Saturday, 04 June 2016 12:12

የፔሌ ውድ ንብረቶች ለጨረታ ሊቀርቡ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

3.5 ሚሊዮን ፓውንድ እንደሚያወጡ ይገመታል

    ብራዚላዊው የእግር ኳስ ንጉስ ፔሌ፤ በተጫዋችነት ዘመኑ የተሸለማቸውና ይጠቀምባቸው የነበሩ የተለያዩ ውድ ንብረቶች በመጪው ወር ለንደን ውስጥ በሚካሄድ ጨረታ ለሽያጭ እንደሚቀርቡና 3.5 ሚሊዮን ፓውንድ ያወጣሉ ተብሎ እንደሚገመት ሮይተርስ ዘገበ፡፡
ጁሊየንስ ኦክሽን በተባለው አጫራች ኩባንያ አማካይነት ለጨረታ ከሚቀርቡት የፔሌ ውድ ንብረቶች መካከል ዋንጫዎች፣ ውድ የእጅ ሰዓቶች፣ ሜዳሊያዎች፣ ኳሶችና ሌሎች የስፖርት ቁሳቁስ ይገኙበታል ያለው ዘገባው፣ ተጫዋቹ ከሽያጩ ከሚገኘው ገቢ የተወሰነውን በብራዚል ለሚገኝ አንድ የልብ ህክምና ሆስፒታል በስጦታ ለማበርከት ማቀዱን ገልጿል፡፡
ለጨረታው ከቀረቡት እቃዎች መካከል በዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ቅርጽ የተሰራው የፔሌ ውድ ዋንጫ፣ እስከ 420 ሺህ ፓውንድ ያወጣል ተብሎ እንደሚገመት የጠቆመው ዘገባው፣ ሜዳሊያዎቹ 141 ሺህ ፓውንድ፣ 1ሺኛዋን ጎሉን ያስቆጠረባት ታሪካዊት ኳስም 42 ሺህ ፓውንድ ይሸጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል፡፡
የ75 አመቱ ብራዚላዊ የእግር ኳስ ኮከብ ፔሌ፤ በአለማችን እግር ኳስ ታሪክ ደማቅ ተግባር የፈጸመ፣ ዘመን የማይሽረው ተጫዋች እንደሆነ የገለጸው ዘገባው፣ “የክፍለ ዘመኑ የዓለማችን ምርጥ የእግር ኳስ ተጫዋች” በሚል በፊፋ መሸለሙንም አስታውሷል፡፡

Read 1387 times