Monday, 25 July 2016 09:05

‹‹ነጋሪት ሲጎሰም የማትሰማ ከተማ››

Written by  ተፊሪ መኮንን
Rate this item
(5 votes)

    ዓሣ በባህር ውስጥ እንዲኖር፤ ሰው በባህል ውስጥ ይኖራል፡፡ ሰው በባህሉ፤ ዓሣም በባህሩ ይዋኛል፡፡ ዓሣ ከባህር ወጥቶ ለመኖር እንደሚቸገርል፤ ሰውም ከሚዋኝበት ባህል ወጥቶ፤ የባህልን ምንነት በግልጽ ለማየት፤ እንዴት እንደሚሰራም ለመረዳት ይቸገራል። ታዲያ ሰው የሚኖርበትን ወይም በዙሪያው ያለውን ዓለም በወጉ ለመረዳት እና አወንታዊ የባህል ለውጥ ለማምጣት ወይም ለባህል ዕድገት ገንቢ አስተዋጽዖ ለማድረግ ከፈለገ፤ ስለ ባህል ግልጽ ግንዛቤ ሊኖረው ይገባል፡፡
ግልጽ እይታ ለመፍጠር መነሻ መደረግ ያለበት የባህል ትርጉም ነው፡፡ በዚህ መጣጥፍ ‹‹ባህል›› የሚለው ቃል የያዘው ፍቺ፤ የሥነ ሰብእ (Anthropology) ምሁራን የሚሰጡትን ፍቺ ነው። በሥነ ሰብእ ምሁራን እይታ ባህል ሁለት ዘርፎች አሉት፡፡ ‹‹ቁሳዊ›› እና ‹‹ቁሳዊ ያልሆነ›› በሚል የሚጠቀሱ ዘርፎች ናቸው፡፡ ቁሳዊ በሆነው የባህል ዘርፍ፤ የሰው መገልገያ የሆኑ የተለያዩ መሣሪያዎች፣ ህንጻዎች፣ ልዩ ልዩ ቴክኖሎጂዎች እና የዕደ ጥበብ ውጤቶች ወዘተ ይካተታሉ፡፡ በሌላ በኩል፤ ቁሳዊ ባልሆነው የባህል ዘርፍ፤ በመማር የተገኙ ባህርያት (learned behaviors)፣ እምነቶች፣ ሥነ ምግባራዊ እሴቶች (norms) እና ክህሎቶች ወዘተ ይካተታሉ፡፡    
ሰዎች ባህል የሚያስፈልጋቸው ፍጡራን ናቸው፡፡ ሰው ሆኖ ባህል የማይኖረው የለም፡፡ ባህል ልናመልጠው የማንችለው ነገር ነው፡፡ ባህል የሰው ‹‹የተፈጥሮ›› ሐብት ነው፡፡ ሰው መሆንን የሚያስገኝ አንድ አላባ ነው፤ - እንግሊዝኛው ይሻላል- Part of what it means to be human፡፡ ሰውን ሰው ያደረገው ባህል ማለት ይቻላል፡፡ ባህል የሰውን መሆን ወሳኝ አላባ ነው (Culture is an essential component of being human)፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅን በደንብ ለመረዳት ባህሉን መረዳት ያስፈልጋል፡፡  
ለምሣሌ የእንስሳት ወገን የሆነ ማንኛውንም ፍጥረት በደንብ ለመረዳት ከፈለግን፤ በወገን የሚመደቡትን እንስሳት አካላዊ መዋቅር (physical anatomy)፤ የእንስሳቱን ባህርያት፤ አንዱ የእንስሳ ወገን ከሌላው የእንስሳ ወገን ጋር ያለውን ዝምድና፤ ምቹጌአቸውን (habitat) በደንብ መረዳት ይኖርብናል፡፡ ይህን ሳናደርግ በቅጡ ልናውቃቸው አንችልም፡፡
በአንጻሩ የሰው ልጆችን በአግባቡ ለመረዳት የምንችለው፤ በተፈጥሮ ውርስ ያገኙትን አካላዊ መዋቅር (physical anatomy) እና ስርዓተ አካላትን፤  የተለያዩ ቡድኖችን ቁሳዊ ያልሆኑ የባህል ጓዞችን፤  እንዲሁም ቁሳዊ የባህል ሐብቱን እና ከሚኖርበት ዓለም ጋር ያለውን ትስስር መረዳት ስንችል ነው፡፡
