Saturday, 04 June 2016 12:21

የሥዕል ትርኢት ዳሰሳ Exhibition Review

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የትርዒቱ ርዕስ፡ W@tch me…
ሠዓሊ፡ ቴዎድሮስ ሐጎስ
የትርዒቱ አይነት፡ የግል፤ የቀለም ቅብ ሥራዎች
ብዛት፡ ሃያ አራት
የቀረበበት ቦታ፡ አሊያንስ ኢትዮ-ፍራንሴስ፡ አዲስ አበባ
ጊዜ፡ ሚያዚያ 03-22፡2008 ዓ.ም
ዳሰሳ አቅራቢ፡ ሚፍታ ዘለቀ (የሥነ - ጥበብ አጋፋሪ)


እንደ መሻገሪያ
ልክ እንደ ወቅታዊ የሀገራችን እውነታ ሁሉ ሥነ - ጥበባችንም በበሰለና በተብላላ የግል የሥዕል ትርዒት አቅርቦት ድርቅ የተመታ እስኪመስል ነባራዊ መሰረት ይዞ፣ ዘመንን የሚተርክና ዘመን የሚሻገር ሃሳብና ክህሎት የሚታይበት ትርዒት በናፈቀኝ (ን) ወቅት ነበር ሠዓሊ ቴዎድሮስ ሐጎስ ‹W@tch me…›ን ይዞ ከተፍ ያለው፡፡  
ለነገሩ፤ የማሳያ ቦታዎች እጥረት፤ በወኔ የመነሳሳት፣ የሞራል፣ የመስሪያ ቦታ፣ የቁሳቁስና ባጠቃላይ የመኖር ዘዴ እጥረት፤ ብሎም በሚሰሩት የሥነ - ጥበብ ስራ የዕምነትና የፍልስፍና እጥረትና የመሳሰሉት ተግዳሮቶች የኢትዮጵያ ሥነ - ጥበብን ጋሬጣ የተሞላበት እንዲሆን ባደረጉበትና አብዛኛዎቹ ዘመነኛ ሠዓልያኖቻችን “የጥበብ መጀመሪያው ኤግዚቢሽን (በተለይ solo exhibition) መፍራት ነው!” የሚለውን ስላቅ እውነታ አድርገው የተቀበሉ በሚመስልበት በዚህ ወቅት ነው ሠዓሊ ቴዎድሮስ ‹የደረስኩበትን እንካችሁ!› ለማለት የደፈረው!
ይህ ዳሰሳ ግላዊ፣ ሃሳባዊና ሂሳዊ አተያዬን ለማንፀባረቅ፤ የትርዒት ዳሰሳ አናስራትን (elements) በጨረፍታም ቢሆን ለማስተዋወቅ የተጻፈ መሆኑንና ምንም ዓይነት ተቋማዊ መሰረትና ዝንባሌ እንደማይከተል ልገልጽ እወዳለሁ!!
*  * * *  *
ይመልከቱኝ …. (1)
የትርዒቱ ርዕስ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተሰየመ፣ የተጻፈ ወይም የተነገረ ሲሆን W@tch me … የተሰኘ ነው፡፡ ይህ ስያሜ አማካይ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታ ላለው ማንኛውም ሰው ውስብስብ አይደለም፡፡
ይመልከቱኝ … (2)
በትርዒቱ የቀረቡ ሁሉም ስራዎች “ይመልከቱኝ … ፤ እኔን ይመልከቱኝ …. እኔን ይመልከቱኝ እንጂ …” ማለት የሚፈልጉ ብቻ ሳይሆኑ እንድንመለከታቸው የሚያስገድዱ ጭምር ናቸው፡፡ እንዴት? ቢባል ዋነኛው ድርሰታዊ አወቃቀራቸው (Composition) ሲሆን የድርሰቱን ገዢ ቦታ በበላይነት ተቆጣጥረውት ነው የሚታዩትና የሚያዩን፡፡ በተጨማሪም ፊት ተደግነው (frontal ሆነው) የተደራሲን እይታዊ ንፍቅ (Visual inter-surface of the viewer’ን) እንዳይፈናፈን ወጥረው በመያዝ፣ ትኩረቱ ሁሉ እነሱ ላይ እንዲሆን ያስገድዱታል፡፡ ታዲያ ይህን ሁሉ አቅም ተጠቅመው ግዘፍ ከነሱ በኋላ ምን እንድናይና ምን አድርጉ ነው የሚሉን?
