Saturday, 11 June 2016 12:04

ጠቅላላ የፌደራል በጀት 275 ቢሊዮን ብር፣ ለፌደራል ባጀት 175 ቢሊዮን ብር፣ ለክልሎች 100 ቢ. ብር

Written by 
Rate this item
(15 votes)

በግንባታ ስራ ላይ መሰማራት ሳያዋጣ አይቀርም፡፡ ከፌደራል በጀት ውስጥ 75 ቢ. ብር ለግንባታ የተመደበ ነው፡፡
በትልቅ በጀት ቀዳሚነቱን የያዘው፣ የመንገድ ግንባታና ጥገና ነው - 46 ቢ. ብር፡፡
38 ቢ. ብር የተመደበላቸው ዩኒቨርስቲዎች፣ ሁለተኛ ደረጀ ላይ ተቀምጠዋል - በገንዘብ ብክነትና በዝርክርክነት ግን አንደኛ ሆነዋል፡፡
26 ቢ. ብር - መጠባበቂያ እህል ለማከማቸት ይውላል ተብሏል፡፡
14 ቢ. ብር ለእዳ ክፍያ (10 ቢ. ብሩ ለወለድ ክፍያ ነው)
11 ቢ. ብር ለመከላከያ፣ 2.3 ቢ. ብር ለፌደራል ፖሊስ፣ 1.2 ቢ. ብር ለብሔራዊና ለመረጃ ደህንነት
የእርሻ በጀት 8.6 ቢ ብር ቢሆንም፣ እንደ ድሮው ለምርት እድገት ሳይሆን፣ በአብዛኛው ለችግረኞች ድጐማ ተመድቧል፡፡
8.8 ቢ. ብር ለውሃ የተመደበ ነው፡፡ ግን በሃብት ብክነቱም ቀላል አይደለም፡፡ ከአስር ዓመት በፊት ይጠናቀቃሉ የተባሉ፣ ግድቦች ዘንድሮም ብዙ መቶ ሚሊዮን ብር ተመድቦላቸዋል
ለጤና አገልግሎት የሚውለው ገንዘብ 8.2 ቢሊዮን ይሆናል፡፡ ከዚህ ውስጥ 6 ቢ. ብር በውጭ አገር እርዳታ የሚሸፈን ነው - በአብዛኛውም በአሜሪካ መንግስት እርዳታ፡፡
በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት በፓርላማ ይፀድቃል ተብሎ የሚጠቀበቀው የ274 ቢሊዮን ብር በጀት፣ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የመንግስት ድርሻ እየገዘፈ መምጣቱን የሚያሳይ ሲሆን፣ የእቅድ ትኩረቶችንና ስራዎችን ይዘረዝራል፤ የሃብት ብክነት አደጋዎችንም ይጠቁማል፡፡ ፌደራል መንግስት ከሚያንቀሳቅሰው ሃብት ውስጥ 40% ያህሉ ለግንባታ የሚውል በመሆኑ፤ የመንግስት የእቅድ ትኩረት፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ፣ ሰራተኞችና ኢንቨስተሮች በግንባታ መስክ እንዲሰማሩ የሚገፋፉ ነው ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ በሌላ በኩልም፤ በሃብት ብክነት ኦዲተርን ያማረሩ  ዩኒቨርሲቲዎች፣ ብዙ ገንዘብ የሚመደብላቸው ተቋማት ስለሆኑ፣ የብክነትና የሙስና አደጋው ከፍተኛ እንደሆነ ያመላክታል - በጀቱ፡፡
በእርግጥ፣ ትልቅ በጀት ከተመደበ፣ ብዙ ሃብት ይባክናል ማለት አይደለም፡፡ ከሌሎች ስራዎች ጋር ሲነፃፀር፣ ለመንገድ ግንባታ የሚውለው ሃብት በአመዛኙ ውጤታማ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በበጀት ትልቅነት ደግሞ የመንገድ ግንባታን የሚስተካከል የለም - 46 ቢ. ብር ነው የተመደበለት፡፡ በዚህ መስክ ብዙ ብክነት የማይታየውና የአገሪቱ የአስፋልት መንገድ የተሻሻለው አለምክንያት አይደለም፡፡
ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ፤ የመንገድ ግንባታ በደህና ሙያዊ መሰረት ላይ መዋቀሩ፣ እንዲሁም ዋና ዋናዎቹ የመንገድ ግንባታዎች በአለማቀፍ የጨረታ አሰራር ለተለያዩ ኩባንያዎች በኮንትራት የሚሰጡ መሆናቸው፤ ለውጤታማነቱ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፌደራልና በክልል ደረጃ፣ መንግስታዊ ድርጅቶች ወደ መንገድ ግንባታ እንዲገቡ መደረጋቸው ግን፣ ለወደፊት አሳሳቢ መሆኑ አይቀርም። የሃብት ብክነትን ያስከትላሉ፡፡ በፌደራልና በክልል መንግስታዊ ድርጅቶች አማካኝነት ላለፉት 12 ዓመታት ሲካሄዱ የቆዩ የግድብ እና የመስኖ ፕሮጀክቶችም፣ አደጋውን አጉልተው ያሳያሉ፡፡
ባለፉት ዓመታት፤ በርካታ ቢሊዮን ብር የፈሰሰባቸው የተንዳሆ፣ ከሰምና የረብ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች፣ የዛሬ አስር ዓመት እንዲጠናቀቁ ነበር የታሰበው፡፡ ነገር ግን ዘንድሮም 500 ሚሊዮን ብር ተመድቦላቸዋል፡፡
ለአስር ዓመት በተጓተቱት ስራዎች ብዙ ቢሊዮን ብር ሃብት ባክኗል፡፡
ነገር ግን በሃብት ብክነትና በዝርክርክ አሰራር፣ ዩኒቨርሲቲዎችን የሚፎካከር አልተገኘም፡፡ ከአመት አመት የዩኒቨርስቲዎቹ አሰራር ከመስተካከል ይልቅ እየተባባሰ በመምጣቱ የተማረሩት የፌደራል ዋና ኦዲተር፤ ዩኒቨርሲቲዎቹ በቀጥታ ሃብት እንዳያንቀሳቅሱ መከልከልና፣… በተለይ የእቃ ገዢዎችን በበላይነት የሚመራ ሌላ ተቋም መፍጠር እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡
ኦዲተርን ያማረሩት 34 ዩኒቨርስቲዎች ናቸው - በዓመት ውስጥ 38 ቢሊዮን ብር የሚመደብላቸው። የሃብት ብክነቱና የሙስና አደጋውም የዚያኑ ያህል ከፍተኛ እንደሚሆን፣ የዋና ኦዲተሩ ተደጋጋሚ ሪፖርት ይመሰክራል፡፡
የመጠባበቂያ እህል ለማከማቸት የተመደበው የ26 ቢሊዮን ብር በጀት፣ በሦስተኛ ደረጃ የሚጠቀስ ሲሆን፤ ከዚህ ቀጥሎ ከፍተኛ ድርሻ የወሰደው የብድር ክፍያ ነው፡፡ መንግስት ብድር ለመክፈል ከሚያውለው 14 ቢሊዮን ብር ውስጥ፣ 10 ቢ. ብር ያህሉ የብድር ወለድ ነው፡፡ እንዲህም ሆኖ በመንግስት በጀት ውስጥ የማይካተቱ ሌሎች ከባድ ብድሮች አሉ፡- የቴሌ፣ የስኳር ፕሮጀክቶች፣ የኤልፓ፡፡ እነዚህ ሲጨመሩበት፣ መንግስት የውጭ ብድር ለመክፈል በዓመት ከሃያ ቢሊዮን ብር በላይ ያወጣል፡፡
ነገር ግን፣ አሁንም የበጀት ጉድለት ለመሙላትና የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን፣ ተጨማሪ ብድር መከማቸቱ አይቀርም፡፡ በተለይ ውጤታማ ያልሆኑ ፕሮጀክቶችና ምርታማነትን የማያሳድጉ ዕቅዶችን ለማስፈፀም የሚመጡ ብድሮች ለወደፊት አደጋ ናቸው፡፡ ከአስር ዓመት በፊት አብዛኛው የእርሻ በጀት፣ ለምርጥ ዘር ምርምር፣ ለቴክኒክ ስልጠና፣ ለማዳበሪያና ለመሳሰሉ ጉዳዮች ነበር የሚመደበው - ምርታማነትን ያሳድጋሉ በሚል፡፡ ከዚያ ወዲህ ግን ችግረኛ ገበሬዎችን ለመደጐም የሚውለው የእርሻ በጀት እየገነነ መጥቷል። ነገር ግን፣ ድጐማ የሚደረግላቸው ገበሬዎች፤ ወደ ምርታማነት ሲያድጉ አይታይም፡፡ እናም ድጐማው እየተስፋፋ ዘንድሮ 6 ቢሊዮን ብር ደርሷል - ከጠቅላላው 8.2 ቢ. ብር የእርሻ በጀት፡፡

Read 2903 times