በርካታ እንስሳት ስኬታማ ህይወት ለመምራት የሚያስፈልጋቸውን ሁሉንም ክህሎት ያለ ትምህርት ያገኙታል፡፡ ከወላጆቻቸው ወይም ከሌላ ወገን መማር ሳያስፈልጋቸው፤ የህይወት ግብራቸውን በደመ ነፍስ ማከናወን ይችላሉ፡፡ ብዙውን ጊዜ ጠንካራ የማህበራዊ ህይወት ዝንባሌ ካላቸው እንስሳት የሚወለዱ ግልገሎች (ጨቅላዎች)፤ ከወላጆቻቸው የሚማሩት የሆነ ነገር ይኖራቸዋል፡፡ ሌሎች በርካታ እንስሳት ግን ከተወለዱ በኋላ ወላጆቻቸውን አይፈልጓቸውም፡፡ ምናልባት የሚፈልጓቸው መስለው ቢታዩ እንኳን፤ የሚፈልጓቸው የህይወት ግብራቸውን ለማከናወን አይደለም፡፡ እንስሳቱ ከተወለዱበት ወይም ከተፈለፈሉበት ቅጽበት አንስቶ በህይወት ለመኖር የሚያስፈልጋቸው ማናቸውም ነገር አላቸው፡፡ ስለዚህ ወላጆቻቸውን የሚፈልጓቸው የኑሮ ክህሎትን እንደ ያዙ ነው፡፡
 የሰው ነገር የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ የሰው ልጆች ከተወለዱበት ዕለት ጀምሮ ለበርካታ ዓመታት የወላጆቻቸው ጥገኛ ሆነው ይኖራሉ፡፡ እኛ ሰዎች፤ በህይወት ለመኖር የሚያስፈልገንን ነገር (ከሞላ ጎደል ሁሉንም ነገር) መማር ያስፈልገናል፡፡ ከምንማራቸው ነገሮች (እንደ ቋንቋ ያሉ) የሚበዙት ምንጫቸው ባህል ነው፡፡ በተጨባጭ ማየት እንደሚቻለው፤ የሰው ልጅ እንደ አንድ የእንስሳት ወገን፤ አሁን የሆነውን ሆኖ መገኘት የቻለው፤ የሆነ ባህል ይዞ በመገኘትና የሆነ ባህል አባል መሆን በመቻሉ ነው። ታዲያ ባህል በህይወታችን ውስጥ የሚጫወተው ሚና አወንታዊ ብቻ ሳይሆን አሉታዊም ገጽታ አለው፡፡ ባህል በረከት ብቻ ሳይሆን መርገመትም ሊሆን ይችላል፡፡
የባህል ሸክም
አንዳንድ ጊዜ በደመ ነፍሳቸው እርግጠኝነት ታምነው የሚኖሩ የሌሎች እንስሳት ሁኔታን በደንብ ከተመለከትን ተገርመን አናባራም፡፡ እነዚህ እንስሳት በሚሊየኖች ዓመታት ሂደት ተሞርዶ በተሳለ ደመ ነፍስ የሚፈጽሙትን ነገር ሰው በጥበብ የሚሰራው አይመስልም፡፡ በደመ ነፍስ ምሪት ብቻ ተገቢውን ነገር በማድረግ ለመኖር መቻል ህይወትን በጣም ቀላል ያደርገዋል፡፡ አንዳንዴ እንዲህ ባለው ህይወት ቅናት ሊያድርብን ይችላል፡፡ ህይወታቸው የሚያስቀና ሆኖ ሊታየን ይችላል፡፡
የእኛ ህይወት እንዲህ ያለ አይደለም፡፡ ‹‹ሪፍሌክስ›› የሚባለውን ነገር ትተን፤ የሰው ልጆች በንጹህ ደመ ነፍሳዊ ምሪት ሊያከናውኗቸው የሚችሉዋቸው ነገሮች በጣም ጥቂቶች ናቸው። ጥቂት ካልናቸው የሰው ልጅ ንጹህ ደመ ነፍሳዊ አድራጎቶች፤ አብዛኛዎቹ ለጨቅላ ህጻናት ኑሮ ብቻ የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ እንደ ማልቀስና ጡት መጥባት ያሉ ደመ ነፍሳዊ ችሎታዎች፤ ለጨቅላ ህጻናት የሚያገለግሉ ከመሆናቸውም በላይ፤ ህጻኑ እያደገ ሲመጣ ባህላዊ ኩታ የሚደርቡ ናቸው፡፡ ነገሩን ከማናቸውም አንጻር ብትመለከቱት፤ የሰው ልጆች በባህል ላይ ያላቸው ጥገኝነት እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡
