Monday, 15 August 2016 09:11

‹አይነኬው› ሲነካ

Written by  ዮናስ ብርሃኔ
Rate this item
(8 votes)

    ሃገራችን ከትውልድ ትውልድ እየተንከባለሉ በመጡ አሁን ድረስ ያልተፈቱ በርካታ ፖለቲካዊ ችግሮች እና ያንን ለመፍታት በተከተልነው አቆርቋዥ አካሄድ ሳቢያ ክፉኛ ጎብጣለች፡፡ ያ ብቻም ሳይሆን ሌሎች መፈታት የሚገባቸው ዘርፈ ብዙ ማህበራዊ ችግሮችንም በጉያዋ እንደታቀፈች በመቃተት ላይ ያለች ሀገር ለመሆንዋ አስረጅ አያስፈልgweግም፡፡ ለማናቸውም አይነት ችግሮች እና ጥያቄዎች ፖለቲካዊ ምላሽ መስጠት ለሚቀናው መንግስታችንም ነገሩ ልክ የሚፋጅ ቆሎ ይዞ ከአንደኛው መዳፍ ወደ ሌላኛው እያገላበጠ ለማባረድ እንደሚሞክር (መጣል አልሆንለት ያለው) ምስኪን የገበሬ ልጅ አይነት የሆነበት ይመስላል፡፡ ወዲህ በህብረተሰባችን ውስጥ ያለውን ሁኔታ የተመለከትን እንደሆነ ደግሞ በቁጥር እጅግ የሚልቀው ሰው ግራ በተጋባ መንፈስ ተወርሮ እናገኘዋለን፡፡ ይህን መምታታት እና ግራ መጋባት የፈጠረው ዋነኛው ነገር ደግሞ በበባህል እና በዘመናዊነት ወይም በስልጣኔ መካከል ያለው ፍጥጫ ነው፡፡ ይህም ከንቃተ ህሊናው አለመብሰል ጋር ተደምሮ ሰው ለራሱ የሚበጀውን አዲስና የተሻለ ማዕከላዊ ንጥር መፍጠር እንዳይችል አድርጎታል፡፡ በሌላ አባባል Golden mean የሚባለውን ነገር ጨምቆ ማውጣት አልተቻለም፡፡
የሰውን ሁኔታ በደንብ ካስተዋልነው አብዛኛው ሰው በህይወቱ ውስጥ ደስተኛ መሆን የሚችልበትን የሚፈልገውን ትክክለኛ ነገር እንኳ በቅጡ የሚያውቀው አይመስልም፡፡ በቃ ሰው ሁሉ የሚይዝ የሚጨብጠው ነገር ጠፍቶበት እንዲሁ ደስታ በራቀው ህይወት ወስጥ እየዋለለ ይገኛል፡፡ ነገሩ ሁሉ በዚሁ ከቀጠለም መጨረሻው ከቀውስ የሚያመልጥ አይሆንም፡፡ የሚያሳዝነው ደግሞ ማህበረሰብን እንደ አዲስ የሚቀርጽና የሚገነባ ዘመን ተሻጋሪ ኅልዬት መቀየስ የሚችል ሩቅ አሳቢ አይውጣላችሁ ተብለን የተረገምን ይመስል የተማረውም ክፍል ቢሆን የሚችለውን/ የሚገባውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ከመጣር ይልቅ እርስ በርስ በመሻኮቱ ላይ መጠመዱ ነው፡፡ እናም ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ ስናጤነው ሁሉም ነገር በራሱ ጊዜ እንደሆነው ይሁን ተብሎ የተጣለ ይመስላል፡፡