ብዙ ይላሉ፡፡ ለምሳሌ፡ ‹ይመልከቱን… እኛ አራታችንን …!!!› ይላሉ፡፡
ከትርዒቱ አዳራሽ መግቢያ በስተግራ ያለው ግድግዳ፣ የሁለት አንጋፋ ሰዓልያን የፊት ገጽ (portrait) የተሳለባቸውና እያንዳንዳቸው መቶ ሰማንያ በመቶ ሃያ ሴንቲ ሜትር አውታር ያላቸው ሁለት ስራዎች ተንጠልጥለውበታል፡፡
(ግድግዳው ከዘመናት በፊት ከብርቱ ደንጊያ የታነጸ በመሆኑ እንጂ ሁለቱ ስራዎች እንደተሸከሙት የሀሳብ ክብደት ቢሆን ግን ገና አንደኛው ስራ ሊሰቀልበት ሲሞክር ተብረክርኮና ተፈረካክሶ የእንቧይ ካብ ሆኖ ይቀር ነበር)፡፡ ቴዎድሮስ ለነዚህ ስራዎቹ ዓይነ - ግብ (Subject - matter) ያደረጋቸው ሁለቱ አንጋፋ ሠዓልያን፣ ሠዓሊ ታደሰ መስፍንና ሠዓሊ መዝገቡ ተሰማ ናቸው፡፡
እኒህ ሁለት ልሂቀ ጠበብት፤ ዘመናዊው የኢትዮጵያ ሥነ - ጥበብ ገና በሁለት እግሩ ለመቆም ደፋ ቀና በሚልበት ዘመን፣ አብዮት ፈንድታ ቋንጃውን መበጠስ ከጀመረችበት ከ1960ዎቹ አንስቶ እስከ አሁኑ ገና አቅጣጫውን መወሰን ካቃተው ዘመነኛዊው የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ትንታግ ድረስ ተመስጦአቸውን ሳያደፈርሱ፣ ጥናታቸውን ሳያቋርጡ፣ ባሕር ሃሳባቸውንና ጥልቅ እውቀታቸውን ሳይሰስቱ ለተማሪዎቻቸው ሲለግሱ፣ ትውልድ ሲገነቡና ራሳቸውን ሲወልዱ የኖሩ ብርቅዬና የቁርጥ ቀን የሀገር ልጆች ናቸው፡፡
 ድንብርብሩ እየወጣ አንዱን ሲይዝ ሌላውን እየለቀቀ በመጓዝ ላይ ባለው የስነ ጥበባችን ታሪክ ውስጥም አንዳችም ሳይረበሹ ይልቁንስ አቅጣጫቸውን እያጠሩ የሚጓዙት እኒህ አንጋፋ ሰዓልያን፤ የደረሱበትን ከፍታ አጥንቶ ተገቢው ቦታ ሊሰጣቸው ባልተቻለበት ሁኔታ በምስላዊ (figurative art) የሄዱበትን ርቀት ለመዘከር እንኳ ልብ በጠፋበት ዘመን ነው ቴዎድሮስ ከሃያ ስምንት ሳንቲ ሜትር የማትበልጥ ረቂቅ የፊት ገጻቸውን በዚያ ግዙፍ ሸራ ላይ ያለ ስስት እንዲናኙ፣ እንዲገዝፉና እንዲንፏለሉ ያደረገው፡፡ ከዚህ የላቀ አክብሮትና ዋጋ ለሁለቱ አንጋፋ ሠዓልያን የትም ተችሮ  አያውቅም! ታዲያ “ይመልከቱ … ይመልከቱ እንጂ … ማለት ይህ ነው ‘ንጂ! ደግ ያደረግህ ቴዎድሮስ!
ከአንጋፋውያኑ ሰዓልያን ትይዩ ደግሞ በተመሳሳይ ጥልቀትና አውታር እንዲሁ በሀገራችን የዘመናችን የሥነ - ጥበብ ፎቶግራፍ ፋና ወጊና ቀድሞ ሰዓሊ የነበረው ሚካኤል ጸጋዬ፤ እንዲሁም በዓለም-ዓቀፉ የሥነ-ጥበብ መድረክ ዘመንኛዊውን የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ እያስጠራ ያለውን ሠዓሊ ዳዊት አበበ በግዝፈት አስቀምጧቸዋል፡፡ በገለልተኛው የሥነ-ጥበብ ታሪካችን ቅብብሎሹን በማስቀጠል ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ካሉ ጥቂት ወጣት ሠዓልያን መሃል ሁለቱን መርጦ መሳሉ፣ ቦታ መስጠቱና የሚጠብቃቸውንም ኃላፊነት ማመላከቱ ሌላኛው የቴዎድሮስ ሐጎስ ‹ይመልከቱ› …. ነው ባይ ነኝ፡፡
ይመልከቱኝ … (3)
የፊት ገጽ እንደ አንድ የሥነ - ጥበብ ዘዬ ስንመለከተው፤ ጥንታዊ መሰረት ያለውና እስከ አሁኑ ጊዜም በስፋት የሚሰራበት ዘዬ ነው፡፡ ለምሳሌ ከጥንታዊት ግብጽ ሥነ - ጥበብ፣ ከጣሊያን ሬኔይሳንስ፣ ከመካከለኛው የአውሮፓ ሥነ - ጥበብ ከፍታ እስከ ዘመንኛ ፎቶግራፍ በሰፊው ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ በዓይነትም ቢሆን ከሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ፣ የታዋቂ ሰዎች፣ የእርቃን፣ የተራና ተርታ ሰዎችን የፊት ገጽ የመስራት ዘዬ በሥነ - ጥበብ ታሪክ ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በዓለም ታሪክም እንደነ ሊዎናርዶ ዳቬንቺ፣ ሬምብራንት፣ቪንሴን ቫን ጎ፣ ፓብሎ ፒካሶን የመሳሰሉ ስመ ጥር የዓለም ሠዓልያንም የፊት ገጽ በመስራት ይታወቃሉ፡፡