ታዲያ ይህ የባህል ጥገኝነት ኢቮልዩሽናዊ ረብ አለው፡፡ የሰው ልጅ የባህል ድጋፍ ሳይኖረው፤ ሚሊየን ዓመታት በሚፈጅ የኢቮልዩሽን ጎዳና ተጉዞ ከአሁን ዘመን ሊደርስ አይችልም ነበር፡፡ ራሳችንን ከአካባቢያዊ ሁኔታዎች ጋር በማስማማት (adaptability) እና እንደ ነገሩ ሁኔታ የኑሮ ዘዬን በመቀየር ለመዝለቅ (flexibility) የሚያስችል ምቹ ሁኔታ የተፈጠረልን ባህል ነው፡፡ ሆኖም አንዳንዴ ከባህል የምናገኘው ከአካባቢ ጋር ራስን የማስማማት (adaptability) ችሎታና የኑሮ ዘዬን በመለወጥ ከሁኔታዎች ጋር የማጣጣም (flexibility) ብቃት ሊሰጠን የሚችለው ባህል በተሳሳተ ጎዳና ይዞን ሊነጉድ ይችላል፡፡ በርካታ ባህሎች/ ህብረተሰቦች/ ሥልጣኔዎች፤ ባለቤቶቻቸውን ዝንጋኤና ድንዛዜ ውስጥ እየጣሉ እንዳነሳሳቸው ወድቀዋል፡፡ አስረጅ የሚፈልግ ሰው ከሮማ ተነስቶ በሰላማዊ ውቂያኖስ ወደ ምትገኘው ኤስተር ደሴት (Easter Island) መሄድ ይችላል፡፡ በማዕከላዊ አሜሪካ የሚገኙትን የማያ ከተሞች (Maya cities) እና የቫይኪንጎች (Viking) ግዛት የሆነውን ግሪንላንድን (Greenland) በመጎብኘት ብዙ የታሪክ ምስክር ለማግኘት ይችላል፡፡ የኢትየጵያን አክሱምና የታላቋን ዝምባቡዌ የታሪክ ቅርስ መጎብኘት ይችላል፡፡ የፍርስራሽ ክምርና የእንቆቅልሽ መደብር ሆነው የቆሙ፤ የዓለም ህዝቦችን ቀልብ የገዙ የሥልጣኔ አሻራዎች በተጠቀሱት አካባቢዎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ የጠፉ ሥልጣኔዎች ናቸው፡፡ ለእነዚህ ሥልጣኔዎች መውደቅ የወዲያው (ግብታዊ)  ምክንያት ሆነው የሚጠቀሱ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ሆኖም፤ ራሱ የህብረተሰቡ ባህል የራሱን ውድቀት በማጋፈር ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት መዘንጋት የለብንም፡፡ ይህ ክስተት በታሪክ ውስጥ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡
ያሬድ ዲያመንድ (Jared Diamond)፤ ‹‹Collapse: How Societies Choose to Fail or Succeed›› በተሰኘ መጽሐፉ፤ የህብረተሰብ የውድቀት ወይም የስኬት ምርጫ ምን እንደሆነ ያስረዳናል፡፡ በእርሱ እምነት ወደ ውድቀት የሚያመራ ጅል ማህበራዊ ውሳኔ የሚመነጨው፤ ቀጥሎ ከተዘረዘሩት ነገሮች በአንዱ ወይም ከአንድ በላይ በሆኑ ምክንያቶች መሆኑን ያስረዳል፡፡
ችግሩ በተጨባጭ ከመፈጠሩ በፊት አስቀድሞ ለማየት ካለመቻል፤ ችግሩም ከመጣ በኋላ የችግሩን ምንጭ ለይቶ እርምጃ ለመውስድ ካለመቻል፤ ችግሩ ተለይቶ ቢታወቅም መፍትሔ ለመሻት ለመንቀሳቀስ ካለመቻል፤ ውድቀት ሊመጣ እንደሚችል ያትታል፡፡
እነዚህን ውድቀቶች ከጀርባ ሆነው የሚገፉ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ በአብዛኛው፤ (1) ልዩ ጥቅም በሚያሳድዱ ወገኖች ስግብግብነት (special- interest selfishness)፤ (2) የለውጥን አስፈላጊነት የሚያውጁ ድምጾች በዙሪያው ሲንጫጩ እየሰማ፤ ‹‹የያዝከውን መስመር እንዳትለቅ›› ብሎ ድርቅ በሚል ግትር የእምነት ስርዓት (rigid belief system)፤ (3) እንዲሁም የሰው ልጆች እንግዳ ከሆነ ክስተት ጋር ሲጋፈጡ ዘወትር እንደ ጋሻ በሚያነሱት እውነታን የመካድ ዝንባሌ (denial with which humans confront unfamiliar conditions) እየተነዱ የሚመጡ ውድቀቶች ናቸው፡፡ ለምሳሌ፤ ‹‹የአክሱም ስልጣኔ የወደቀው በዮዲት ጉዲት ነው፡፡ በእስልምና መስፋፋት ነው›› ወዘተ የሚሉ ግብታዊ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ ሆኖም፤ አክሱማውያን ችግሩ ከመምጣቱ በፊት ለማየት፣ ከመጣ በኋላም ምንጩን ለመለየት፣ ለይተውትም ከሆነ መፍትሔ ለመሻት አለመቻላቸው፣ ውድቀታቸውን አምጥቶታል ማለት ይቻላል፡፡
