Saturday, 25 June 2016 11:42

ሼህ መሐመድ አሊ አላሙዲ ለመቄዶንያ ሁለተኛ አምቡላንስ ሰጡ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   ሞሓ የለስላሳ መጠጦች ፋብሪካ፣ ለመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል አንድ ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ሁለተኛ አምቡላንስ በዕርዳታ ሰጠ፡፡ ርክክቡ የተከናወነው መንግሥት ለመቄዶንያ በነፃ በሰጠውና አያት ኮንዶሚኒየም አጠገብ በሚገኘው 30ሺ ካ.ሜ ቦታ ላይ ሲሆን በስፍራው 5 ብሎክ ቤቶች ተሰርተው ኮተቤ የነበሩ 350 ተረጂዎች ገብተውበታል፡፡
በአያት ኮንዶሚኒየም አጠገብ የሚሰራው የመቄዶንያ አረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል፤ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ የሚፈጅ ስለሆነ፣ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች ኤክስካቫተር፣ ሎደር፣ ሚክሰር፣ ሲኖትራክ፣ የመሳሰሉትን ለተወሰነ ሰዓት ወይም ለአንድ ቀን ይዘው በመምጣት በሕዝብ ድጋፍ የሚሰራው ማዕከል ግንባታ አካል እንዲሆኑ መቄዶንያ ጠይቋል፡፡
“አገር በቀሉ መቄዶንያ እስካሁን እየተንቀሳቀሰ ያለውና አዲሱ ማዕከልም የሚሰራው በኢትዮጵያውያን በጎ አድራጎት ስለሆነ ለማዕከሉ ግንባታ ገረጋንቲ፣ የምግብ ማብሰያ እንጨት (የቤት ፍራሽ) ብሎኬት፣ አሸዋ፣ ጠጠር፣ ሚስማር፣ ቆርቆሮ የመሳሰሉትና የሙያ እገዛም በጣም ስለሚያስፈልገን፣ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ወደ ማዕከሉ መጥተው በመጎብኘትና የጎደለውን በማሟላት፣በማዕከሉ ግንባታ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ እንጠይቃለን” ብሏል፡፡
“ይበል ኢንዱስትሪያል፤ለመቶ ሰዎች በነፃ በብረት ተገጣጣሚ ቤት እየሰራ ነው፡፡ ቤቱን፣ በ3 ወር ሰርተው እንደሚያስረክቡን ነግረውናል፡፡ የአንቡላንስ ርክክብ ስነ ስርዓቱ የተከናወነበትን 4 ድንኳኖች በነፃ የሰጠን ልዩ የድንኳን ሽያጭና አከራይ ድርጅት ነው፡፡ ሌሎችም ያላቸውን ለአረጋውያኑ እንዲለግሱ እንጠይቃለን፡፡ ዳይፐር፣ ሞዴስ፣ ቅባት … ያስፈልገናል፡፡ በማዕከሉ ያሉት ብዙዎቹ የአዕምሮ ሕሙማን ናቸው፡፡ ሞዴስና ዳይፐር ሲታሰርላቸው ይቀዳሉ፣ አውልቀውም ይጥላሉ፡፡
 ያገለገሉ የቤት ዕቃዎች፣ ፖፖ፣ መዘፍዘፊያ፣ የሚገፋ ወንበር (ዊል ቸር) አልጋ፣ ፍራሽ፣ … በጣም ስለሚያስፈልጉን፣በተረጂዎቹ ስም እንጠይቃለን” ሲል ማዕከሉ ተማፅኗል፡፡
የአንቡላንሱን ቁልፍ ለመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል መስራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ለአቶ ቢኒያም በለጠ ያስረከቡት የሞሓ ለስላሳ መጠጦች ፋብሪካ የማርኬቲንግ ኃላፊ አቶ ማሩ ሞላ፤ባዩት ነገር ከልብ መደሰታቸውን ገልጸው ወደፊትም አስፈላጊ በሆነው ነገር ሁሉ ከማዕከሉ ጎን እንደሚቆሙ እንዲያረጋግጡ መልዕክት እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት መቄዶንያ፤ ምንም ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው ከአንድ ሺህ በላይ አረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን ምግብ፣ ልብስ፣ መጠለያ፣ ሕክምናና የቤተሰብ ፍቅር እየሰጠ እንክብካቤና ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የገለፁት አቶ ቢኒያም፤በዕለቱ በስጦታ የተረከበው ሁለተኛ አንቡላንስ፣ በጎዳና ላይ የወቀዱትን ወገኖች ለማንሳትና ያሉትንም ተረጂዎች ወደ ሆስፒታል ለማድረስ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ጠቅሰው፣ለፋብሪካውና ለባለቤቱ ለሼሕ መሐመድ አላሙዲ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

Read 4064 times