ቴዎድሮስ ሐጎስ፤ በዚህ ዘዬ ከአስር ዓመት በላይ ከመስራቱም ባሻገር ምናልባትም የራሱን ዘዬ በማዳበር፣ ስራዎቹ ጥልቀት እንዲኖራቸው በመመራመርና ሃሳቡን በማጠናከር ረገድ ግንባር ቀደም ዘመንኛ ሠዓሊያችን ነው ማለት እችላለሁ፡፡ ቴዎድሮስ የራሱን ዘዬ አዳብሯል? አዎ! ይህን ደግሞ ማየት የምንችለው የሚሰራቸውን ሰዎች የፊት ገጽ ከእውነታ አግዝፎ (larger than life size) ነው የሚሰራቸው፡፡ ከእውነታ አግዝፎ መስራት አዲስ ነገር ባይሆንም በእያንዳንዱ ስራዎቹ ይህንን የሙጥኝ ብሎ መስራቱ ዘዬውን ለማዳበር ረድቶታል፡፡
 በዚህ ትርዒት ከቀረቡ ስራዎች ሶስት አራተኛዎቹ ሞዴሎቹ የቀን ሰራተኞች ናቸው፡፡
የቀን ሰራተኞች እንደ ዓይነ - ግብ (Subject matter) መጠቀሙ ራሱን የቻለ ውሳኔና ድንጋጌ ነው፡፡ የቀን ሰራተኞች በአሁኗና በግንባታዎች አማካኝነት ዘመንኛ ለመሆን በምትጣጣረው ኢትዮጵያችን ያላቸውን ሚና ማንም አይዘነጋውም፡፡ ቴዎድሮስ ይህንን ሃቅ ከፊታቸው ይመልከቱ … እያለን ይመስለኛል፡፡
አለም አላለም ግን ሠዓሊው እንካችሁ ያለውን ተመልካቹ የመጠየቅ፣የመመርመርና የማዛመድ መነሳሳት ቢኖረው፣ ሠዓሊውን ከመረዳት አልፎ ለግል አስተሳሰቡና ለግንዛቤው የሚጠቅሙ አያሌ መንገዶችን መፍጠር ይችላል ባይ ነኝ፡፡ ደግሞ ምንስ ቢሆን የእነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎችን አኗኗርና አመለካከትን መመልከት የለብንም? ከ“ይመልከቱ” … ብዙ ነገር ማየት ይቻላል፡፡ ሌላው እንደ ዓይነ - ግብ (Subject matter) የተጠቀማቸው የቀን ሰራተኞች የለበሱት ልብስና በልብሶቹ ላይ የታተሙት ጽሁፎች ነው፡፡
ቴዎድሮስ እንደነገረኝ ከሆነ፣ በልብሶቹ ላይ የታተሙት ጽሁፎችን ትርጓሜ ለባሾቹ አያውቁትም፣ አያስጨንቃቸውምም፡፡ ይህ ደግሞ በሰፊው ህዝብም የሚስተዋል ነው፡፡
ይህንን ከአያሌ ጥያቄዎች ጋር ማገናኘት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ግሎባላይዜሽን የሀገርና የግለሰብ ማንነት ላይ ሊያደርሰው የሚችለው ተጽዕኖ፤ ተጽዕኖዎቹን ለመቋቋምም ሆነ በተጽዕኖዎቹ ስር ለመውደቅ እንደ ሀገርና ግለሰብ የገነባነው ማንነት ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ለማሰላሰል ያስችሉናል፡፡
ምናልባት የመጨረሻ “ይመልከቱ”… የአንዳንድ ሞዴሎቹ አቋቋም፡
አቋቋማቸው ከትከሻቸው ዞር ያሉ፣ እይታቸውን ወደ ተመልካችና ወደ ሩቅ ያደረጉ ሰዎችን እንደ ሞዴል ተጠቅሟል፡፡
እንዲህ አይነት አቋቋሞች በአብዛኛው ልበ ሙሉነትን፣ ሩቅ አላሚነትን፣ ተስፈኝነትንና ታላቅነትን አመላካች ናቸው፡፡
ከነዚህም መሃል አንደኛውን የሥዕል መስሪያ ቀለም፣ ሌላኛውን ደግሞ በአንድ እጁ ደብተር በሌላኛው እጁ ሹራብ አንጠልጥሎ ሰርቷቸዋል፡፡ … ቀለምና ደብተር ምንን ይወክላሉ? ለምን ሌላ ነገር አልያስያዛቸውም?
እንደው ሳስበው  W@tch me…. ን መዳሰስ ብቀጥል ይመልከቱኝ … እያልኩ ላተክናችሁ ነው፡፡ ስለዚህ ይብቃኝ፡፡ እስቲ እናንተም የበኩላችሁን … በሉኝ! ቸር እንሰንብት፡፡

Read 1162 times