Saturday, 04 June 2016 12:04

በፈተና ስርቆት ላይ ፖሊስ ምርመራውን አጠናክሮ ቀጥሏል

Written by 
Rate this item
(14 votes)

    ለ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና መቋረጥ ምክንያት የሆነውን የፈተና መሰረቅ ጉዳይ ፖሊስ እየመረመረ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ለድጋሚ ፈተና የህትመትና የመጠረዝ ስራ እየተከናወነ ነው ተብሏል፡፡
በስርቆቱ ጉዳይ የሚደረገው ምርመራ በተጠናከረ መልኩ ሙሉ ለሙሉ በፀጥታ ኃይሎች መያዙን ያስታወቁት በትምህርት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አህመድ ሲራጅ፤ ጉዳዩን ተከታትሎ ለህግ የማቅረብ ስራ የፖሊስ መሆኑን ጠቁመው ጉዳዩ የፀጥታ አካላት የሚፈትኑበት ነው ብለዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው የህግ ባለሙያ፤ በመንግስት ከፍተኛ መስሪያ ቤት እንዲህ ያለው ወንጀል ሲያጋጥም ፖሊስ በሁለት መንገድ ምርጫ ሊያደርግ እንደሚችል ጠቅሰው አንደኛ ቀጥታ ጥቆማ ከመስሪያ ቤቱ ሲደርሰው፣ ጥቆማ ካልደረሰው ያገኘውን ፍንጭ መነሻ አድርጎ ምርመራ እንደሚያደርግ አብራርተው፤ ማህበራዊ ድረ ገፅ ላይ “ፈተናው ተሰርቋል” ተብሎ ይፋ በተደረገ ጊዜ ፖሊስ ምን ህል ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ምርመራ ለማድረግ እንደሞከረ መጠየቅ አለበት ብለዋል፡፡ ትምሀርት ሚኒስቴር በበኩሉ፤ በአሁን ወቅት በዋናነት ትኩረት የሰጠው ፈተናው በድጋሚ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ በጥንቃቄ ማካሄድ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ መሆኑን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
ቀደም ሲል ፈተናው ተጠርዞ፣ ታሽጎ፣ በሀገሪቱ በሚገኙ 802 የፈተና ጣቢያዎችና በውጭ ሀገር በሚገኙ 3 ጣቢያዎች ለማድረስ እስከ 3 ወር ይፈጅ እንደነበርና የተዘጋጀው መጠባበቂያ ፈተና በልዩ ግብረ ኃይል እየተመራ፣ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ በ23 ቀን ውስጥ ሁሉንም ጉዳዮች ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ፈተናውን ለመስጠት የታቀደው ከሰኔ 22 እስከ 30 ባለው ጊዜ ውስጥ ሲሆን የረመዳን የፆም ወቅት መሆኑንና የኢድአል ፈጥር በአልም ከተያዙት ቀናት መካከል በአንዱ ሊሆን እንደሚችል በመግለፅ የተያዘው ፕሮግራም እንዲቀየር እየተጠየቀ ቢሆንም ትምህርት ሚኒስቴር ፕሮግራሙን እንደማይቀይር አስታውቋል፡፡
ፈተናው ተሰርቆ መውጣቱ ተረጋግጦ ቀደም ያለው መርሃ ግብር ከተሰረዘ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈተናውን እንዴት መስጠት ይቻላል በሚለው ላይ አመራሮችና ባለሙያዎች ውይይት ማድረጋቸውን ሃላፊው ጠቁመው፤ በ23 ቀናት ውስጥ ማከናወን እንደሚቻል ታምኖበት ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መገባቱን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል ይሄም የተማሪዎችን የጭንቀትና የመቆዘሚያ ጊዜ ለመቀነስ ታስቦ ነው” ገልፀዋል - ይሄም፡፡
የረመዳን ወር መሆኑ እንደሚታወቅና ካለው ችግር አንፃር በአሉ የሚውልበትን ቀን መዝለሉ አማራጭ ሆኖ መገኘቱን ያብራሩት ኃላፊው የረመዳንን ወር “ፆም ከስራ ጋር የታረቀ  ህብረተሰብ በስራ የሚያሳልፈው መሆኑን ሙስሊሙ ህብረተሰብም መንግስት ያለበትን ጫና በአግባቡ ይረዳል የሚል እምነት እንዳለ ተናግረዋል፡፡ አሁን በድጋሚ ከተያዘው ቀን ወደፊት ይራዘም ቢባል የፈተና ማረሚያ፣ ውጤት ማሳወቂያና የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፕሮግራሞችን የሚያፋልስ መሆኑን ያስረዱት ኃላፊው አስቀድሞ የተያዘውን የጊዜ ሰሌዳ ለማሳካት ሲባል ርብርብ ማድረጉ አስፈላጊ ሆኗል ብለዋል፡፡

Read 4077 times