ለእነዚህ ሁሉ ችግሮች መፋጠር መሰረታዊ ምክንያት ወደሆነው ባህል ስንመጣ በዚሁ ዙሪያ ያለው የህብረተሰቡ ግንዛቤ በአየር ላይ የተንጠለጠለና (የጠቀስነውን መምታታት የፈጠረ በራሱ) የተምታታ ነው፡፡ ይህም መጥራት የሚገባው ትልቅ ብዥታ ሆኖ ሳለ እየሆነ ያለውን ነገር ስንመለከት ግን አንድ የምንገነዘበው ነገር እውነታን ተጋፍጦ መቀበል የሚችል አዕምሯዊ ብቃት ካለመዳበሩ ጋር ተያይዞ ሁሉም በየፊናው የተያያዘው አካሄድ ነገሩን በግልጽ (እያፍረጠረጡ) ከመተቸት ይልቅ ፈራ-ተባ እያሉ ማሽሞንሞን እንደሆነ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የትም የማያደርስ አካሄድ ስለመሆኑ የእስከዛሬው ጉዟችን በግልጽ የሚያስረዳው ምንም የማያወላዳ ጥሬ ሐቅ ነው፡፡
ይሁንና ከዚህ ከተለመደው አካሄድ መውጣት ባለመቻላችን የህዝቡ ኑሮ ብሎም ሀገሪቷም እንደሀገር የምታደርገው መፍጨርጨር ሁሉ “ባለህበት ሂድ” ሆኖ እያየነው ነው፡፡ እና ምን ይፈጠር ነው እምትለው ካላችሁኝ ባጭሩ ሲወርድ ሲዋረድ ለመጣ ባህልና ልማድ በጭፍን መገዛቱ ይቁም ነው፡፡ ለዘመናት አይነኬ ሆኖ በዘለቀው ባህል ወይም ባህላዊ አስተሳሰብ ላይ አምጾ የሚነሳ አሻፈረኝ ባይነት (በውስጣችን) መፈጠር አለበት ነው ነገሩ፡፡ በቃ! ያረጀና አገልግሎቱን የጨረሰ ባህል አውጥቶ የሚጥል አዲስ ትውልድ፣ አዲስ አስተሳሰብ፣ አዲስ አብዮት ያሻናል፡፡ አለበለዚያ እንዲሁ ባለንበት ተቀብሮ መቅረት ነው፡፡
ምናበ ሰፊው የስነ-አእምሮ ሊቅ ሲግመንድ ፍሩድ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም አነጋጋሪ የሆነ እሳቤውን ያቀረበበት አንድ ግሩም መጽሐፍ  አለው፡፡ ባጭሩ ፍሩድ በዚህ ስራው ላይ ለመመለስ የሞከረው ቁልፍ ጥያቄ የሰው ልጅ አሁን ከደረሰበት የስልጣኔ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ያስቻለው አስተሳሰብ በትክክል መጠንሰስ የጀመረው የቱ ጋ ነው የሚለውን ነጥብ ነው፡፡ ለዚህም የሰው ልጅ ከእንስሳዊነት ደረጃ ወጥቶ መኖር ከጀመረበት ጥንታዊ ማህበረሰብ አኗኗር አንስቶ ዛሬም ድረስ በአፍሪካ፣ በአውትራሊያ እና በሌሎች ቦታዎች ባሉ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ በሆነ የእድገት ደረጃ ላይ በሚገኙ የሰብዓ ትካት አኗኗር ዘይቤ፣ አስተሳሰብ እና ስርአተ አምልኮ ዙሪያ የተደረጉ ጥልቅ ስራዎችን እያጣቀሰ ነገሩን እራሱ ከሚታወቅበት የሳይኮአናሊሲስ እይታ አንጻር በመመርመር ሰፊ ሃተታ ያቀርባል፡፡ እና ነገሩን ስናሳጥረው በዚህ ውስጥ የሚያስረግጥልን አንዱ ትልቁ ነጥብ በመሰረታዊነት የሰው ልጅ አሁን ከደረሰበት የአስተሳሰብ/ የእድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ የተጓዘው እረጅም የለውጥ ጉዞ (እርምጃ) አሃዱ ብሎ የጀመረው የጥፋተኝነት ስሜት እና ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው ልማዳዊ አስተሳሰብና ድርጊት ላይ አምጾ እንደሚነሳ ያደረገው ባይነት በሰዎች አዕምሮ ውስጥ መፈጠርን ተከትሎ እንደሆነ ነው፡፡
