለስራ ስንሄድ ከሌሎች ጋር ለመግባባት ስንሞከር፣ ትርፍ ጊዜያችንን ስናሳልፍ… ወዘተ ሁሉ በማወቅም ሆነ ልብ ሳንል ያካበትናቸውን ባሕላዊ እሴቶችንና መገለጫዎችን ጥቅም ላይ እያዋልንና እያመረትን ነው፡፡ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻችን ለኛ የተለመዱና ተፈጥሮአዊ በመሆናቸው ካከበትነው ባሕል እየተመነዘሩ፣ የኛን ባሕል ማሳያ እንደሚሆኑ ቆም ብለን ላናስብ እንችላለን፡፡
ባሕልን ማምረት የሚጀመረው ወይም የባሕል ምርት የሚባለው ደግሞ የባሕላችንን ዓውድና ባሕላችን የቆመበትን፣ የተገነባበትን መሰረቶችና የሚያካትታቸውንም ሆነ የሚያገላቸውን ነጥቦች በነቃ ሕሊና (consiously) ለይተን ማስቀመጥ ስንችልና ከለየናቸው ነጥቦች አንጻር ባሕልን ማምረት ስንጀምር ይሆናል፡፡ ይህም እሴቶችን በማሰብ የጋራ ደንቦችንና በግልጽ ያልተቀመጡትንም ህግጋቶች ለምናመርተው ባሕል መሪ በማድረግና እንቅስቃሴዎችን በባሕላችን አጠቃቀም ላይ መንጸባረቅ ሲችሉ የባሕል ምርት ጅማሬዎች መሆን ይችላሉ፡፡ በቀጣይነትም ይህ የባሕል ምርት ማሕበረሰብንና የማኀበረሠብን መስተጋብራዊ እሴቶች መቅረጽ እንዲሁም ማኀበረሠብ በጐ ወይም መጥፎ እያለ ውሳኔና ፍርድ ላይ እንዲደረስ የሚያስችሉ ሂደቶች ውስጥ የየበኩሉን ድርሻ መወጣት የሚያስችል ሚና ያለው እንቅስቃሴ ማድረግ፣ የባሕል ምርት ፍሬዎችን ማየት እንጀምራለን፡፡ እንዲህ አይነት ውጤት ላይ ለመድረስ የሚያስችሉ ስራዎች ደግሞ በኪነ-ጥበብ አማካኝነት መሰራት ሲችሉ የባሕል ምርት እውን ይሆናል፡፡ የሚሳሉ ሥዕሎች፣ መጽሐፍት፣ ሙዚቃዎች… ወዘተ በምርት ደረጃ እውን ሲሆኑ የባሕል ምርት በመሆን ማሕበረሠብን መቅረጽና ማነጽ ብቻም ሳይሆን ማኀበረሠቡ በቀረጻቸውና ባነጻቸው የባሕል መገለጫዎችና እሴቶች ላይ ሂሳዊ ስራዎችን በማቅረብ የባሕላችንን አቅጣጫዎች የማቃናትም ሆነ የማጣመምና የመቀየስ ሚና መጫወት የሚችል ይሆናል፡፡
በሌላ መልኩም የባሕል ምርት አንድ ማኀበረሠብ ለትርጓሜዎቹና ለማንነት መገለጫዎቹ የሚሆኑ እሴቶችን ለማምረት በሚያደርገው ሂደት ውስጥ የሚፈጠር ጣልቃ ገብነት ሊሆን ይችላል፡፡ ሂደቱ ሁሌም ቢሆን ቀጣይ በመሆኑ ባሕልን የሚቀርጸውና ደግሞ የሚወልደው ይህ የባሕል ምርት ባሕሉን ሊገልጹና  ሊያሻሽሉ የሚችሉ መገለጫዎችንና ትርጓሜዎችን ይዞ ብቅ ሊል ይችላል፡፡ በባሕል ምርት ፍጆታና ምርት ተገቢ የሚሆኑ ጥያቄዎችን በማስነሳትም የባሕል ምርት እንዲፋፋም ያግዛል፡፡ ከጥያቄዎቹ መሃልም፤ የትና መች ነው የባሕል ቁስ (የኪነ-ጥበብ ውጤቶች ማለትም፡- ሥነ-ጥበብ፣ ሙዚቃ፣ ቴአትር …ወዘተ) የሚመረተው? የትኞቹ ሕጋዊ፡ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ኃይሎች ናቸው የባሕል ምርትን የሚያበረቱትና የሚያግዱት? የወቅቱ የማኀበረሠብ ባሕላዊ መገለጫዎችንና የባሕል ኃይል ሚዛንን በምን መልኩ ነው የባሕል ምርቱ የሚገልጸው? ለምንድነው ባሕል የሚመረተው: ማን ነው አምራቹስ? ለማን ፍጆታ ነወ የባሕል ምርቱ የሚውለው? ተጠቃሚው ማን ነው? እነዚህንና ሌሎች የባሕል ምርት ጥያቄዎችን ለመመለስ በሚደረግ ጥረት ውስጥ የኢፌዲሪ የባሕል ፖሊሲ ለሁለት አስርት አመታት ገደማ ተጋድሞ ለሽ ያለ እንቅልፉን ነው ያጣጣመው ወይስ በእንቅልፍ ልቡም ቢሆን ማሳካት አሊያም መከሠት የቻለው የባሕል ምርት ይኖር ይሆን? ካለስ በምን ያህል ደረጃ? ለመሆኑ የመንግስታችን የልማት ፖሊሲና እስትራቴጂ ከባሕል ጋር ምንና ምን ናቸው? የጆሮ ጉትቻና ያንገት ሃብል ናቸው ወይስ…? ሳምንት ይቀጥላል፡፡
ቸር እንሰንብት!

Read 2386 times