Saturday, 04 June 2016 12:30

በተቆለፈበት ቤት ውስጥ የሚኖር ህዝብ!!

Written by  (ይትባረክ ዋለልኝ) yetebarek@yehoo.com
Rate this item
(3 votes)

“ኔሽን ኢን ዘ ኮንቴምፖራሪ” የስዕል አውደርዕይ

  ባለፈው ረቡዕ በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴዝ የስዕል አውደ ርዕይ የተከፈተ ሲሆን ሰዓሊ አዲስ ገዛኸኝ፣ ደረጀ ደምሴ፣ ታምራት ገዛኸኝና ሱራፌል አማረ የስዕል ሥራዎቻቸውን ለዕይታ አቅርበዋል፡፡ ሰዓሊያኑ በእውቀትም በልምድም የዳበሩ፣ ለበርካታ ጊዜያት በሀገር ውስጥና በውጭ አገራት፣ሥራዎቻቸውን  በቡድን ያቀረቡ ናቸው፡፡  በዚህ አውደ ርዕይ ላይም  በጠቅላላ 27 የጥበብ ስራዎችን ለተመልካች ለዕይታ ያቀረቡ ሲሆን ስራዎቹም የሰዓሊያኑን የአሳሳል ዘዬ፣ ሃሣብ፣ ፍልስፍና እና ተጨባጩን ህይወታቸውን የሚያሳዩ ናቸው፡፡
ሰዓሊ አዲስ ገዛኸኝ ለዕይታ ካቀረባቸው 6 ሥራዎች ውስጥ “የሚፈርስ ከተማ” በሚል ርዕስ የሰራቸው 2 ስዕሎቹና  በርን የድርሰቱ አካል አድርጐ የተጠበበባቸው 3 ስራዎች እጅግ ግዙፍ ሐሣብ የሚያንጸባርቁ ናቸው፡፡
 የከተማችንን እያፈረሱ የመገንባት ሂደት በጠሊቅ እይታ እንደተመለከተው የስዕል ስራዎቹ ይመሰክራሉ፡፡
ከሚፈርሰው ቤታችን ውስጥ ያለውን የዛሬንና የወደፊቱን ህይወታችንን በቀለሞች በሚገባ ለማሳየት ሞክሯል፡፡
ይሄን ሥራውን በተመለከተ ሰዓሊ አዲስ ገዛኸኝ ሲናገር፤“እየሰራሁት ያለሁት ከተማችን ላይ የሚታዩትን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ነው፡፡ አዲስ ነገር የለውም፡፡ አዲሱ ነገር አቀራረቡና እይታ ብቻ ነው፡፡ በዚህ ስራዎቼ ዋና ዓላማዬ የማውቀውን ማህበረሰብ፣ ኑሮውን ከምትፈርሰው ከተማ ጋር አጣምሮ ማሳየት ነው፡፡” ብሏል፡፡  ሰዓሊው ማብራራቱን ቀጥሏል፤“መፍረስ የሚለው ቃል ብዙ ትርጉም አለው፤አዲስ ከሚፈርሰው ቤት ውጪ ሰው ይፈርሣል፡፡
 የቤቶቹ ቀለሞች፣ በርና መስኮቶቹ የእኛ መልክ ናቸው - እነሱን ስናይ እራሳችንን እናያለን፡፡ እንግዲህ የሚፈርሰውን ዘልቆ መመልከት የተመልካቹ ሥራ ነው፡፡
እኔ መንገድ ነው የሰጠኋቸው፤ ከሚፈርሰው ቤት ጀርባ ምን እንዳለ ይድረሱበት፡፡ ይመልከቱ ይወቁ”
 ቤት ሚስጢር ነው፡፡ ቤት ውስጥ ታሪክ አለ፡፡ ቤት ውስጥ የአኗኗር ዘዬ፣ የትውልድ ቅብብሎሽ፣ ተረት --- አለ፡፡ ቤት ውስጥ ፍልስፍና አለ፡፡ ቤት በአገር ይመሰላል፡፡ የአንድ እናት አባት ልጆች፤ የተለያየ ፆታ፣ ቀለም፣ አስተሳሰብ፣…አለ፡፡ ማንነታችን የተገነባው ቤት ውስጥ ነው፡፡
 የተለያዩ ቤቶች በአንድ ቦታና አካባቢ መኖር ደግሞ ቀደም ብዬ የዘረዘርኩትን የተናጥል የቤትን ፅንሰ ሐሳብ አጣምሮ የሚይዝ ነው፡፡ በመሆኑም የአንድን አካባቢ እያፈረሱ መገንባት ውስጥ ሰውን ያማከለ አይመስለኝም፡፡ ሰዓሊው በበኩሉ፤ በሚፈርሰው ነገር ውስጥ ውበት አለ ባይ ነው፡፡ “በሚፈርሰው ነገር ውስጥ ውበት አለ፡፡ ፍቅር… ብዙ ነገር አለ፡፡ እየደጋገመ ቤታችን ቢፈርስብን እንኳን በውስጣችን የምናቆየው አንድነታችን፣ ታሪካችን፣ ፍቅራችን፣ ውበታችን አለ” በማለት አስረድቷል፡፡  
