Saturday, 11 June 2016 12:22

ባለፉት 25 ዓመታት ከ1ሺህ በላይ የህትመት ውጤቶች ከገበያ ውጪ ሆነዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(17 votes)

   ባለፉት 25 አመታት ከ1ሺህ በላይ የሚሆኑ ጋዜጦችና መጽሔቶች ከህትመት ውጪ የሆኑ ሲሆን በአሁን ወቅት የቀሩት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው ተብሏል፡፡  ከ1993 ዓ.ም ወዲህ በአጠቃላይ 1400 ያህል የፕሬስ ድርጅቶች የምዝገባ ሠርተፍኬት መውሰዳቸውን የጠቆሙት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወርቅነህ ጣፋ፤ በአሁን ወቅት ግን በህትመት ላይ ያሉት ጥቂት ናቸው ብለዋል፡፡
ወደ ህትመት ከገቡት ውስጥ ከ2ሺህ በላይ የሚሆኑት ለመረጃ ተደራሽ ባለመሆን፣ በአከፋፋዮች ተፅዕኖ፣ በፋይናንስ አቅምና ኢ-ፍትሐዊ በሆነ የማስታወቂያ ክፍፍል ምክንያት ህትመታቸው መቋረጡን ለአዲስ አድማስ ያስረዱት አቶ ወርቅነህ የብሔር ብሔረሰቦች መብትን፣ የሃይማኖት እኩልነትንና በአጠቃላይ ህገመንግስቱን የሚፃረሩ ተግባራት ላይ ተሠማርተው የተገኙ በጣት የሚቆጠሩ የህትመት ውጤቶችም በህግ እርምጃ ተወስዶባቸዋል ብለዋል፡፡
“አንዱ የግንቦት 20 ፍሬ የህትመት ኢንዱስትሪው እንደ አሸን የፈላበት ሂደት ነው” ያሉት አቶ ወርቅነህ፤ አብዛኞቹ የህትመት ውጤቶች በራሣቸው ችግር ከገበያ የወጡ ናቸው ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል ሀገር ውስጥ ሆነው በሣተላይት አማካኝነት የሚሠራጭ ቴሌቪዥን ጣቢያ ፍቃድ ለመስጠት ባለስልጣኑ ያወጣውን የውድድር ማስታወቂያ ተከትሎ እስካሁን 27 ድርጅቶች ፍላጐት አሳይተዋል ተብሏል፡፡
ባለስልጣኑ የተወዳዳሪ ድርጅቶችን የፕሮጀክት ፕሮፖዛል እስከ ሰኔ 30 ተቀብሎ ይገመግማል ያሉት ሃላፊው፤ ፍላጐቱ ያላቸው ድርጅቶች ፕሮፖዛላቸውን እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርበዋል። ከአናሎግ ወደ ዲጅታል የሚደረገው ሽግግር ከተጠናቀቀ በኋላ ከሳተላይት ውጪ ለማሠራጨት ለሚፈልጉ ድርጅቶች ጨረታ እንደሚወጣ ያስረዱት ሃላፊው፤ ይህ ሊሆን የሚቻለው ቢያንስ ከ1 ዓመት በኋላ ነው ብለዋል፡፡  


Read 4410 times