Saturday, 02 July 2016 12:06

20 ሺ ቤቶች በሚፈርሱበት ክ/ከተማ የሰዎች ህይወት አልፏል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(65 votes)

በግጭቱ ተሳትፈዋል የተባሉ ከ200 በላይ ሰዎች ታስረዋል
ነዋሪዎች መውደቂያ አጥተናል ሲሉ እያማረሩ ነው

በላፍቶ ክ/ከተማ ቀርሳ ከንቱማና ማንጎ ሰፈር በተባሉ አካባቢዎች ህገ ወጥ ናቸው የተባሉ ቤቶች ከትላንት በስቲያ ጀምሮ በአፍራሽ ግብረ ኃይል እየፈረሱ ሲሆን በአጠቃላይ 20 ሺ ገደማ ቤቶች ሊፈርሱ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡
ባለፈው ረቡዕ በደንብ ማስከበርና በክ/ከተማው ነዋሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የአንድ የወረዳ ሥራ አስፈፃሚና የሁለት ፖሊስ ኃላፊዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን በርካቶች መቁሰላቸው ታውቋል፡፡ ሟቾቹ የላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ታሪኩ ፍቅሬ፣ የለቡ የወንጀል መከላከል ኃላፊ ረዳት ኢንስፔክተር ተስፋዬ ባህሩ፣ እንዲሁም የለቡ ፖሊስ ጣቢያ ወንጀል ምርመራ ክፍል ኃላፊ  ም/ኢንስፔክተር ሚካኤል ሽፈራው ናቸው ተብሏል፡፡
ግጭቱ በተከሰተበት በዚያው እለት ከሰዓት በኋላ የፀጥታ ኃይሎች በአካባቢው በመሰማራት በግጭቱ ላይ ተሳትፈዋል በሚል የተጠረጠሩ ከ200 በላይ ነዋሪዎችን በቁጥጥር ስር እያዋሉ፣ በመኪና በመጫን ወደ ፖሊስ ጣቢያዎች ሲያጓግዙ እንደነበር የአይን እማኞች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
ቤታቸው ከፈረሰባቸው ነዋሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት ግለሰብ፤ በቀን ሥራ እንደሚተዳደሩ ገልፀው፤ በ1998 ዓ.ም 150 ካሬ ሜትር ቦታ ከገበሬ ላይ በ20 ሺህ ብር መግዛታቸውንና ሁለት ክፍል የጭቃ ቤት ቀልሰው በቦታው ላይ መኖር እንደጀመሩ ይናገራሉ፡፡
 “በወቅቱ ቤቱን ስንገነባ ህገ ወጥ ነው ያለኝ የለም፤ ዛሬ ህይወቴን አስተካከልኩ ብዬ ትዳር ይዤ ሁለት ልጆች ከወለድኩ በኋላ ህገ ወጥ ነው ተብሎ ይፈርሳል መባሌ ግራ አጋብቶኛል” ብለዋል ነዋሪው፡፡
የወረዳው አመራሮች በተደጋጋሚ ስለጉዳዩ እንዳወያየቸውና አንዴ ህጋዊ የምትሆኑበትን መንገድ እንፈጥራለን ሲሏቸው፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ይፈርሳል እያሉ መክረማቸውን የተናገሩት ነዋሪው፤ በዚህ ውይይት ላይ እያሉ ረቡዕ እለት አፍራሽ ግብረ ኃይልና የመብራት ኃይል ሰራተኞች በፖሊስ በመታገዝ የኤሌክትሪክ መስመሮችን ለመቆራረጥ ሲንቀሳቀሱ ግጭቱ መፈጠሩን ማታ ከስራ ውለው ወደ ቤታቸው ሲገቡ መስማታቸውን ገልፀዋል፡፡ ፖሊስ በበኩሉ፤ ወደ ቦታው ያመሩት የፀጥታ ሃላፊዎችና የወረዳ ሥራ አስፈፃሚዎች፣ በእለቱ ቤቶችን ሊያፈርሱ ሳይሆን የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ሊሰጡ ነበር ብሏል፡፡
በአንድ የግል ድርጅት ተቀጥረው የሚሰሩ ሌላ ነዋሪ፤ ከኪራይ ቤት ለመላቀቅ በሚል ከሚያገኙት ደሞዝ በቆጠቡት 30ሺህ ብር ከገበሬ ላይ ቦታ ገዝተው፣ ባለ ሶስት ክፍል የጭቃ ቤት መስራታቸውን ይናገራሉ፡፡
 የእኔም እንዲፈርሱ ከተወሰነባቸው ቤቶች አንዱ ነው የሚሉት ነዋሪው፤ “ከእነ ቤተሰቤ ሜዳ ላይ ልወድቅ ነው” በሚል ስጋት መወጠራቸውን ገልፀዋል፡፡
“መንግስት ህገ ወጥ ናችሁ ብሎ ካመነ መንገድ እንድንሰራና ውሃ በመዋጮ እንድናስገባ ለምን ፈቀደ” ሲሉ የሚጠይቁት ነዋሪዎቹ፤ “ዛሬ ህገ ወጥ ናችሁ ያለን ወረዳ፣ እነዚህን መሰረተ ልማቶች ስንሰራ ህጋዊ ትሆናላችሁ ሲለን ነበር” ይላሉ፡፡
አብዛኞቹ የአካባቢው ነዋሪዎች ተቀጣሪ የወር ደሞዝተኞች እንጂ ሰሞኑን እንደሚባለው ትርፍ ሃብት ፈላጊዎች አይደለንም ይላሉ - ከሁለትና ሶስት ክፍል ቤት የበለጠ እንደሌላቸው በመግለፅ፡፡
ከዚህ ቀደም በዚያው አካባቢ እንዲሁ ህገ ወጥ ናችሁ የተባሉ በርካታ ቤቶች ፈርሰው እንደነበር ያስታወሱት ነዋሪዎቹ፤ በፈረሱ ቤቶች ቦታ ላይ የሪል እስቴት ባለሀብቶች ዘመናዊ ቪላዎችን እንደገነቡባቸው ተናግረዋል፡፡
ስለጉዳዩ ከመንግስት አካላት የበለጠ ማብራሪያ ለማግኘት ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ፅ/ቤት ብንሄድም የስራ ኃላፊዎችን ለማነጋገር ተደጋጋሚ ሙከራ አድርገን አልተሳካም፡፡ ቤቶች ወደሚፈርሱበት አካባቢ ቀርበን ለመመልከት ያደረግነው ሙከራ በፖሊስ ኃይል በመካከላችን ሳይሳካልን ቀርቷል፡፡
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በገርጂ አካባቢ “ወረገኑ” በተባለ ስፍራ በሺዎች የሚቆጠሩ ህገ ወጥ የተባሉ ቤቶች መፍረሳቸው የሚታወስ ሲሆን በወቅቱም ነዋሪዎች ከፖሊስ ጋር ተጋጭተው በሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡ የከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ፤ ህገወጥ ቤቶችን እየለየ እርምጃ መውሰዱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ሰሞኑን አስታውቋል፡፡

Read 16178 times