ሰዓሊ አዲስ በሌላ ስዕሉ፣ ከፈረሰው ቤት ውስጥ እንደ ተምሳሌት /Symbol/ አድርጐ የተጠቀመባቸው 3 የበር ስራዎች፣ ድንቅ ሃሳብ የተሸከሙ ናቸው፡፡ “ባዶ 6”፣  “ፎቶግራፍ ማንሣት ክልክል ነው”፣ እንዲሁም “በእዳ የተዘጋ ቤት” የሚሉት ስራዎቹ ሁሉም ቢር ናቸው፡፡ ሦስቱ ተምሣሌታዊ አድርጐ የሰራቸው በሮች፤- በቀለም፣ በመጠን፣ በባህሪ የተለያዩ ቢሆኑም ተመሳሳይ ሃሳብ ነው የሚያንፀባርቁት፡፡
ስዕሎች እኔን፣ ህብረተሰቡን፣ ሀገሬን---በሚገባ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በር ለአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት አስፈላጊ ነው፤ መግቢያና መውጫው.. መተንፈሻው፡፡ ለአንድ ሀገርም ሁለንተናዊ እድገት በር ወሳኝ ነው፤ የራስን ለመስጠትም ሆነ የሌላውን ለመቀበል፡፡ ይሄ እማሬያዊው ትርጉም ነው፡፡  
 የተቆለፈባቸው 3ቱ በሮች ምን ትርጉም፣ምን መልዕክት አዝለው ይሆን? ሰዓሊው ምን ሊነግረን ፈልጎ ነው?
“እነዚህ ስራዎቼ ሁሉም የተቆለፉ በሮች ናቸው፤ መቆለፋቸው --- መዘጋታቸው የሀገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ያሳያል፡፡ ህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ስሜት በሚገባ ያንጸባርቃል፡፡ በሮቹ እያንዳንዶቹ የራሳቸው ሃሳብና መልዕክት አላቸው፡፡ 3ቱም የተለያዩ ናቸው፤ የግለሰብ በር፣ የመንግስት በር፣ የፓርቲ (የማህበረሰብ) በር አሉ፡፡ እነዚህ በሮች የተቆለፉ፤ የተዘጉ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ከግለሰብ እስር ቤት እስከ መንግስት እስር ቤት የሚያሳይ ነው፡፡ ገፋ ካልክ ሌላም አለ” ይላል - ሰዓሊ፡፡ የአዲስን ሥራዎች በአንክሮ ሲመለከት የነበረውን ታዲዎስ የተባለ ጎብኚ አስተያየት ጠየቅሁት፡-“በአገራችን ሃሳብ የታሰረበትን ሁኔታ ያሳያልለ፤መወያየት፣ መነጋገር ---- ስለ አንድ ስርዓት ወይም አንድ ቡድን፣ ሃሳብ ማቅረብ፣መተቸት የተከለከለ----የተዘጋ ነገር ነው” አለኝ፡፡ ግን አስተያየቱን እንዳልቋጨ ገብቶኛል፡፡ “የሀገራችንን የመናገር ነፃነት መጥፋት፣ የግለሰቦችን በፍርሃት መቆለፍ፣ መዘጋት…እነዚህ የጥበብ ስራዎች በእጅጉ ያሳያሉ” ብሏል - ታዲዎስ፡፡“በሰዓሊ አዲስ ሶስት ግሩም ስራዎች ውስጥ ሀገሬን በሚገባ አይቻታለሁ” ያለው ደግሞ የህክምና ባለሙያው ዶ/ር ዘርይሁን ግርማ ነው፡፡ “እነዚህ ሶስት፣ የተቆለፈባቸው የጥበብ ስራዎች ማለትም በዕዳ ከታሸገበትና ከተቆለፈበት አንስቶ፣ በየደረጃው የሰው ልጅ በምን አይነት እስር ቤት ውስጥ እየኖረ እንዳለ የሚያሳይ ነው፡፡ እነዚህ በርካታ በሩ የተዘጋባቸው ቁልፎች፣ “ህጎች” ናቸው፡፡