ባህላዊ ውድቀቶች፤ ምንም ቢደረግ ሊቀሩ የማይችሉ ውድቀቶች አይደሉም፡፡ ሆኖም ከፍ ሲል የተጠቀሱት ቅድመ ሁኔታዎች ሲሟሉ ውድቅት ሊመጣ ይችላል፡፡ ስለሆነም፤ ‹‹ባህልን እንደ ሸክም›› የሚለው ጽንሰ ሐሳብ የያዘው መሠረታዊ መልዕክት፤ ባህል በጥንቃቄ መታየት የሚገባው ነገር መሆኑን ያስረዳል፡፡ ባህል እንዳሻው ሊጋልብ የማይገባው የጋሪ ፈረስ ነው፡፡ ልጓሙን ከእጃችን አውጥተን እንደ ፈቀደው እንዲጋልብ መብት ከሰጠነው፤ ይዞን ገደል ሊገባ ይችላል የሚል መልዕክት ያለው ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡
ይህ ነገር በደንብ የታወቀ እውነት ነው፡፡ አሁን በዓለማችን ያለው ስልጣኔ (ባህል) ከቀደምት ስልጣኔዎች ውድቀት ብዙ መማር ይችላል፡፡ በኒውክሌር መሣሪያ የሚታመን ጉልበተኝነት፣ አሸባሪነት፣ የሐይማኖት አክራሪነት፣ የአየር ብክለት፣ ዘላቂ ያልሆነ የተፈጥሮ ሐብት አጠቃቀም፣ ያልተመጣጠነ የሐብት ስርጭት ወዘተ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ለማስወገድ ከልብ የሆነ ጥረት እያደረገ አይደለም፡፡ ይህ ስልጣኔ ዘላቂ ለመሆን አይችልም፡፡ ‹‹የሚጠፋ ከተማ፤ ነጋሪት ሲጎሰም አይሰማም›› የሚያስብል ሁኔታ ውስጥ ነው፡፡ ዓለም በአስቀያሚ የዘረኝነት መንፈስና በአሸባሪዎች አረመኔያዊ ድርጊት ተበክላለች፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማህበራዊ ጉዳዮች ዓለም አቀፍ ገጽታ እየያዙ በመምጣቸው የተነሳ፤ ስህተቱ የሚያስከፍለው ዋጋም በዛው ልክ ከፍተኛ ሆኗል።
ድሮ ድሮ ከመንደር ያለፈ አደጋ የማያስከትሉ የነበሩት ባህላዊ ውድቀቶች፤ ዛሬ ጠቅላላ የሰውን ልጅ ወይም ጠቅላላ ሥነ ፍጥረትን ወደ መቃብር ሊያወርድ የሚችል (ኬሚካል እና ባዮሎጂካዊ የጦር መሳሪያን አስቡ) አደጋ ሆኖ ይታያል፡፡
አንድ ማለፊያ ብሂል አለ፡፡ ‹‹ባህል ከሰው ልጆች የሚጠይቀው ዋጋ፤ ዝንታለም በርን ለለውጥ ከፍቶ አድርጎ መኖርን ነው›› ይባላል፡፡ ብሂሉ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተመቸ ለዛ አለው፤ The price of culture is eternal openness to change ይላል፡፡
የሰው ልጅ በአሁኑ ሰዓት ከባድ ፈተናዎች ተጋፍጠውታል፡፡ ሆኖም ፈተናዎቹን ተጋፍጦ ለማለፍና እንቆቅልሾቹን ለመፍታት፤ ስኬታማ የሆኑ ባህሎች ከዚህ ቀደም ያደረጉትን ነገር ለማድርግ መነሳት ይኖርበታል፡፡ መጭው ጊዜ ወቅታዊ ፈተናዎችን ለማለፍ የሚያስችሉ የፈጠራ ብቃትና ራስን ከሁኔታዎች ጋር አስማምቶ የመገኘት ብቃትን ይጠይቀናል፡፡ ሆኖም አሁን የሚታየው ነገር የወደቁ ባህሎች ባህርያት ነው፡፡ ዓለም፤ ነጋሪት ሲጎሰም የማትሰማ ከተማ ሆናለች፡፡


Read 2969 times