እንግዲህ ነገሩን ጠምልለን ወደራሳችን የተነሳንበት ርዕሰ ጉዳይ ስናመጣው ሲወርድ ሲዋረድ እንደመጣ በተረከብነው ባህላዊ አስተሳሰብ ላይ ማመጽ እናም ያንን የማጥራት ዘመቻ ምን ያህል መሰረታዊ እና አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነገር መሆኑን ማየት ይቻላል፡፡ ባህል በሀገራችን ለዘመናት አይነኬ ሆኖ የቆየ ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም ተሃድሶ የሚባል ነገር ሰብሮት ሊገባ አልቻለም፡፡ ስለዚህ አሁን ደግሞ እስኪ ይነካና ይታይ፡፡ እርግጥ ነገርየው መንጋውን ብቻ ሳይሆን ‹ባህላችን ይጠበቅ› እያሉ በባዶ ሜዳ የሚውተረተሩትን ወገኖች እንደሚያስቆጣ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን ‹የባህል ወረራው› ተከላካይ አርበኞች ነን የሚሉት እነዚህ እራሱን የቻለ ጽንፍ የያዙ ሰዎች እዚህ ላይ አንድ መገንዘብ ያለባቸው ነገር ይኼ የሚሉትና የሚያጫጩሃቸው ነገር በራሱ አንድም ከፍርሃት የመነጨ መሆኑን ነው፡፡ ማለትም ነገሩን ገልብጠን ስናየው ይህ ሊያፈራርሰን የመጣ ‹ወራሪ› ነው የተባለው (የምዕራባውያኑ)ባህል የእኛን ነባር ባህል ማሸነፍ የሚችል አቅምና ኃይል እንዳለው እናም የተሻለ እንደመሆኑ በውስጠ ታዋቂነት ማሸነፉ እንደማይቀር ከማመን እና ያንን ከመፍራት የሚመነጭ ነው፡፡ መጀመሪያውኑም ቢሆን ሊያሸንፈን የማይችልን ነገር ልንፈራው ስለማንችል ማለት ነው፡፡ እናም እንደዚያ የሚሆኑበትን ምክንያት በ “ሳይኮአናሊቲክ” መንገድ ውስጣቸው ቢፈተሸ እውነታው ከላይ እንዳልኳችሁ የተገላቢጦሽ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የተደበቀ ፍራቻ እና (እራሱ ባህሉ የፈጠረባቸው) ፋርሃ ለውጥ ነው የሚያውተረትራቸው፡፡
ነገርየውን ከሌላ አቅጣጫ ያየነው እንደሆነም አንድ ባህል ራሱን መመከትና መከላከል ካልቻለ በሰዎች ውስጥ ያለን የተቀበረ ፍላጎት ማስተናገድ እና ማርካት ካለመቻልም እንጻር ቢሆን መጀመሪያውኑ የጎደለው ነገር አለ ማለት ነው፡፡ ይሁንና ‹ወራሪ› የተባለው የምዕራባውያኑ ባህል (ከነትሩፋቶቹ ማለት ነው) የሰዎችን ውስጣዊ ፍላጎቶች ያማከለ ስለሆነ እናም በዚሁ የተነሳ ያንን ያዩና የቀመሱ ሰዎችን ቀልብ የመግዛት ኃይል እንዳለው ስለሚታወቅ ያን በመፍራት አስቀድሞ ለመከላከል ሲባል በሚደረገው ግብግብ ይኸው እንደምናየው ችግር እየፈጠረ ይገኛል፡፡ (በአረብ አገራትም ያለውን ሁኔታ ልብ ይሏል)


Read 5115 times