 በህጎች የታሰረ ህዝብ ነፃነት የለውም፡፡ እነዚህ ቁልፎች የመናገር፣ የመወያየት፣ የመፃፍ … መብት፣ ከንድፈ ሀሳብ በዘለለ እንደ ሌለ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ እነዚህ ቁልፎች የፍርሃት ዲሞክራሲ መኖርን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ እኔ በጣም የገረመኝ አዲስ፣ እኛን ከተዘጋባቸው በብዙ ቁልፎች ውስጥ ከተቆለፈበት በር ጀርባ ማድረጉ ነው፡፡ ጥበብ ማለት እንዲህ  ነው፡፡
 ጊዜን፣ ዘመንን፣ የህብረተሰቡን አሉታዊና አዎንታዊ ጎን ማሳየት አለበት፡፡ በዚህ ረገድ አዲስ ግሩም ስራ አቀብሎናል” ሲል ዶ/ር ዘርይሁን ሰዓሊውን አድንቆታል፡፡   ስሙ እንዲገለፅ ያልፈለገ ሌላ የኪነ ጥበብ ባለሙያ በሰጠው አስተያየት፤“የአዲስ ስራ የራሳችንን የስነ ጥበብ ተጨባጭ ሁኔታ በደንብ የሚያሳይ ነው፤ በጥበቡ ዙሪያ መቼ መነጋገር አለና፡፡ ስነ ጥበብን በተመለከተ ሀሳብ፣ ትችት (ሂስ) የሚሰጥ ማን አለ? እርስ በእርሳችን ተፈራርተን እንዳንነጋገር፣ እንዳንወያይ የሚያደርግ ዘመን ላይ መድረሳችንን የአዲስ ስራ ያሳየናል፡፡” ብሏል፡፡ በመጨረሻም ሰዓሊ አዲስ እንዲህ ብሎኛል፤“በዚህ ስራዬ በውስጤ የታየኝ፣እነዚህ የተዘጉ በሮች ናቸው፡፡
 በሌላ ጊዜ በሮቹ ሲከፈቱ ደግሞ እኔም የተከፈ በር እስላለሁ”፡፡ ሌላው የአውደ ርዕዩ ተሳታፊ፣ ሰዓሊ ደረጄ ደምሴ፣ 6 የስዕል ስራዎችን ያቀረበ ሲሆን ሁሉም  “ሀገር” የሚል ርዕስ ነው የሰጣቸው፡፡ የደረጀ የአሳሳል ዘዬና የቀለም አጠቃቀሙ ከሌሎች ሰአልያን የተለየ ነው፡፡ የሀገርን ሁኔታ መሰረት በማድረግ ነው የሰራቸው፡፡ የዶርዜ ብሄረሰብን የቤት አሰራር መሰረት ያደረጉ እንደሆነ ሰዓሊው ይናገራል፡፡
“ዶርዜዎች ቤት ከሰሩ በኋላ ያ ቤት በስብሶ ሲወድቅ፣ ሌላ አካባቢ ሄደው ቤት ይሰራሉ እንጂ ሳያረጅ ሳይበሰብስ አፍርሰው ቤት አይገነቡም፤ እኔም ይህን የህይወት ኡደት መሰረት አድርጌ፣ የሰው ልጅን ህይወት ለመቃኘት ነው የሞከርኩት” ብሏል፡፡
እውነት ነው፡፡ የደረጀ ስራዎች የሰው ልጅ የተፈጥሮን ኡደት ጠብቆ መጓዝ አለመቻሉ የሚያመጣውን አሉታዊ ጎን በስዕሎቹ ውስጥ በቀለም በማደብዘዝና በማጉላት ሊያሳየን ሞክሯል፡፡ ህይወት ኡደቷን ሳትጠብቅስ ስትጓዝ ትበላሻለች፤ ሰውም አገርም ይበላሻል የሚሉ ሀሳቦችን ስራዎቹ አጉልተው ያሳያሉ፡፡
 በመጨረሻም እኔ በእነዚህ ሁለት የስዕል ባለሙያዎች ስራ ላይ አተኮርኩ እንጂ የሱራፌል አማረም የታምራት ገዛህኝም ስራዎች የተመልካችን ቀልብ የሚይዙ፣ መንፈስን የሚያስገዙ ናቸው፡፡
 በተረፈ የዘርፉ ባለሙያዎች፣በጥበብ ስራዎቹና በሰዓሊያኑ ፍልስፍና ዙሪያ ውይይት ቢያደርጉ በእጅጉ ጠቃሚ ነው፡፡ ተመልካቹም በጥበቡ ዙሪያ ያሉትን የተለያዩ አመለካከቶችንና ጥበቡ የደረሰበትን ፍልስፍና የማወቅ ዕድል ያገኛል፡፡ ቸር እንሰንብት!!

Read 2298 times